[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በመጀመሪያው ዙር የሊጉ ውድድር ጥቂት የግብ ማግባት ሙከራዎችን ያደረጉ ቀዳሚ ክለቦች የሚያደርጉትን ጨዋታ እንዲህ ተመልክተነዋል።
በዘንድሮ የውድድር ዓመት አስገራሚ ግስጋሴ እያደረገ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ሳይጠበቅ ራሱን በዋንጫ ፉክክር ውስጥ በመክተቱ ነገም ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት አጥቦ ለመጓዝ ብርቱ ትግል ማድረጉ እሙን ነው። ከወላይታ ድቻ በተቃራኒ ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ በአንድ ነጥብ እና ደረጃ ብቻ ከፍ ብሎ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር በመታረቅ ከአስጊው ቀጠና በትንሹም ቢሆን ፈቅ ለማለት ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርግ ይገመታል።
በአሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የሚመሩት ወላይታ ድቻዎች የውድድር ዓመቱን በሽንፈት ቢጀምሩትም ከሊጉ ክለቦች የበለጠ 9 ጨዋታዎችን አሸንፈው ራሳቸውን ከመሪዎቹ ተርታ አሰልፈው የመጀመሪያውን ዙር አገባደዋል። ይህንን ፅሁፍ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ በዝውውር መስኮቱ በውሰትም ሆነ በቋሚነት አንድም ተጫዋች ወደ ስብስባቸው ካልቀላቀሉ አራት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ድቻ በአንፃራዊነት በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ ሚዛኑን የጠበቀ ቡድን ይመስላል። በዋናነት በፊትዮሽ እና ጎንዮሽ ስፋት ችምችም ብሎ ለተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ክፍተት ባለመስጠት አቀራረቡን መሠረት የሚያደርገው ቡድኑም የግብ ምንጮቹ በአብዛኛው በረጃጅም ኳሶች እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ ናቸው። ድቻ በአሁኑ ሰዓት ሁለተኛ ደረጃን ቢቆናጠጥም አጠቃላይ የግብ ማግባት ሙከራዎችን በማድረግ ትንሹ ሁለተኛ ቡድን (106) ነው። እርግጥ ጨዋታን የሚወስኑ ግቦችን በማስቆጠር የሚገዳደረው ባይኖርም እንደ ዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን የተጋጣሚን የግብ ክልል የሚጎበኝበት ድግግሞሽ መብዛት ይኖርበታል። የቡድኑን 68.8 % ጎሎች ያስቆጠሩ ሦስቱ አጥቂዎች (ስንታየሁ፣ ምንይሉ እና ቃልኪዳን) ደግሞ በሁለተኛውም ዙር ውድድር መተማመኛ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው።
ካለው አንፃራዊ ጥሩ ስብስብ አንፃር ከሚጠበቅበት በታች ውጤት እያስመዘገበ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ዓመቱን ከአሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ጋር በድል ቢጀምርም በጊዜያዊ አሠልጣኙ ፉዐድ የሱፍ እየተመራ አጋማሹን በሽንፈት አገባዷል። ሁለተኛውን ዙርም አሠልጣኝ ሳምሶን አየለን በመንበሩ ሾሙ የሚጀምር ይሆናል። በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ ደካማ የሆነው ድሬ ሁለተኛውን ዙር በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሎ ካልቀረበ ከፊቱ ያለው አደጋ አስጊ ነው። በመከላከሉ ሦስተኛው ብዙ ግብ ያስተናገደ በማጥቃቱ ደግሞ ከሁለት ክለቦች ጋር በጣምራ ሦስተኛው ትንሽ ግብ ያስቆጠረ የሊጉ ክለብ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ጎል ፊት ያለው ስልነት እጅግ ጥያቄዎች ይነሱበታል። በሊጉም ጥቂት አጠቃላይ ሙከራዎችን (101) እንዲሁም ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን (38) ያደረገ ክለብ ነው። ይህንን ተከትሎ በቦታው መሻሻል ለማምጣት በዝውውሩ ይሳተፋል ተብሎ ቢጠበቅም የግራ መስመር ተከላካዩ አማረ በቀለን በቋሚነት እንዲሁም የመሐል ተከላካዩ ከድር ሀይረዲን እና አማካዩ አባይነህ ፊኖን በውሰት ብቻ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል። እርግጥ በአጥቂ ቦታ ላይ ያሉት ተጫዋቾች ያን ያህል መጥፎ የሚባሉ ባይሆንም ከብዛት ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በዝውውሩ ቢሳተፍ መልካም ነበር። የሆነው ሆኖ በመግቢያችን እንደገለፅነው ስብስቡ መጥፎ ስላይደለ በሥራዎች ወደ መልካም መንገድ ይገባል ተብሎ ይታሰባል።
ቡድኖቹ በየመንገዳቸው ሦስት ነጥብ ስለሚያስፈልጋቸው ጨዋታውን በጠንካራ መንፈስ እንደሚከውኑት ቀድሞ መናገር ይቻላል። በዋናነት ደግሞ በመቀመጫ ከተማው እንኳን ከአንድ በላይ ድል ማስመዝገብ ያልቻለው ድሬዳዋ ማጥቃት ላይ የተመረኮዘ አቀራረብ ሊከተል ይችላል። ወላይታ ድቻም ድሉ ብዙ ጥቅም ቢሰጠውም የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ለብርትካናማዎቹ በመስጠት ቀጥተኝነትን አዘውትሮ ሊንቀሳቀስ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ከመከላከል ወደ ማጥቃት ፈጣን ሽግግሮችን በማድረግ አደጋ ለመፍጠር መውተርተሩ አይቀሬ ነው።
ወላይታ ድቻ በነገው ጨዋታ የአምበሉን ደጉ ደበበ ግልጋሎት በህመም ምክንያት አያገኝም። ከላይ እንደገለፅነው በዝውውሩ ምንም ተሳትፎ ያላደረገው ክለቡ ከአካባቢው የተገኙ ተጫዋቾችን ከነባሮቹ ጋር በማቀናጀት ሁለተኛውን ዙር ለመቅረብ እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ታውቋል። በድሬዳዋ በኩል ግን ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የለም። አዲሱ ተጫዋች አማረ በቀለ መጫወት እንደሚችል ሲታወቅ ከድር ሀይረዲን እና አባይነህ ፊኖ ግን ዛሬ ገና ቡድኑን በመቀላቀላቸው የመሰለፍ ዕድላቸው ጠቧል።
ይህ ጨዋታ በእንስቷ አልቢትር ሊዲያ ታፈሰ አማካይኝነት ሲመራ ለዓለም ዋሲሁን እና ሙሉነህ በዳዳ ረዳት ሚካኤል ጣዕመ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው እንደሚሰየሙ ታውቋል።
እርስ በርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም 11 ጊዜ መገናኘታቸውን ታሪክ ያመላክታል። በግንኙነታቸው የምስራቁ ክለብ ስድስት ጊዜ ድል በማድረግ ቀዳሚ ሲሆን ወላይታ ድቻ አንዱን ብቻ ረቷል። አራት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።
– ሊጉ ከረጅም ዕረፍት እንደመመለሱ ለዛሬ ግምታዊ አሰላለፍ እንደማይኖረን ለመግለፅ እንወዳለን።