የአሠልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 1-0 ድሬዳዋ ከተማ

በጦና ንቦቹ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የ9 ሰዓቱ ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሠልጣኞች አስተያየት ተቀብሏል።
ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ስላደረጉት እንቅስቃሴ?

በመጀመሪያው አጋማሽ ድሬዳዋ የተጫወተው አጨዋወት ግልፅ ነው። ሦስት የተከላካይ አማካይ ነበር ያሰለፈው። ወደፊት የማይሄዱ ነገርግን ኳስ የሚነካኩበት ነገር ነበር የበዛው። ይህንን እኔ እንደ ብልጫ አልወስደውም። በሁለተኛው አጋማሽ እኛ በሌላ የአደራደር ቅርፅ ነው የገባነው። ካነበብናቸው በኋላም ተጭነናቸው ተጫውተናል። የተዋጣለት እንቅስቃሴም አድርገናል። ድሬዳዋዎች ኳስ እንደሚችሉ እናውቃለን ግን ውጤታማ የሚያረግ የጎል ሙከራ አላየንም ነበር። ዞሮ ዞሮ መሸናነፍ ያልነበረበት ሳምንት ስለሆነ ሁለተኛ አሸናፊ በመሆናችን ደስ ብሎኛል።

ስለሦስቱ የቡድኑ አጥቂዎች…?

የሦስቱ አጥቂዎች ድምር ጎል ቡድናችንን ውጤታማ እያደረገ ነው ያለው። አስተዋፅዋቸውም በግልፅ ይታያል። ግን እኛ በሁሉም የሜዳ ክፍል ጥንካሬ አለን ብዬ ነው የምገምተው። የሚገባብን ጎልም አነስተኛ ነው። ስለዚህ ሚዛናዊ እያደረግን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው። በየጨዋታው እንቅስቃሴውን እየተቆጣጠርን እንሄዳለን። በአጠቃላይ በዛሬው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ በልምድ አጨዋወት እኛ የተሻልን ነበርን ማለት ይቻላል።

ከመሪው ጋር ስላላቸው የ3 ነጥብ ልዩነት?

በዕለቱ ሆነህ መገኘት ነው። አሁን ሁለተኛ ዙር ላይ ነው ያለነው። ሁለተኛ ዙር ደግሞ የልምድ አጨዋወት ነው የሚያስፈልገው። ያለን ነጥብ እንደተጠበቀ ሆኖ ከእኛ የሚጠበቀው የዕለት ተዕለት የሜዳ አጨዋወታችን ነው ሁሉን ነገር የሚወስነው። እኛ ከፊት እና ከኋላ ያሉትን ተጋጣሚዎቻችንን አናይም። ማድረግ የሚገባንን እያደረግን እያንዳንዱን ጨዋታ የፍፃሜ ያህል እየተጫወትን ቀኑ የሚሰጠንን ውጤት እየተቀበልን እንሄዳለን።

በዚህ ሳምንት እስካሁን 2 ቡድኖች ብቻ ማሸነፋቸው?

በሁለተኛ ዙር ክለቦች ከመጀመሪያው ዙር ድክመታቸው ተጫዋች አስገብተው ነው የሚመጡት። ከሁለተኛ ዙር በኋላ የምታስተካክለው ነገር የለም። ጨዋታዎች እየቀነሱ ነው የሚሄዱት። በእያንዳንዱ ጨዋታ የሚገኙት ነጥቦች ዋጋቸው ከፍ ያለ ነው። ይሄ የተለመደ ነው። የከፋ ነገር ብቻ አይምጣ። በቀጣይ የሚሰጠንን ደግሞ አናውቅም። ስለዚህ ሁሌ ሆኖ መገኘት ነው።

ድሬዳዋ ከተማ – ሳምሶን አየለ

በሜዳ ላይ ስለገጠማቸው ነገር?

በተቃራኒ በኩል ያሰብነው ነው የሆነው። ረጃጅም ኳሶች እየለቀቁ እሱን ተከትሎ በመልሶ ማጥቃት እንደሚመጡ ይታወቃል። ይህ የገመትነው ነው። በእኛ በኩልም በምንፈልገው ልክ ነው። ጥሩ ነው። ኳሱን ይዘን ለመጫወት ሞክረናል። ነገርግን የሜዳው ሦስተኛው ክፍል ጋር ስንደርስ ጎል ለማግኘት ስንደርስ ክፍተቶች ነበሩን። በቀጣይ እሱ ላይ ጠንክረን እንሰራለን። ይህንን ካረምን በመከላከሉም ሆነ ኳስ ይዞ በመጫወት ጥሩ ነን። በአጠቃላይ ጎል የማስቆጠር ጉልህ ክፍተት አለ። እዚህ ላይ እንሰራለን።

ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸው አማካዮችን መጠቀሙ?

አንዱ ችግር እሱ ነው። ከፊት ያሉት ተጫዋቾች ለጎል የተመቻቸ ኳስ የማያገኙት መሰረታዊ ችግር ሦስቱም ተመሳሳይ አይነት የጨዋታ ባህሪ ስለነበራቸው ነው። አሁን በዛ ቦታ በዝውውሩን የሚሸፍንልን ተጫዋች አላገኘንም። በውሰት ካመጣናቸው አንደኛው የዚህ አይነት ባህሪ ያለው ተጫዋች ስለሆነ እሱን ለመጠቀም እንሞክራለን። ክፍተቱም የሚታይ ነው።

በሁለተኛው ዙር ከቡድኑ ምን ይጠበቅ?

በዋናነት ቡድኑን በ2015 በፕሪምየር ሊጉ እንዲቆይ ማድረግ ነው። ከዚህ አንፃር ስራ ይፈልጋል። እኛም ጠንክረን እንሰራለን። ቡድኑንም ከወራጅ ቀጠናው እናተርፋለን ብዬ አስባለው።