ኢትዮጵያ ቡና አንድ ተጫዋች በውሰት አግኝቷል

በከፍተኛ ሊግ ጥሩ የውድድር ጊዜ ያሳለፈውን ግዙፉን የተከላካይ አማካይ ተጫዋች ኢትዮጵያ ቡና በውሰት አገግኝቷል።

ከቀናት በፊት በነበረው ዘገባችን በከፍተኛ ሊግ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር መልካም የሚባል የውድድር ጊዜ ያሳለፉትን አጥቂ ኢብራሂም ከድር ፣ ፊሊሞን ገ/ፃድቅ እና የተከላካይ አማካይ አብነት ደምሴን በውሰት ለመውሰድ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን መጠቆማችን ይታወሳል። ከእስከ ትናትናው ረፋድ ድረስ ሦስቱን ተጫዋች ለማግኘት ጥረት ያደረገው ኢትዮጵያ ቡና በስተመጨረሻ አጥቂውን ፊሊሞን ገ/ፃድቅ እና የመስመር አጥቂው ኢብራሂም ከድር የውሰት ጥያቄ ሳይሳካ ቀርቷል። 

ምንም እንኳን ሁለቱ ተጫዋቾች ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርተው የመጫወት ፍላጎት ቢያሳዩም ያላቸው ቀሪ የአራት ወር ኮንትራት በመሆኑ ለተጨማሪ ዓመት በኤሌክትሪክ ለመቆየት አዲስ ውል አድሰው በውሰት እንዲሄዱ የተጠየቁት ተጫዋቾቹ ጥያቄውን ባለመቀበላቸው የውሰት ዝውውራቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

ሆኖም የአንድ ዓመት ቀሪ ኮንትራት ያለው ግዙፉ የመሐል ተከላካይ አብነት ደምሴ የውሰት ዝውውሩ ተቀባይነት በማግኘቱ ለስድስት ወር ኢትዮጵያ ቡናን ለማገልገል መስማማቱ ተረጋግጧል። አብነት ደምሴ ከዚህ ቀደም በፌደራል ፖሊስ እና በወላይታ ድቻ ቆይታ ያደረገ ሲሆን ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመቀላቀል ለተከላካዮች ሽፋን በመስጠት እና በማጥቃቱም እንዲሁም ጎል በማስቆጠርም ለቡድኑ ጥሩ አገልግሎት ሰጥቷል።