ቤኒናዊው የግብ ዘብ ጅማ አባ ጅፋርን ተቀላቅሏል

በአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመራው ጅማ አባ ጅፋር ያለፉትን ዓመታት በኢትዮጵያ ያሳለፈውን ግብ ጠባቂ በቋሚነት ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል ስምምነት ሲፈፅም ተከላካይም በውሰት አምጥቷል።

በወራጅ ቀጠናው ቅርቃር እየዳከረ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር በውድድር አጋማሹ የዝውውር መስኮት በስፋት ባይሳተፍም በውሰት ጫላ በንቲ፣ አስጨናቂ ፀጋዬ እና ቦና ዓሊን ከከፍተኛ ሊግ እንዳገኘ ዘግበን ነበር። አሁን ባገኘነው መረጃ ደግሞ ክለቡ አንድ ተጫዋች በውሰት እንዲሁም አንድ ተጫዋች በቋሚነት ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

ጅማን ለማገልገል በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ የሚገኘው ተጫዋች የግብ ዘቡ ሀሪሰን ሄሱ ነው። ቤኒናዊው ግብ ጠባቂ ከ2009 ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ለኢትዮጵያ ቡና ሲጫወት የነበረ ሲሆን በኮቪድ-19 የተሰረዘው የውድድር ዓመት ጨምሮ ሁለት ዓመታትን ደግሞ በባህር ዳር ከተማ ግልጋሎት ሰጥቶ ነበር። ከባህር ዳር ከወጣ በኋላ ያለፉትን 6 ወራት በሀገሩ ቤኒን ያለ ክለብ የቆየው ግብ ጠባቂ ትናንት አዲስ አበባ በመግባት ከጅማ ጋር ስምምነት ፈፅሟል።

በውሰት አባጅፋሮቹን የተቀላቀለው ሌላኛው ተጫዋች ደግሞ የውድድር ዓመቱን በከፍተኛ ሊጉ በቤንች ማጂ ቡና ያሳለፈው አካሉ አቲሞ ነው። በምድብ ለ እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ ቤንች ማጂ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ ሲያደርግ በነበረው ፉክክር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገው የመሐል ተከላካይ እንደ ሀሪሰን በትናንትናው ዕለት የውሰት ውሉ ፈርሟል።

ሀሪሰን እና አካሉን ጨምሮ ከቀናት በፊት በውሰት የመጡት ጫላ፣ አስጨናቂ እና ቦና የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት ውል ቢፈርሙም ጅማ ከደሞዝ ጋር በተያያዘ በቀረበበት ክስ ውል እንዳያፀድቅ በመታገዱ ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ የተጫዋቾቹ ውል እንዳልፀደቀ አውቀናል። በነባር ተጫዋቾቹ የቀረበው የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄ በከፊል ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነገ አልያም ከነገ በስትያ ዕግዱን አንስቶ ውሉ እንዲፀድቅ እንደሚያደርግም ይጠበቃል።

ያጋሩ