አርባምንጭ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚሰለጥኑት አዞዎቹ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቀዋል፡፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዳግም ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ከመጀመሪያው ዙር የሊጉ እረፍት መልስ በትላንትናው ዕለት ሁለተኛውን ዙር ከመከላከያ ጋር ያለ ጎል በማጠናቀቅ ወደ ውድድር ተመልሷል፡፡አጥቂው አህመድ ሁሴንን ከወልቂጤ ከተማ ቀደም ብሎ በእጁ ያስገባው ክለቡ በዛሬው ዕለት የሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ዝውውር በውሰት አጠናቋል፡፡

አላዛር መርኔ ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰበትን ዝውውር አጠናቋል፡፡ከሀዋሳ ከተማ ተስፋ ቡድን እስከ ዋናው ድረስ ለተከታታይ አምስት አመታት ተጫውቶ ያሳለፈው ይህ ግብ ጠባቂ በከፍተኛ ሊጉ አምና በኢኮስኮ ዘንድሮ ደግሞ በአሰልጣኝ ዳዊት ታደለው ገላን ከተማ ቆይታ ካደረገ በኋላ ዛሬ መዳረሻው አርባምንጭ ሆኗል፡፡

ሌላኛው ፈራሚ ኤርሚያስ ሰበረ ነው፡፡ በመስመር አጥቂነት በቡታጅራ ከተማ እና ዘንድሮ ደግሞ በንግድ ባንክ አሳልፎ የነበረው ይህ ተጫዋች አሁን ደግሞ አርባምንጭን መቀላቀሉ ዕርጥጥ ሆኗል፡፡

ያጋሩ