ኢትዮጵያ መድን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል

የ2014 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ ሲጠናቀቅ ከምድብ ሐ ኢትዮጵያ መድን ከስምንት አመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰበትን ድል አግኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ ሲጠናቀቅ ረፋድ 3፡00 ላይ ወደ አንደኛ ሊግ ላለመውረድ ብርቱ ትግል የታዩበት ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰአት እና በሁለት ሜዳዎች ተደርገዋል፡፡ ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ፌድራል ፖሊስ እና ወላይታ ሶዶ ከተማ ተገናኝተው በሶዶ አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡ ተመጣጣኝ ፉክክር በተስተናገደበት እና በሁለተኛው አጋማሽ ሶዶዎች ላለመውረድ ብልጫ ወስደው በተንቀሳቀሱበት አጋማሽ 62ተኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ የግራ መስመር ተከላካዩ ሱራፌል ተሾመ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ 1ለ0 በማሸነፍ በሊጉ መቆየታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ሌላኛው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሀምበሪቾ ዱራሜ እና ጅማ አባ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ በተራራ አናብስቶቹ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ አባቡና ወደ አንደኛ ሊግ ተሸኝቷል፡፡ ጅማ አባቡናዎች ከወትሮው በተሻለ ለመንቀሳቀስ በሞከሩበት እና ጨዋታው ሊጠናቀቅ 20 ደቂቃዎች ሲቀሩ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ፍፁም ጫና በማሳደር ሁለት ጎሎችን አስቆጥረዋል፡፡ 81ኛው ደቂቃ ላይ ልዑልሰገድ አስፋው ከተመስገን ዱባ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ይዞ ከገባ በኋላ ተቀይሮ የገባው ዘርዓይ ገብረስላሴ ወደ ጎልነት በመለወጥ ቡድን መሪ አድርጓል፡፡ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ የቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ እና ወላይታ ድቻ አጥቂ ተመስገን ዱባ ከርቀት ከግራ የአባቡና የግብ ክልል ውጪ በማስቆጠር ሀምበሪቾ 2ለ0 አሸናፊ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ጅማ አባቡና ወደ አንደኛው ሊግ መውረድ ዕርግጥ ሆኗል፡፡


ከሰአት 9፡00 ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያልፈውን ቡድን ለመለየት ተቀራራቢ ነጥብ ያላቸው ነቀምት እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታቸውን ከውነዋል፡፡ በሰው ሰራሽ ስታዲየም ነቀምት ከተማ ረፋድ የተደረጉ ውጤቶትን ተንተርሶ መውረዱን ካረጋገጠው የካ ክፍለ ከተማ ጋር ተገናኝቶ 2ለ2 ጨዋታው ፈፅሟል፡፡
የፌድሬሽኑ የህክምና ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሙኤል የሺዋስ ባስጀመሩት እና በሜዳ ለዕይታ ማራኪ የሆኑ ቅብብሎች በርከት ብለው መታየት በቻሉበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ 12ኛው ደቂቃ ላይ አራት ተጫዋቾች በማለፍ አማካዩ ካሳሁን ገብረሚካኤል ጎል በማስቆጠር የካን መሪ አድርጓል፡፡ ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ በሚታወቁበት ረጃጅም ኳስ ወደ አቻ ውጤት ለመመለስ ኢብሳ በፍቃዱን ዒላማ ያደረጉ ባደረጉ ተሻጋሪ ኳሶች መጫወት የቀጠሉት ነቀምቶች የመጀመሪያው አርባ አምስት ሊገባደድ አንድ ደቂቃ ብቻ ሲቀረው ዳንኤል ዳዊት አስቆጥሮ ወደ ጨዋታ ተመልሰዋል፡፡

ከእረፍት ጨዋታው ሲመለስ አሁንም ወደ መሪነት መሸጋገር የቻሉት የካዎች ናቸው፡፡50ኛው ደቂቃ ላይ ካሳሁን ሰቦቃ ግብ ቢያስቆጥርም ከሁለት ደቂቃዎች መልስ ምኞት ማርቆስ ነቀምት አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ በቀሩት ደቂቃም ግብ መቆጠር ሳይችል ጨዋታው 2ለ2 በማለቁ ነቀምት ወደ ሊጉ ለማደግ መጀመሪያ መወጣት የነበረበትን ዕድል መጠቀም ሳይችል ቀርቷል፡፡


ሌላኛው ተጠባቂ ጨዋታ በኢትዮጵያ መድን እና ደቡብ ፖሊስ መካከል በዩኒቨርሲቲው ሜዳ ላይ ተከውኗል፡፡ ከፍተኛ የመንግስት እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አመራሮች ያስጀመሩት ጨዋታ እጅግ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተካሄደ ነበረ፡፡በአመዛኙ መሀል ሜዳ ፉክክሩ በርክቶ መታየት በቻለበት ጨዋታ ምንም እንኳን የጨዋታው ሂደት ተመጣጣኝነት ቢኖረውም በርካታ ሙከራን በማድረጉ ረገድ የተሳካላቸው መድኖች በፈጠሩት ጫና ግብ አግኝተዋል፡፡ 37ኛ ደቂቃ ላይ ከመስመር መነሻውን ካደረገ ኳስ ቢኒያም ካሳሁን ለያሬድ ዳርዛ ሰጥቶት ወደ ሳጥኑ ሲያሻግር ኪቲካ ጀማ ሲነካት የደቡብ ፓሊሱ ፍፁም ተስፋዬ ኳሷን ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ ወደ ራሱ ግብ ሰዷት መድኖችን መሪ ሆነዋል፡፡ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች መድኖች አንዷን ግብ ለማስጠበቅ በሚመስል መከላከል ተጠምደው በመዋል ጨዋታውን ድል በማድረግ ከስምንት አመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለሳቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የኢፌዴሪ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሀላፊዎች እና የፌዴሬሽን አመራሮች ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ የተለያዩ አካላት ፣ ግለሰቦች ፣ ተቋማት እና ድርጅቶች የሰርተፍኬት ሽልማቶች አበርክተዋል፡፡ውድድሩኝ 3ኛ በመሆን ላጠናቀቀው ሀምበሪቾ ዱራሜ የነሀስ ሜዳሊያ ፣ ሁለተኛ ሆኖ ለፈፀመው ነቀምት ከተማ የብር ሜዳሊያ እና ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለገባው ኢትዮጵያ መድን የወርቅ ሜዳሊያ እና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል፡፡ መድን ከ ደቡብ ፓሊስ እና ነቀምት ከየካ ያደረጉት ጨዋታ ለመሩት ስምንት ዳኛ እና ሁለት ኮሚሽነር የሜዳሊያ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡
በውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን በስምንት ጎሎች ሦስት ተጫዋቾች አጠናቀዋል፡፡ ያሬድ ዳርዛ ከመድን ፣ ኢብሳ በፍቃዱ ከነቀምት እንዲሁም ጉልላት ተሾመ ከአቃቂ ሲፈፅሙ የምድቡ ኮከብ ተጫዋች በሌላ ጊዜ የሚገለፅ ሆኖ መድን ኮከብ ግብ ጠባቂ ጆርጅ ደስታን ኮከብ አሰልጣኝ ደግሞ በፀሎት ልዑልሰገድ አስመርጧል፡፡ የፀባይ ዋንጫ ለጉለሌ ክፍለ ከተማ ሲበረከት ውድድሩን ላስተናገደው ሲዳማ ክልል (ሀዋሳ ከተማ) በመጨረሻም ሽልማት ከተበረከተ በኋላ ውድድሩ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ያጋሩ