በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ ተቀምጦ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ማግኘቱ ታውቋል።
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደካማ የውድድር አመትን እያሳለፈ የሚገኘው ሰበታ ከተማ በጊዜያዊ አሰልጣኙ ብርሀን ደበሌ መሪነት የሁለተኛውን ዙር ውድድር ከቀናት በፊት ሲጀምር በቅዱስ ጊዮርጊስ 3ለ1 መረታቱ ይታወሳል፡፡ ቡድኑ አሁን ያለበትን ክፍተት ለመሙላት ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ መቀላቀሉን ስራ አስኪያጁ አቶ አለማየሁ ምንዳ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡
ጋብሬል አህመድ የመጀመሪያው የክለቡ ፈራሚ ሆኗል፡፡ የጋና ዜግነት ያለው እና ኢትዮጵያ ውስጥ ከአስር አመታት በላይ በመጫወት እያሳለፈ የሚገኘው የቀድሞው የደደቢት፣ ሀዋሳ ከተማ፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ፋሲል ከነማ እና በድጋሚ ወደ ሀዋሳ ተመልሶ በተጠናቀቀው አመት ቆይታ ያደረገው ይህ የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋች ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ያለፉትን ስድስት ወራት ቆይታ አድርጎ ቀሪ የውል ጊዜ እየቀረው በስምምነት ከተለያየ በኋላ ማረፊያውን ሰበታ አድርጓል፡፡
ዓለምአንተ ካሳም ሰበታን ተቀላቅሏል፡፡የቀድሞው የደደቢት እና የኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ስፍራ ተጫዋች በያዝነው የውድድር አመት መከላከያን ተቀላቅሎ በክለቡ ያሳለፈ ቢሆንም በቅርቡ ከክለቡ ጋር በስምምነት ተለያይቶ ወደ ሰበታ ከተማ አምርቷል።
ገዛኸኝ ባልጉዳ ደግሞ ሦስተኛው ፈራሚ ነው፡፡ የቀድሞው የነቀምት ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና እና አዲስ አበባ ከተማ አጥቂ በመከላከያ አመቱን ከጀመረ በኋላ እንደ ዓለምአንተ ከቀናቶች በፊት ቀሪ ውል እያለው ተለያይቶ አሁን መዳረሻው ሰበታ ሆኗል፡፡