“አልጠራጠርም ! ራሴ ነኝ የምቀጥለው ብዬ አምናለሁ” አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና (ኢትዮ ኤሌክትሪክ)

“አሳድጌ ፕሪምየር ሊግ ላይ ሳልታይ ገፉኝ ማለት እችላለሁ…

“ውጤት ካላመጣማ ይፈርሳል እየተባለ ይናፈስ ሁሉ ነበር…

“ሁለተኛውን ዙር ስንጀምር ባንክ እየተነሳ መጣ ያ ደግሞ ልጆቹ ላይ ትንሽ መደናገጥ ፈጠረ ፤ እኛ ጠብቀን የነበርነው አርሲ ነገሌን ነበር…

ሁለት ጊዜያት ያህል የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን ነው፡፡በቀድሞው አጠራሩ መብራት ሀይል የአሁኑ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፕሪምየር ሊጉ ከ1990 ጀምሮ ሲጀመር ተሳታፊ የነበረው እና 2010 ላይ ለመውረድ የተገደደው ቡድኑ ወደ ታችኛው የሊግ ዕርከን ከወረደ በኋላ ወደ ሊጉ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡የቀድሞው ተጫዋቹን እና አሰልጣኙ የነበረው ክፍሌ ቦልተናን ባለፈው አመት ለሁለት የውድድር ዘመን በመቅጠር ዳግም ለመመለስ ሲጥር የነበረው ቡድኑ አምና ሁለት ዕድል አግኝቶ ባይሳካለትም በዘንድሮው የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ስር ጅማ ከተማን ፣ አየር ሀይልን እና ሰበታ ከተማን ከዚህ ቀደም ባሳደጉት አሰልጣኝ እየተመራ አንጋፋው ክለብ በድጋሚ ወደ ሊጉ ብቅ ብሏል፡፡የክለቡን ከአራት አመታት በኋላ መመለሱን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገናል፡፡

አሰልጣኝ ክፍሌ በቅድሚያ የውድድር ዓመቱ ጉዞ እንዴት ነበር ከሚለው እንጀምር ?

“ዘንድሮ ከጅምሩ የምድብ ድልድል አወጣጡ ግልፅ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ የምድብ አባት ነው መሆን ያለብህ ፤ ከዛ ዕጣ ይወጣል። በዕጣው ሦስቱም ይገባሉ ፤ አምና በነበረው ውጤት መነሻነት። አሁን ግን አባት በዕጣ ነው የተደለደለው። የአምና ውጤት ታይቶ ድልድሉ ዋጋ ሊሰጠው ይገባል እና ሁሉን ያማከለ ባላንስ ያልነበረ ድልድል ነበር፡፡ ቢሆንም ውድድሩ ጠንካራ ነበር ፤ ጠንካራ ቡድኖች ናቸው የነበሩት። ይሄ እንደሚሆን ቀድሜ አውቃለሁ ፤ አንደኛ ዙር ሆሳዕና ነው፡፡ ሆሳዕና ሜዳው ያስቸግራል ብለን ገምተን ነበር ፤ ግን ጥሩ ነው። በመሪነት ጨረስን ወደ ባህርዳር ቀጥሎ ሄድን። ፉክክሩም ጠንካራ እና በጣም በጣም ከባድ የነበረ ነው ማለት እችላለሁ፡፡

በ2013 ከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ኤሌክትሪክ ከጫፍ ደርሶ በመከላከያ ተበልጦ ነበር ሳይሳካለት የቀረው ያለፈው ዓመት ውጤት ቡድኑ ላይ የጨመረው ነገር ይኖር ይሆን ?

“አዎ የሚገርምህ ነገር ሱፐር ሊጉ ላይ ብዙ ስለሰራሁ ውጤታማም ስለነበርኩ 100 ፐርሰንት ያሳልፋል የሚል ዕምነት ነበራቸው። አምና በጣም ጠብቀው ነበር ፤ ይሄ ደግሞ እግር ኳስ ነው እንግዲህ የሚቻለኝን አደረኩ። ስቀጠር ተወዳድሬ ነው ህዳር 21 አካባቢ ነው የተቀጠርኩት። እንዲህ ዓመት ከምናምን በኮቪድ ውድድር ተቋርጦ ነበር። እኔ ደግሞ ከህዳር በኋላ ነበር የመለመልኩት ፤ የምርጫ ምርጫ ውስጥ ያሉ ልጆችን ነው የመረጥኩት እና በዛ ሰዓት ምንም መሠረት አልነበረውም። በ21 ቀን ዝግጅት እንደዛ ተጫውቼ በመጀመሪያ ጨዋታዬ ተሸነፍኩ ፤ በመቀጠል አቻ አቻ። ዘጠኝ ቡድን ነበሩ በእኛ ቡድን አንዳንድ ምድቦች ላይ አስራ ሁለት ቡድኖች ነበሩ ፤ መሸጋሸግ ነበረበት። ዘጠኝ ሆነን በእኛ ምድብ ላይ የተወዳደርነው ዕኩል ቁጥር ሊሆን ይገባ ነበር ፤ መሆን አልነበረበትም። ውድድሩን ስንጀምር ሦስት አራት ጨዋታዎች ላይ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ነበርን። ከዛ ተነስተን አምስት ስድስት ጨዋታ በማሸነፍ አንደኛውን ዙር አንደኛ ሆነን ጨረስን። መጀመሪያ ያልተስተካከለ ነገር ነበረው። ዝግጅት በደንብ አላደረግንም ፣ እኔም ስቀጠር ማስታወቂያ ወጥቶ ሁለት ወር ነው የፈጀው ፣ ኢንተርቪው ሲያጣሩ ፈተና ሲሰጥ በዚህም ብዙ ጊዜ ቆዩ። አምና ከዚህ አንፃር የመጣው ውጤት ጥሩ ነው ግን እኔ ሳልቀጠር በወቅቱ መከላከያ ሰፈሬ የወዳጅነት ጨዋታ ያደርግ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲጫወት አንድ ለዜሮ ተሸንፏል። የተወሰነውን አይቻለሁ እና ስድስት ወር ያህል ነው የተዘጋጀው። ደብረዘይት ገብተው ወጣቶችንም ይዘው ልምድ ያላቸውን ይዘው ከፍተኛ ዝግጅት ነው ያደረጉት እና እኛ ያንንም አይተናል፡፡ እኔ ደግሞ እግዚአብሔር አይደለሁም ታች ሊግ ላይ ሰርቼ ውጤታማ ስለሆንኩ አምና ሁለተኛ በእነዚህ መንገድ ስለወጣው አስደሳች አልነበረም። ዘንድሮ ስንጀምርም ተስፋ መቁረጥ ነበረው። ውጤት እያመጣን ስንሄድ ነው ከፍተኛ ድጋፍ መደረግ የጀመረው። እንደውም ውጤት ካላመጣማ ይፈርሳል እየተባለ ይናፈስ ሁሉ ነበር፡፡ እና በጣም አስቸጋሪ ዓመት ነበር ዘንድሮ በመጨረሻም ግን እግዚአብሔር ይመስገን ተሳክቷል፡፡

በውስጥህ ዘንድሮ ይሳካል የሚል ዕምነትህ ምን ያህል ነበር ?

“ዘንድሮ ጥሩ ነገሩ ከአምና ብዙ የወጡ ልጆች የሉም። አንድ ልጅ ተከላካይ የነበረው ወልደአማኑኤል ሰበታ የገባው ሌላው ፣ ተከላካይ ነስረዲን ቡና ገባ። ሁለት የመሀል ነበር ተከላካይ በአንዴ ያጣነው። እዛ ቦታ ላይ ነበር የሰጋሁት እንጂ ሌላ ቦታ ላይ ብዙም አልፈራሁም። ቡድኑ አምናም ውጤታማ ነበር ፤ ዘንድሮ በእነኚህ ባጣዋቸው ቦታ ላይ ሰው ለመተካት ሞከርኩ። የተወሰኑ ተጫዋቾችን ጨመርኩ እርግጠኛ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንወጣለን የሚል ተስፋ ነበረኝ። ግን ባንክ እኛ ምድብ በመምጣቱ እንደሚከብደን እናውቅ ነበር። ሀላባም ሀላባ በጣም የሚታወቅ ጠንካራ ቡድን ነው። እነኚህን ቡድኖች ሳይ ‘ይሄ ውድድር ትንሽ ቻሌንጅ አለው’ አልኩኝ። ከጠነከርን በዚህ ውስጥ ማለፍ እንደምንችል ግን አመንኩ። እኔ ክለብ ደግሜ አላውቅም። አንደኛው ዓመት ትሰራለህ ካልሆነ ትባረራለህ። እኔ ግን ኤልፓ ስገባ የጠቀመኝ ሁለት ዓመት መፈረሜ ነው፡፡ አንድ ዓመት ሆኖ ቢሆን ሁለተኛውን ዓመት የምቀጥል አይመስለኝም ነበር። መቶ በመቶ ባለፈው ዓመት በዛች አጭር ጊዜ ሰርቼ እንዳሳልፍ ነበር፡፡ ግን ሁለት ዓመት ስለነበረ የፈረምኩት ብዙ ጭቅጭቅ ነበር። ‘እንዴት ሁለት ዕድል አግኝተን አናልፍም ?’ (ከፕሪምየር ሊግ ከወረዱት ጋር የተደረገውን ጨዋታ ጨምሮ) የሚል ግምገማ እና ጭቅጭቅ ነበር። ቀን ላይ 8 ሰዓት ስብሰባ ገብተን ማታ 1 ሰዓት ላይ ነው የወጣነው። ከሀዋሳ ያኔ እንደሄድን እና ብዙ ክርክሮች ስለነበሩ በሰዓቱ ‘ሸኙኝ !’ ነበር ያልኳቸው። ‘ይሄ ውጤት ለእኔ ጥሩ ነው በቃ እናንተ መግባት ነበር ፍላጎታችሁ አልተሳካም የዝግጅት ጊዜ አጭር ነው፡፡ እኔን ስትቀጥሩ ዘግይታችኋል ፣ እንደምፈልገው ተጫዋች አልያዝኩም በዚህ ውስጥ ሰርቼ ሁለተኛ ወጥተናል። እንደገና ደግሞ ከፕሪምየር ሊግ ከወረዱት ጋር የተደረገው ነገር ትክክለኛ አካሄድ አልነበረም።’ አልኩ። እንደ ኳስ ስታየው ዕድሉን እንጠቀም ነው እኛ እንጂ አንድ ወር ከሀያ ቀን መርነናል። ይሄ ማለት ስድስት ሳምንት እና ከዚህ በላይ ዝግጅት ያስፈልገው ነበር። ከፕሪምየር ሊግ መጥተው የነበሩ ቡድኖች ደግሞ በአስር ቀን ውስጥ ከውድድር ወደ ውድድር መጥተው ነው ውድድር ያደረግነው። እኛ ከተቻለ ይሄንን ዕድል እንጠቀም የሚል ሀሳብ ነበረን። ቢያንስ ዕኩል እንድንሆን አንድ ወር የዝግጅት ጊዜ ይሰጠን ካልሆነ ከውድድር መጥተው ሊሆን አይችልም ነበር። በወቅቱ ዕድሉን የተጠቀሙት ራሳቸው የፕሪምየር ሊግ ቡድኖች ናቸው እና ያን ያን ለማስረዳት ሞከርኩ። ግን ያው ቡድኑም ትልቅ ቡድን ነው ፣ 70 ዓመቱን ሊያከብር ነው ፣ ብዙ ወጣቶችን ያሳደገ ሁለት ጊዜሞ የኢትዮጵያ ቻምፒዮን የሆነ ፣ የመጀመሪያውን ፕሪምየር ሊግ የበላ እና በርካታ ወጣቶችን ለብሔራዊ ቡድን የሚያስመርጥ ከፍተኛ ደጋፊም ያለው ቡድን ነው፡፡ ይሄ ቡድን በአንዴ እንዲወጣ ነበር እኔም ስመጣ ቦርዱም በአዲስ መልክ ሲመጣ የታሰበው። ዘንድሮ ግን እውነት ለመነጋገር አጀማመር ላይ ተስፋ በመቁረጥ ብዙም ድጋፍ አልነበረውም። ከፈለገ ባለው ነገር ይስራ ፣ ደመወዛቸው ይቀነስ ከፌዴሬሽኑ ግማሽ በግማሽ እንደገና ደግሞ ወጣት ብቻ ይዞ ይቀጥል ከ20 እና ከ17 ዓመት በታች ቡድኖች መርጦ በእነዛ ይቀጥል የሚሉ ብዙ አወዛጋቢ ነገሮች ነበሩ፡፡ ግን እንደእግዚአብር ፍቃድ ጠንክሮ መስራት ጥሩ ነው ባለው ነገር ላይ ጠንክረን በመስራት ለውጥ እየመጣ ሲሄድ እነሱም ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ መጡ። እንደ ዘንድሮ ደግሞ በጣም ተቀራርበን የሰራንበት ጊዜ የለም። ከቦርዱ ጋር በጣም ተቀራርበን ነበር ፤ በመጨረሻም የሰራነው ያም እንዲሳካልን ሆኗል፡፡

ንግድ ባንክ ነጥብ በጣለበት ሳምንት ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንገባለን የሚል ሀሳብ ነበረህ ? አንድ ጨዋታ ቀርቷችሁ ስለነበር ?

“አላሰብኩም። ሁለተኛው ዙር ላይ እኛ እና ባንክ በዚህ ደረጃ እንፎካከራለን ብለን አላሰብነውም ጭራሽ። በስምንት ነጥብ ስለምንበልጠው ትኩረት ያደረግነው አርሲ ነገሌ ላይ ነው፡፡ አርሲ ነገሌ ከመጀመሪያ ጀምሮ ተፎካካሪው ነበር። አንደኛውን ዙር ስንጨርስ በመሪ ሂደት መጨረስ እንችል ነበር። እኛ አራት ሰዓት ተጫውተን ለዕረፍት ወደ አዲስ አበባ ተመለስን። እነሱ በነጋታው አንድ ለአንድ ከገላን ጋር ወጡ ፤ ያ በመሆኑ በመሪነት ጨረስን። ባንክ አዲስ ነው ግን አውርደን አላየነውም። ሁለተኛውን ዙር ስንጀምር ባንክ እተነሳ መጣ ያ ደግሞ ልጆቹ ላይ ትንሽ መደናገጥ ፈጠረ ፤ እኛ ጠብቀን የነበርነው አርሲ ነገሌን ነበር፡፡ እንደገና አርሲ ነገሌ ደግሞ መሞራት ጀመረ። አንድ ሳምንት ሳይጓዝ መልሶ ነጥብ ጣለ። በዚህ ሂደት አንድ ነጥብ ሁሌ ከባድ ነው ፤ በሥነ ልቦና ጫና የመሸከም ልጆቹ ላይ በጣም ያላቸውን አውጥተው በነፃነት የመጫወት። አንደኛው ዙር ላይ እንዲህ መቀራረብ ቢኖር ሁለተኛው ዙር አለ ትላለህ ብዙ ጨዋታ ስላለ። ሁለተኛ ዙር ላይ ግን እያንዳንዱ ጨወታ አስጊ ነው ፤ እንቅልፍ ታጣለህ። እኔ አላውቅም አሁን አሁን ነው ይሄን ሁለት ሦስት ቀን መተኛት የቻልኩት። አልዋሽህም አርባ ቀን እዚህ ብንቆይ አስር ቀን ነው ጥሩ እንቅልፍ የተኛሁት ሠላሳ ቀኑ ሀሳብ ነው። ምክንያቱም ጥለህ የምታስተካክልበት ሦስተኛ ዙር የለም ። ሁለተኛ ዙር ላይ ሆነን ነጥብ ላለመጣል ልጆቹም እኛም ጫና ውስጥ ገባን። በጣም ጥሩ ይሆናሉ የምንላቸው ልጆች እንደምንፈልገው አልሆን አሉ። ከአምቦ ስንጫወት አስረኛ ደረጃ ላይ ያለ ቡድን ነው ተበልጠን ጎል ስተው 0ለ0 ነው የወጣነው ፤ የባሰ ደግሞ ተደናገጥን በዚህ ጨዋታ። እና እናስተካክላለን ስንል ቾንቤ የሚሉት አሰልጣኝ የሀዋሳ ሰው ነው ፣ ሀላባ እሱን ከቀጠረ በኋላ ተሻሽሎ የመጣ ቡድን ነው ፣ ተጫዋች ጨምሮ እሱም ደግሞ ከመጣ ጀምሮ ቡድኑም ለውጥ አድርጎ ነው የመጣው ፣ አንድም ነጥብ ሳይጥል እየሰበሰበ የመጣ ቡድን ነው፡፡ ከእነሱም ከባድ ተጋድሎ አድርገን በልጦናል ግን 1ለ1 ሆንን። እና በጣም እየተጣበበ መጣ ደረጃችንም ነጥባችንም ባንክም ከፍተኛ ተስፋ በማድረግ እኛ አርሲ ነገሌን ስንጠብቅ እሱ እየተጠጋን መጣ። ስለዚህ ከዛ የሦስት ቡድን ሩጫ ሆነ እና ግን በመጨረሻ የፈጣሪን ስራ አላውቅም ብቻ የቦርድ ሰዎች በቅርብ ስለሚሰሩ ‘ምንድነው ችግሩ ?’ ተባብለን ተሰበሰብን ፤ ልጆቹንም ተሰበሰቡ። ‘የአዕምሮ ጉዳይ ነው ጫና ለመሸከም እንዴት ነው መስራት ያለብን ?’ የሚለው ላይ ተነጋገርን። ከዛ ውጪ በቃ ልጆቹም ነፃ እንዲሆኑ የምንመገብበትን ሆቴል ትተን አቫንቲ የሚባል ሆቴል መናፈሻ ያለው የባህርዳር ኃይቁ ዳር ራት እዛ እንዲበሉ ነፃነት እንዲሰማቸው ሞከርን። በዚህ በዚህ ጥሩ እደሆንን ማሸነፍ ጀመርን። አዕምሮ ላይ ነበር ችግሩ ምንም የኳሱ ችግር የለም። እኛ ስንጥል ደግነቱ ተከታያችንም ይጥላሉ ፤ በተለይ አርሲ ነገሌ። ያልፈናል እያልን በመጨረሻ አርሲ ነገሌን ባንክ አሸንፎ ባልታሰበ ሁኔታ የሁለት ነጥብ ልዩነት መጣ። አሁን ማድረግ ያለብን ተነጋገርን። ‘እጃችን ላይ ነው ያለው ባንክ ይመጣል ነጥብ ይጥላል አይጥልም የሚለውን ነገር ማሰብ የለብንም በእጃችን የያዝነውን እያሸነፍን ከሄድን ቻምፒዮን እንሆናለን እጃችን ላይ ያለውን ብቻ ማጣት የለብንም’ በሚለው ላይ አወራን። ይሄ መሆኑ ደግሞ ቆርጠን እንድንገባ አደረገን እና በቀጣይ ሁለት ጨዋታዎችን ካሸነፍን እናልፋለን። ስለ ባንክ ማሰብ የለብንም ስለ አርሲ ነገሌም ማሰብ የለብንም ያሸንፉ እኛም እናሸንፍ በእጃችን ያለውን እንዳናጣ ብለን ነበር። ደግነቱ ሁለቱ ሲጫወቱ ባንክ አሸንፎ አርሲ ነገሌ ቀረ። እኛ ደግሞ ከሁለቱም ስለ ተጫወትን እስከ መጨረሻው ፉክክር ነበረው። የመጨረሻ ባለፉንበት በባለፈው ጨዋታ እኛ አሸንፈን ባንክም እየተጫወተ አንድ ደቂቃ ቀርቷል። ሊያልቅ እኛ ጨርሰናል ግን አንድ ደቂቃ ቀርቶናል ይሉናል። ጨዋታ ጨርሰን ሜዳ ውስጥ ቆመን እንሰማለን። አቻ አለቀ ሲባል ሜዳ ላይ የምንይዘው የምንጨብጠው ጠፋን። እስከ መጨረሻው ቀን ይረስ እንቅልፍ እያጣን እዚህ ደረስን ይሄን ባናሸንፍ ኖሮ እንደ ገና አምስት ቀን መጠበቅ ነበረብን። ከባቱ ጋር ተገናኝተን እንደገና ማሸነፍ አለብን። በለእሱ ደግሞ እንቅልፍ አጥቶ መዘጋጀት ቢሆንም በጊዜ አሸንፈን አረጋገጥን። ፈጣሪን በጣም አመሰገንኩ። የመጨረሻ ደስታ ነው የተሰማኝ ፤ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

በከፍተኛ ሊጉ ረዘም ያለ ጊዜ ሆኖሀል ወደ ፕሪምየር ሊግ ከፍ ብሎ ለማሰልጠን ያለህ ውጥን ምን ይመስላል ? ዕድሉን የምታገኝ ይመስልሀል በሰበታ ከገጠመህ አንፃር ?

“አዎ ሰበታን ይዤ ምንም ሳይሸነፍ አሳልፌ ቤተሰብ ጋር እያለው በእናንተ ሚዲያ ላይ ነው ያየሁት አዲስ አሰልጣኝ መቀጠሩን። በጣም ገረመኝ እኔ አላሰብኩም። አንድ አምስት ቀን አርፌ ምልመላ ላደርግ ነበር። የተወሰነ ቀን ኮንትራት ነበረኝ እና እቀጥላለሁ የሚል ነገር ነበረኝ። አላውቅም ብዙ ግብ ግብ ተፈጠረ እጅግ በርካታ ደጋፊዎች በወቅቱ በእኔ ምክንያት የታሰሩ ሁሉ ነበሩ። ከፍተኛ ተቃውሞ ነበር ሚዲያውም ዕገዛ አደረገልኝ ግን አልተሳካም። መጨረሻ ላይ በጊዜ አሰልጣኝም አልተቀጠረም በኋላ ላይ ውበቱ መጣ። አጋጣሚ ነፃ ስለነበረ እሱ ተቀጠረ ፤ ከዛ በፊት ግን ማንም አልመጣም ብዙ አተካራዎች ብቻ በወቅቱ ነበር፡፡ ይሄ ሲሆን ሞራሌ በጣም ተነካ። ለምሳሌ ሀድያ አሰልጣኝ መንቾን እስከ አንደኛው ዙር አይተውታል እኔ ግን አሳድጌ ፕሪምየር ሊግ ላይ ሳልታይ ገፉኝ ማለት እችላለሁ። በጣም ግፍ ነው የሰሩት። በህይወቴ በጣም ነበር ያን ጊዜ የተሰማኝ። ሥልጠና ሁሉ አስጠላኝ። በኋላ ላይ ከስንት ጊዜ ቆይታ ወደ ሥልጠና ዓለም እስቲ ከታች አሁንም ልስራ መብራት ኃይልን ልመልስ ብዬ መብራት ኃይል ተወዳድሬ ነው የገባሁት። ድሮ ተጫውቼበታለሁ ፣ አሰልጥኛለሁ ፣ ሥልጠና የጀመሩኩበት ተጫውቼ ሻምፒዮን የሆንኩበት ቡድን ነው። ቤቴ ነው ብዬ አልኮራሁም ፤ ከ35 አሰልጣኝ ተወዳድሬ ነው ሰበታ ላይ ባመጣሁት ውጤት ነው የተቀጠርኩት። አምና ተፎካካሪ ሆንን ዘንድሮ ቡድኑን አሳድጌያለሁ። ጥቅማ ጥቅሙ ላይ ላንስማማ እንችላለን ፤ አንደኛው ዙር ሲያልቅ ቃል የገቡልኝ። እኔ በሰዓቱ የገንዘብ ቃሉ ሳይሆን የስራ ዋስትና ይሰጠኝ ብዬ በቃል ነው የጠየኩት። ኮንትራቴ ሰኔ 30 ያልቃል የሁለት ዓመቴ እና የሥራ ዋስትና ይሰጠኝ ብዬ ጠይቄያለሁ። ፕሪምየር ሊጉ ላይ መስራት ስለምፈልግ በግልም በዚህ ጉዳይ ከቦርዱ እና ከኃላፊዎቹ ጋር የተነጋገርንበት ነው፡፡ ፕሪምየር ሊጉ ላይ እስቲ ሥራዬን ልይ የሚል ነው። በዛ ያው ቃል ገብተውልኛል።

‘ካላሳለፍክ ልትቀጥል እትችልም ካለፈ ግን ትሰራለህ’ የሚል በስልክ ከአንድም ሦስት የቦርድ አባላት ቃል ገብተውልኛል። በመሀል እኔ እንደውም የሥራ ዋስትና ካላገኘው ስራውን እንኩ ብዬ ነበር፡፡ይሄ ደግሞ ሰበታ ላይ ለፍቼ ለፍቼ የደረሰብኝን ስለማውቀው ነው። የምትለፋው ለማደግ ነው። ይሄ ካልሆነ ደግሞ ምን ትርጉም አለው ፤ ሱፐር ሊግ ላይ መስራት በጣም ከባድ ከባድ ነው፡፡ በተገባልኝ ቃል መሠረት በጥቅማጥቅም ካልተለያየን በስተቀር በተለያየ ነገር የገቡልኝን ቃል አይጠብቁም ብዬ አላስብም። ተነጋግረን ካልተስማማን በስተቀር የሚለወጥ ነገር ይኖራል ብዬ አልጠራጠርም ራሴ ነው የምቀጥለው ብዬ አምናለሁ፡፡

ኤሌክትሪክ ካሳለፈበት ሁኔታ አንፃር ወደ ሊጉ ከማለፍ በዘለለ በወጣቶች የማመን ስሙን እና ተፎካካሪነቱን መልሶ የሚያገኝ ይመስልሀል ?

“አዎ እኔ እዛው ላይ ነው የምሰራው። ኤሌክትሪክ ትልቅ ማህበራዊ ኃላፊነቱን የሚወጣ ክለብ ነው፡፡ ብዙ የስፖርት ዓይነት አለው። የሴቶች ቡድን አለው ፣ የታዳጊ እግር ኳስ ቡድኖች በደረጃ አለው እና ከሦስት መቶ በላይ ከነቤተሰቦቻቸው ብዙ ስፖርተኛ ያቀፈ ቡድን ነው። ከድሮ ጀምሮ ከፍተኛ ሀገራዊ ግዴታውን የሚወጣ ትልቅ ክለብ ነው፡፡ በጋሽ ሀጎስ ጊዜ እኔ ሦስት ዓመት ነው ኤልፓ ሲ ውስጥ የሰራሁት በዓመት አስር ተጫዋች አሳድግ ነበር። በጣም ነበር ስራውን የወደድኩት ፤ ቋሚ ስራዬን ትቼ። ኤልፓ የራሱ መለያ የራሱ አጨዋወት ያለው ክለብ ነው። በጣም የሚታወቀው ወጣቶችን በማሳደግ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ነው ሙገር የሚባል ቡድን የመጣሁ ኤልፓ አሁን 70ኛ ዓመቱን ሊያከብር ነው፡፡ ግማሽ ያህል ብሔራዊ ቡድን ከኤልፓ ያደጉ ነበሩ አሁን እንደዚህ ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን አልነበረም ፤ ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን ነበር። ኤልፓ ታዳጊ ላይ ከዚህ በፊት ስለሰራው በእኔ ጊዜ የበለጠ የቀደመው ባህል እንዲዳብር የበለጠ ከ20 ፃመት በታች ቡድኑ ላይ ከአሁን በኋላ ተጫዋቾች ለማግኘት ትኩረት አድርጌ እከታተላለሁ። የኛን ብቻ አይደለም የሁሉም ቡድን ታዳጊዎችን አያለሁ። ይሄን ስል ግን ነባር ተጫዋች አያስፈልጉም ማለቴ አይደለም። ምንያህል ዘንድሮ እንዴት እንደጠቀመን እናውቃለን። ቡድን በማነሳሳት ፣ ቡድኑን ሼፕ በማድረግ የሜዳ አሰልጣኝ ሆኖ ፤ ሳሚ ልምሻም። በሌላ በኩል ከሁለቱ ውጪ አብዛኛዎቹ 98 ፐርሰንት ወጣቶች ናቸው። ወጣቶች መሀል ላይ በሰል ያለ ቡድኑን የሚመሩ ተጫዋቾች ያስፈልጋሉ። ስለዚህ የበለጠ ወጣት ላይ ትኩረት አድርጌ ነው የምሰራው፡፡ ይሄ ባህል እንዲዳብር የምችለውን አደርጋለሁ ፤ ለክለብ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም መሠረት ስለሚሆን፡፡

ቡድንህ ወደ ሊጉ እንዲያድግ ከፍ ያለ አስተዋፅዖ የነበራቸው ተጫዋቾች እነማን ነበሩ ?

“አሁን ኢብራሂም ከፍተኛ ግብ አግቢ ነው፡፡ እንዳለ ዘውገ አምናም የቡድኑ ሞተር ነበር ፤ ተሰጥኦ ያለው ተጫዋች ነው፡፡ አንዳርጋቸው ይላቅ ሁለተኛው ዙር የመጣው ፣ ግብ ጠባቂው ዘሪሁን እነ ስንታየው በርካታ ናቸው። አምና ባደገበት ዓመት የውድድሩ ኮከብ ፀጋ ዘንድሮ ደግሞ በበለጠ ተንቀሳቅሷል። ሌላው ደግሞ ተአምር ነው ማለት ይቻላል። ፌድራል ፖሊስ ራሴ ነው ያሳደኩት ወታደር ነበር። አንድ ሁለት ወር ፌድራል ፖሊስ ሰርቻለሁ። ያኔ ያሳደኩት ልጅ ነበር አብነት ደምሴ፤ ዘንድሮ ክስተት ነበር። እነዚህ ሁሉ ተጫዋቾች ቡድኑን በደንብ አግዘው ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንድንገባ ሆኗል፡፡”

ያጋሩ