[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ድሬዳዋ ከተማን 1-0 በማሸነፍ በሦስት ነጥብ ልዩነት ቅዱስ ጊዮርጊስን መከተሉን ቀጥሏል።
ሁለቱ ተጋጣሚዎች በተመሳሳይ የ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ሲገቡ በድሬዳዋ በኩል የግራ መስመር ተከላካዩ አማረ በቀለ በአዲሱ ቡድኑ የመጀመሪያ ምርጫ ውስጥ ተካቷል።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረ እና ወደ መጨረሻው ላይ በንፅፅር ንቃት የታየበት ነበር። ጨዋታውን በተሻለ የማጥቃት መነሳሳት ጀምረው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በሂደት ተቀዛቅዘዋል።
ከኳስ ጋር ከሜዳው የመውጣት ምልክት ይሰጥ የነበረው ቡድኑ ደቂቃዎች ሲሄዱ በአመዛኙ ከኳስ ውጪ የሚያሳልፍባቸው አጋጣሚዎች ሲበዙ ሲነጥቅም በመልሶ ማጥቃት ለመሄድ የሚያደርገው ጥረት አስፈሪነት ቀንሶ ነበር። ዋነኞቹ የወላይታ ድቻ ሙከራዎች ይተገኙትም ከቆሙ ኳሶች ነበር። በዋናነት ያሬድ ዳዊት በ6 ፣ 28 ፣ እና 45ኛ ደቂቃ ላይ ከቀኝ ካደሉ ቅጣት ምቶች የላካቸው ኳሶች ዕድሎችን ፈጥረዋል። ሁለቱ በአንተነህ ጉግሳ በግንባር ተግጭተው አንዱ ደግሞ በቀጥታ ወደ ግብ ደርሶ የነበረ ሲሆን ፍሬው ጌታሁን ኢላማቸውን የጠበቁትን የአንተነህ እና ያሬድ ሙከራዎች አድኗል።
ድሬዳዋ ከተማዎች ኳስ መስርተው የመሄድ ዕቅድ እንዳላቸው ቢታይም ከድቻ አንፃር የተሻለ የኳስ ቁጥጥርን ይያዙ እንጂ እስከመጨረሻው ሰንጥቀው የሚገቡ ቅብብሎችን ሲከውኑ ግን አልታየም። ለዚህም ቀዳሚዎቹ ከባድ ሙከራዎች ከሳጥን ውጪ መደረጋቸው አንዱ ማሳያ ነው። 33ኛው እና 39ኛው ደቂቃ ላይ ጋዲሳ መብራቴ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታቸው ኳሶች ሲጠቀሱ በተለይ የመጀመሪያው በግቡ አግዳሚ የተመለሰ ነበር። የዕረፍት ሰዓት ሲቃረብ የድሬ የኳስ ቅብብሎች በተሻለ ሁኔታ ለድቻ የግብ ክልል መቅረብ ሲጀምር በተለይም 43ኛው ደቂቃ ላይ አማረ በቀለ ከግራ መስመር ያሳለፈውን ኳስ ማማዱ ሲዲቤ ወደ ግብ ልኮት ፅዮን መርዕድ እና አንተነህ ጉግሳ አድነውታል።
በሁለተኛው አጋማሽ ድሬዳዋዎች የማጥቃት ጉልበታቸውን ጨምረው ገብተዋል። ፈጠን ባለ ጥቃት ወደ ድቻ ሳጥን በማማዱ ሲዲቤ እና እንየው ካሳሁን አማካይነት የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር። በሂደት ከቆሙ ኳሶች እና ከቀጥተኛ ጥቃት ምላሽ መስጠት የጀመሩት ድቻዎች የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ከነበረበት መንገድ እና የሜዳ ክፍል ላይ ግብ አስቆጥረዋል። 69ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳዊት ራቅ ካለ ወደ ቀኝ ያደላ ቦታ ላይ ያሻማውን የቅጣት ምት ኳስ በግራው የድሬዳዋ ጎል ክፍል ላይ አናጋው ባደግ ወደ ውስጥ ሲልክለት ከደቂቃ በፊት በተሳሳተ የረዳት ዳኛ ውሳኔ ግቡ የተሻረበት ቃልኪዳን ዘላለም ከመረብ አገናኝቶታል።
እንደአጀማመራቸው ያልቀጠሉት ድሬዎች ግብ ካስተናገዱ በኋላ የሰጡት ምላሽ አጥጋቢ አልነበረም። ቅብብሎቻቸው ክፍተቶችን የመፍጠር አቅማቸው ወደ ራሳቸው ሜዳ ያፈገፈጉት ድቻዎችን ማስጨነቅ የቻለ አልሆነም። ይልቁኑም 83ኛው ደቂቃ ላይ ድቻዎች አበባየሁ አጪሶ ከግማሽ ጨረቃው ላይ ለግብ አግቢው ቃልኪዳን ባሳለፈለት ኳስ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበት ቢያገኙም ቃልኪዳን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። 88ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ ከማዕዘን ምት በግንባር ያደረገው ሙከራም ለጎል የቀረበ ነበር። በድሬዎች በኩል ጋዲሳ መብራቴ በጭማሪ ደቂቃ ከአማረ የቀኝ መስመር የተላከውን ኳስ በግንባር የሞከረበት የአጋጣሚ ብቻ የተሻለ ዕድል ሆኖ ሲታይ ከአዲስ ህንፃ በተላከ ኳስ በምንይሉ ወንድሙ የመጨረሻ የመልሶ ማጥቃት ሙከራ ያደረጉት ድቻዎች ጫና ሳይሰማቸው መሪነታቸውን በማስጠበቅ አሸንፈው ወጥተዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ ነጥቡን 31 አድርሶ ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት ዳግም ወደ ሦስት ሲቀንስ ድሬዳዋ ከተማ አሁንም ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ብቻ ከፍ ብሎ ለመቀመጥ ተገዷል።