ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ በዋንጫ ፉክክር ሩጫው ቀጥሏል

በምሽቱ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋርን 2-0 የረቱት ሀዋሳ ከተማዋች ነጥባቸውን 30 በማድረስ የሦስተኛ ደረጃቸውን አስጠብቀዋል።

ተጋጣሚዎቹ በተመሳሳይ የ3-5-2 አሰላለፍ ሲጀምሩ በውሰት ከሀዋሳ ወደ ጅማ የሄደው ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ ባለቤት ክለቡን ለመግጠም ተሰልፏል።

ጨዋታው በሁለቱም በኩል ጥሩ የማጥቃት ተነሳሽነት እየታየበት ጀምሯል። ጅማዎች በኳስ ቁጥጥር እና አልፎ አልፎ ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ መነሻቸውን ከአማካይ ክፍል ባደረጉ ኳሶች ዕድል ለመፍጠር ሀስቡ እንዳላቸው የሚጠቁም እንቅስቃሴ ነበራቸው። ሀዋሳዎች በበኩላቸው ከሚያቋርጧቸው ኳሶች በቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ያደርጉ ነበር።

የጅማዎች የቅብብል ሂደት 11ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ ዕድልነት ሲቀርብ ዳዊት እስጢፋኖስ ከኢዮብ ዓለማየሁ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ከሳጥን ውስጥ ያደራገው ሙከራ ወደ ላይ ተነስቶበታል። በቀጣዩ ደቂቃ ሀዋሳዎች ተባረክ ሄፋሞ ግብ አስቆጥሮ ኳስ በእጅ በመንካቱ ቢሻርባቸውም ህጋዊ ጎል ለማግኘት ብዙ አልቆዩም። 15ኛው ደቂቃ ላይ ወንድምአገኝ ኃይሉ ሀዋሳዎች ያቋረጡትን እና ተባረክ ሄፋሞ ያረጋጋለትንን ኳስ በግሩም ሁኔታ ሲሰነጥቅለት ብሩክ በየነ የኳሱን ጥራት በሚመጥን አጨራረስ ግብ አድርጎታል።

ከግቡ በኋላ በነበሩት ደቂቃዎች ግን ጨዋታው በጀመረበት ፍጥነት አልቀጠለም። ሀዋሳ ከተማዎች ወደራሳቸው ሜዳ አዘንብለው ከመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን የሚያነፈንፉ ቢመስሉም የጅማ የኳስ ስርጭት ወደ አደጋ ዞን እንይደርስ ከማድረግ ባለፈ ተደጋጋሚ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን አልፈጠሩም። የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን የያዙት ጅማዎችም እንደነበራቸው የኳስ ድርሻ ባይሆንም ሁለት ጊዜ ለግብ ቀርበው ነበር።

19ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ ከበላይ ዓባይነህ የተሻማውን ኳስ እዮብ በግንባሩ አመቻችቶለት ሙሴ ካበላ ከግብ አፋፍ ላይ አምክኖታል። 28ኛው ዳቂቃ ላይ ደግሞ ከተነጠቀ ኳስ ዳዊት የሰነጠቀውን መሐመድኑር ከመጠቀሙ በፊት የሀዋሳው ተከላካይ አዲስዓለም በስህተት ወደ ግብ ቢልከውም ዳግም ተፈራ ይዞታል።
የአጋማሹ የመጨረሻ የግብ ዕድል በሀዋሳ በኩል ሲፈጠር ቡድኑ ሲጠብቅ የነበረው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ወደ ጅማ ሳጥን ቢጣልም የተባረክ ሄፋሞ ሙከራ ኢላማውን አልጠበቀም።

ሁለተኛው አጋማሽ በተመሳሳይ ሁኔታ በጅማዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የቀጠለ ነበር። ቡድኑ በጥሩ ቅብብሎች በሀዋሳ ሳጥን ውስጥ የተገኘባቸው አጋጣሚዎችም አልጠፉም። ከእነዚህም ውስጥ 48ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ከመሐመድኑር ጋር ባደረገው ቅብብል ሳጥን ውስጥ ለጎል የቀረበ ዕድል አምክኗል። በሌላኛው ፅንፍ 55ኛው ደቂቃ ሀዋሳዎች ሌላ መልሶ ማጥቃት አምክነዋል። ተባረክ ሄፋሞ የተጣለለትን ኳስ በፍጥነት ይዞ ወደ ሳጥን ቢጠጋም የመጨረሻ ውሳኔው ሙከራውን ደካማ አድርጎታል።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የጨዋታው ፍሰት ፈጠን ሲል እና ክፍተቶች እየተፈጠሩ ሲታይ ጅማዎች 64ኛው ደቂቃ ላይ በአድናን ረሻድ 67ኛው ላይ ደግሞ በላይ ዓባይነህ ከሀዋሳዎች የቅብብል ስህተት የመነጩ የግብ ዕድሌችን ሳጥን ውስጥ ቢያገኙም ሙከራቸው ኢላማውን ስቷል። ሀዋሳዎች ግን በሁለቱ ሙከራዎች መሀል የሰነዘሩት መልሶ ማጥቃት ሁለተኛ ግብ ሆኗል። 65ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂ የተነሳ እና ብሩክ ጨረፈውን ኳስ መድሀኔ ብርሀኔ ከግራ መስመር ሲያሻግርለት ተባረክ ሄፋሞ በግሩም ንክኪ ጎል አድርጎታል።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የጅማዎች የኳስ ቁጥጥር የመጨረሻ የግብ ዕድል ካለመፍጠሩ በተጨማሪ ቡድኑን ይበልጥ ለመልሶ ማጥቃት አጋልጦታል። 76ኛው ደቂቃ ላይ ወንድምአገኝ ብሩክን ከግብ ጠባቂ ጋር አገናኝቶት ሲሞክር እንዲሁም ከአንድ ደቂቃ በኋላ መድኃኔ ከግራ ያደረሰውን ወንድምአገኝ ከግማሽ ጨረቃ ላይ አክርሮ ሲሞክር አላዛር በድንቅ ሁኔታ ያወጣቸው የሀዋሳ መልሶ ማጥቃት የወለዳቸው ለግብ የቀረቡ ጥረቶች ነበሩ።

ከዚህ በኋላም ጅማዎች ቅብብሎቻቸው ወደ ሳጥን ቢቀርቡም አደገኛ የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ ቆይተዋል። 83ኛው ደቂቃ ላይ መስዑድ መሀመድ በቀኝ ገብቶ ያመቻቸውን ተቀይሮ የገባው ቤካም አብድላ ከሳጥን ውስጥ ያረገው ሙከራ የተሻለው የግብ ዕድል ሲሆን ግብ ጠባቂው ዳግም በቀላሉ ይዞታል። ሀዋሳዎች በጭማሪ ደቂቃም በተባረክ ሄፋሞ ሌላ የፈጣን ጥቃት ዕድል ቢፈጥሩም በውሰት የሰጡት አላዛር ማርቆስ በድጋሚ የግብ ልዩነቱን እንዳያሰፉ አድርጓቸዋል። ጨዋታውም በ2-0 ውጤት በሀዋሳ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በውጤቱም ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 30 በማድረስ ወደ ሦስተኛ ደረጃው ሲመለስ ጅማ አባ ጅፋር በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ለመቆየት ተገዷል።