ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ሀዋሳ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ላይ የሚያተኩረው ዳሰሳችንን እነሆ።

16ኛው ሳምንት የሚገባደድበት ጨዋታ ለተጋጣሚዎቹ በሰንጠረዡ ሁለት ጫፎች ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ነው። ሀዋሳ ከተማ በቅርብ ርቀት ከተቀመጡት ተፎካካሪዎቹ ከፍ ብሎ ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት ወደ አራት የሚመልስበት ዕድል በዚህ ጨዋታ ውስጥ ይገኛል። በአንፃሩ ጨዋታው ለጅማ አባ ጅፋር የደረጃ ማሻሻያ ምክንያት ባይሆንም ከበላዩ ካለው አዲስ አበባ ከተማ በአንድ ነጥብ ልዩነት ለመጠጋት ይረዳዋል።

ለረጅም ሳምንታት የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሰነበተው እና በመጨረሻ ቦታውን ለሰበታ ከተማ ያስረከበው ጅማ አባ ጅፋር ወደ ማብቂያው ላይ መጠነኛ መሻሻል ቢያሳይም ከወራጅ ቀጠናው መውጣት አልቻለም። ሜዳ ላይ እንደቡድን በሂደት የውህደት ምልክት እየሰጠ ሊጉ ቢጋመስም እንደክለብ ያለበት የፋይናንስ አለመረጋጋት ግን አሁንም እንደተከተለው ነው። ምንም እንኳም ትናንት በወጣ ዜና ጫላ በንቲ ፣ አስጨናቂ ፀጋዬ እና ቦና ዓሊን በውሰት ወደ ስብስቡ ቢቀላቅልም ጅማ ከዕርፍት መልስ ዝግጅት የጀመረ የመጨረሻው ክለብ ነው። ከደመወዝ እና ከሆቴል ክፍያ ጋር በተያያዘም ልምምዱ እየተቆራረጠ ቆይቶ ለነገው ጨዋታ ደርሷል።

በሀዋሳ ከተማ ደጃፍ ግን ከጅማ አባ ጅፋር የተለየ አየር ሲነፍስ ቆይቷል። ከመጨረሻ አምስት ጨዋታዎቹ በአንዱ ብቻ ሽንፈት ያገኘው ሀዋሳ ከተማ በመጀመሪያው ዙር ያሳካውን የሦስተኝነት ደረጃ ምክንያት በማድረግ ለስብስቡ የማበረታቻ ሽልማት ሰጥቷል። ውድድሩ አዳማ ላይ ከመቀጠሉ በፊት ለ20 ቀናት ልምምድ ላይ በቆየው የኃይቆቹ ስብስብ ላይ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዜግነት ያለው ተከላካይ ዳርለስ ካሎንጂ እና አቤኔዘር ኦቴ አዳዲስ ፈራሚዎች በመሆን ተጨምረዋል።

ከተጋጣሚው አንፃር በዝግጅት እና ወቅታዊ ሁኔታም ሆነ በውጤቶቹ መነሻነት ከሚገኝበት የሥነልቦና ደረጃ አንፃር ሁለተኛ ግምት ተሰጥቶት የሚገባው ጅማ አባ ጅፋር በጨዋታው ላይ ግን ተከላክሎ የመጫወት እሳቤ የሚኖረው አይመስልም። ቡድኑ የኋላ መስመር ችግሩ እንዳለ ሆኖ ኳስ መስርቶ በመውጣት ሁለቱን መስመሮች ባማከሉ ከመሀል የሚነሱ ኳሶችን በመጠቀም ወደ ፊት ገፍቶ ለመጫወት የሚያደርገው ጥረት ነገም እንደሚተገበር ይጠበቃል። እንደእዮብ እና መሀመድኑር ዓይነት አጥቂዎቹ ከዳዊት መስዑድ ጥምረት የአማካይ ክፍል በሚመጡ ኳሶች ሀዋሳን ለመፈተን መጣራቸው እንዳለ ሆኖ የኃይቆቹን የመልሶ ጥቃት ለመመከት ያላቸው ብቃት ግን አጠራጣሪ ይሆናል።

ሀዋሳ ከተማ አስተማማኝ የተከላካይ መስመር የሌላቸው ቡድኖች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ይዘው ሊያጠቁት ሲሞክሩ ወደሚፈልገው ወጥመድ ለማስገባት የሚያበቃ ስብስብ አለው። ቅብብሎች አደጋ የሚፈጥሩበት ቦታ ላይ ሳይደርሱ ማቋረጥ እና ከተጋጣሚ ተከላካዮች ጀርባ ለሚሮጡ አጥቂዎቹ ማድረስ ለአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ቡድን የተመቸ አቀራረብ ነው። ነገም ሀዋሳ ለጅማ የጨዋታ ዕቅድ ምላሽ የሚሰጥበት አኳኋን በጨዋታው ላይ ከባባድ ፍልሚያዎችን እንደሚያስመለክተን ይጠበቃል።

ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የሚመሩት ኤፍሬም ደበሌ ሲሆኑ ሸዋንግዛው ተባበል እና ባደታ ገብሬ በረዳትነት ተከተል ተሾመ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሰባት ጊዜ ተገናኝተው ሦስቱን ሀዋሳ ሲያሸንፍ አንዱን ጅማ አሸንፎ በሦስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። ሀዋሳ 8 ፣ ጅማ 6 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

– ሊጉ ከረጅም ከዕረፍት እንደመመለሱ ለዛሬ ግምታዊ አሰላለፍ እንደማይኖረን ለመግለፅ እንወዳለን።