ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለስ ትልቅ ድርሻ ከነበራቸው ተጫዋቾች መካከል ሁለቱ ይናገራሉ

“ቡድኑ ብቻም ሳይሆን እኔንም በግሌ ወደ ላይ የመጣውበት ነው…ግብ ጠባቂ ዘሪሁን ታደለ

” እኔ መቼም ቢሆን ተስፋ አልቆርጥም…አጥቂው ኢብራሂም ከድር

ዘሪሁን ታደለ – በቅዱስ ጊዮርጊስ ለአስር ዓመታት ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥም ከወጣት እስከ ዋናው ድረስ ሀገሩን አገልግሏል፡፡ 2010 ላይ ጊዮርጊስን ለቆ ወደ ጅማ አባ ጅፋር ቢያመራም የተሳኩ ጊዜያት ነበሩት ማለት አይቻልም። 2013 ላይ ግን ወደ ከፍተኛ ሊግ በመውረድ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመቀላቀል በሁለተኛ ዓመቱ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ኮከብ ግብ ጠባቂ በመሆን ያጠናቀቀው እና ወደ አዳማ ከተማ በውሰት ለማምራት ጥያቄ ቢቀርብለትም ክለቡ ፍቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ እዛው ቆይቷል።

ኢብራሂም ከድር – ሰበታ ከተማን ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማስገባቱ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ የነበረው እና ዘንድሮ ሰበታ ከተማን በመልቀቅ የቀድሞው አሰልጣኙ ክፍሌ ቦልተናን ጥሪ ተቀብሎ ለኤሌክትሪክ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የመመለስ ትልቅ ድርሻ ያበረከተው ሌላኛው የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ኢብራሂም ከድር ደግሞ የቡድኑ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ አጠናቋል።

ሶከር ኢትዮጰያ የኢትዮ ኤሌክትሪክን ወደ ፕሪምየር ሊግ በማስመልከት ከሁለቱ ተጫዋቾች ጋር ቆይታ አድርጋለች።

ዘሪሁን ታደለ …

የውድድር ዓመቱ ጉዟችሁ እንዴት ነበር ?

“አምና መከላከያ ሲገባ ከጫፍ ደርሰን ነበር የተመለስነው። ዘንድሮ ገና ከዝግጅታችን ጀምረን ባለፈው ያጣነውን አሁን እንደምናሳካው እና እስከ መጨረሻው ታግለንም ቢሆንም እንደምንም ብለን እንደምንገባ ሁላችንም ጠንክረን ለመስራት ተነጋግረንበትም የመጣንበት ነገር ነው፡፡የመጀመሪያው ዙር ሲጀመር ሆሳዕና ላይ ነበር ዘጠኝ ጨዋታዎች ተደርገው የነበረው፡፡ እና እዛ ላይ በቃ አንድ አንድ አስበን የሄድነው የነበረው ሁሉንም ጨዋታዎችን በበላይነት ለመወጣት እና ካለን የማሸነፍ ፍላጎት የተነሳ ሁላችንም አዕምራችንን አዘጋጅተን ነበር የሄድነው፡፡ እንዳሰብነውም ሳንሸነፍ ነው የመጣነው ፤ አንደኛውን ዙር በአንደኝነትም ጨርሰን ነበር፡፡ ሁለተኛው ዙር ላይም ያንን ነገር ለመድገም እና በዛው በነበረን ሁኔታ ይበልጥ የተሻሉ ነገሮችን ጨምረን ለመሄድ ነበር ያሰብነው። እንደ ፈጣሪ ደግሞ ያ ነገር አልቀጠለም ፤ የመጀመሪያውን ጨዋታ በባንክ ተሸንፈን ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ግን የማሸነፍ ሪትም ውስጥ ገብተን ሳንሸነፍ እያሸነፍን አቻም እየሆንን ወደ ፕሪምየር ሊጉ በመግባት ቻምፒዮን ሆነን ጨረስን፡፡

የእግርኳስ ህይወትህ በተለይ ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት ከዚህ ቀደም እንደነበረህ ነው ማለት አይቻልም ፤ መቀዛቀዞች ነበሩበት። ይህ ስኬት ምን ያህል የቀድሞ ዘሪሁንን ያሳየናል ብለን እናስብ ?

“መቀዛቀዙ የሆነው እና እንዲሆንም ያስገደደው ሁኔታ እንደሚታወቀው እዚህ ሀገር ላይ ከአሰልጣኞች ጋርም ሆነ ከተለያዩ አካላት ጋር ግንኙነትህ በጣም የተስተካከለ ወይ ደግሞ የተሳሰረ ካልሆነ እስከ መጨረሻው እግር ኳስ የምታቆምበት ሁኔታ ነው የሚፈጠረው። አሁን እንዳየኸው ከሆነ ወደ ተሻለ ወደ ነበርኩበት ሁኔታ እየመጣው ነው ብዬ ነው የማስበው። ምክንያቱም አንድ ተጫዋች ተደጋጋሚ ስታጫውተው ፣ ተደጋጋሚ ኃላፊነት ሰጥተኸው ከፊት ስታወጣው ያለውን አቅም እስከ መጨረሻው አውጥቶ እሱም ውጤታማ ይሆናል ቡድኑንም ውጤታማ ያደርጋል፡፡ እኔ አሁን የምልህ መብራት ኃይልን አሁን ስላሳደኩኝ ብቻም ሳይሆን ስኬቱ እኔን ራሴን ወደ ላይ ያመጣኝ ነገር ነው፡፡ ቡድኑ ብቻም ሳይሆን እኔንም በግሌ ወደ ላይ የመጣውበት ነው፡፡ከዚህ በፊት ጅማ በነበርኩበት ወቅት ተሸፍኜ በተቀመጥኩበት እና ከሆንኳቸው ነገሮች አሁን በተሻለ የምነሳሳበት አልፎም ወደ ላይ የመጣሁበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብዬ ነው የማምነው፡፡

 

እንደ ቀደመው የፕሪምየር ሊግ ተጫዋችነትህ ከፍ ብሎ ስለ መጫወት ምን ታስባለህ ?

“እግር ኳስ ተጫዋች እና ግብ ጠባቂ አንድ ዓይነት ሚና እንዳለው ሆኖ ግን ይለያያል። ማለት የዕድሜ ሁኔታህም ራሱ ላይ ቢሆንም ራሱ ግብ ጠባቂነት በጣም ዕድሜህም ሄዶ የምትጫወተው ቦታ ነው። እኔ እንደዚህ ስልህ እኔ ዕድሜዬ ሄዷል ማለቴ ሳይሆን ጊዮርጊስ ቤት ሳድግ 2000 ላይ ሚቾ ነው ያሳደገኝ። እንደ አጋጣሚ ቢ ለመጫወት ህፃን ሆኜ (እነፋሲል ያውቃሉ እነሱም ናቸው ያሳደጉኝ) የነበረው ሚቾ ነው አይቶኝ ‘ሰውነቱ ጥሩ ነው እና ቁመቱም የተሻለ ነገር አለው’ ብሎ አስቦ ዋናው ቡድን ላይ በሦስተኛ በረኛነት ያመጣኝ። አስር ዓመት ቆይቻለሁ ጊዮርጊስ ቤት። በመሀል ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥም ተጫውቻለሁ። ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን ራሱ ተጫውቻለሁ። ያ እኔን በይበልጥ የተሻለ እንድነሳሳ እና ጥሩ እንድሆን አድርጎኝ ነበር። በወቅቱ እና በሰዓቱ እግር ታውቀዋለህ ትወጣለህ ትወርዳለህ። ጅማ አባ ጅፋር ከሄድኩኝ በኋላ ነው ብዙ ነገሮቼ የተበላሹት ብዬ ነው የማስበው። ምክንያቱም ትንሽ እግርኳስ እንደለመድከው አይሆንልህም። ካሳለፍክበት እና ከነበርክበት ሁኔታ አንፃር እንደፈለከው የማትሆንበት ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። በወቅቱ ኮቪድም ገብቶ ስለነበር የተወሰኑ ወራቶችን ቤታችን ተቀምጠን ነበር ሁላችንም። ከዛ በኋላ ነው ራሴን ይበልጥ እንደ አዲስ ማነሳሳት አለብኝ የሚሉ ነገሮችን አስቤ እና ሆኜ ወደ መብራት ኃይል መምጣት አለብኝ ቡድኑንም አሳድጌ ራሴም አብሬ ማደግ አለብኝ የሚለውን በማሰብ የመጣውት። ያም ነገር ተሳክቶልኛል ብዬ ነው የማስበው አሁን ላይ፡፡

ዘንድሮ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ ያበቃው ስኬት ምን ነበር ትላለህ ?

“ለስኬታችን ትልቁ ነገር ምንድነው አንድ ላይ ነገሮች እና ሁኔታዎችን በህብረት ነው የምናደርገው። አንድ ላይ በመነጋገር ሥራዎቻችንን አሰልጣኙ በሚሰጠን የስራ ኃላፊነት በመወጣት አንድ ሆነን ቡድኑን አምጥተነዋል ብዬ ነው የማስበው። አንድነታችንን በዚህ ነው የምገልፀው፡፡

ኢብራሂም ከድር…

ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ዓመቱ እንዴት አለፈ የውድድር ጉዞ እንዴት ነበር ?

“ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ዓመቱ ጥሩ ነበር። እና በመጀመሪያ ደረጃ ከዝግጅቱ ጀምሮ በጥሩ መንፈስ ነው ክለቡም ሆነ አሰልጣኛችንም ሆኑ በጥሩ መንፈስ ነው የተቀበሉን። ጥሩ ካሊቲ ያለቸውም ተጫዋቾች ነበሩ። እና በጣም ደስ ይል ነበር ፤ ጥሩ ፍቅርም ነበረን፡፡ በልምምድም ሆነ በሆቴልም በሁሉም ረገድ ጥሩ ፍቅር ነበር እና ለዛም ነው አንደኛ ሆነን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ልንገባ የቻልነው፡፡

ሰበታ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግ ትልቅ ድርሻ ነበረህ ፤ በፕሪምየር ሊጉ ላይም ተመልክተንህ ነበር። ከክለቡ ጋር ስትለያይ ግን ቁጭት በውስጥህ ነበር ?

“ማለት አንዳንዴ የማያስማሙ ነገሮች ይኖራሉ በውስጥህ፡፡ አንደኛ ደረጃ እኔ ሰበታ ውሌን ከማራዘሜ በፊት ሌላ ክለብ ጠይቆኝ ነበር፡፡ ያው ተጫዋች ስትሆን ደግሞ ለነበርክበት ክለብ ቅድሚያ ትሰጣለህ። ያው ካልተስማማህ ነው የምትለያየው ፤ ተስማምቼ ግን ፈረምኩ። ከፈረምኩ በኋላ የእኛን ሀገር ውላችንን ታውቃለህ መቼስ በቢሮ ደረጃ ነው የምንፈርመው። ፌዴሬሽን ግን አልፈረምኩም ነበር። ዝግጅት ከገባው በኋላ ብዙ ጊዜም አልሰራሁም ልጆች መቀነስ አለባቸው ተብሎ ውል ያራዘምን ልጆች ተቀነስን ከዚህ ቀደም ደግሞ ሌላ ክለብ እንደ ፈለገኝ እና የፈለገኝ ክለብ ጋርም መሄድ እንዳልፈለኩኝ እንዲሁም ለነበርኩበት ክለብ ቅድሚያ መስጠት አለብኝ ብዬ ነው የነገርኳቸው። በወቅቱ ስፈርም ቢሮ ሁሉም ባለበት ነበር። መጨረሻ ላይ ይሄ ሲከሰት ‘እንዴት እንደዚህ ታደርጉኛላችሁ ?’ ብዬ ቁጭ አድርጌ ነግሬያቸዋለሁ፡፡ ያው እንደ ተጫዋች እንደ ቤተሰብ በክለቡ ስቆይ ሦስት ዓመቴ ነበር ፤ ይሄ ማለት ከቤተሰብም በላይ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገርም ይፈጠርብኛል ብዬ አስቤም አላውቅም አንድም ቀን ፤ ውስጤን ተጎድቼ ነበር። እውነት ለመናገር አዕምሮዬ በጣም እስኪሰማኝ ድረስ እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ አዝነው ነበር ፤ ያው እግር ኳስ ነው፡፡ እኔ መቼም ቢሆን ተስፋ አልቆርጥም። መቼም ቢሆን የፈለገ ይሁን ተስፋ መቁረጥ የሚባል አስቤም አላውቅም። አንድ ቀን እግርኳስ ስለሆነ እንደሚስተካከል አውቀዋለሁ፡፡ ዋናው ጠንክሮ መስራቱ ነውና ያንን ነገር ጠንክሬ ሰርቼ ደግሞ አሳይቻለሁ። አሁን በኤሌክትሪክ ቤት ነኝ ብዬ ነው የማምነው፡፡

በከፍተኛ ሊጉ በተደጋጋሚ እያበብክ ትገኛለህ። ሰበታም እያለህ ቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ ጎል አግቢ ነበርክ። ዘንድሮም በተመሳሳይ በኤሌክትሪክ በጎል አስቆጣሪነቱ ውስጥ አለህ። በከፍተኛ ሊጉ ላይ ራስህን በደንብ ታሳያለህ የከፍተኛ ሊጉን ያህል በፕሪምየር ሊጉ ላይ እንዳትደግመው ያደረገህ ምንድነው ? ይሄንንስ ለመሻሻል ምን ታስባለህ ?

“አዎ በከፍተኛ ሊጉ በጣም ከባድ ነው። ለእናንተ አልነግራችሁም እና በጣም ቻሌንጅ የሚጠይቅ ውድድር ነው፡፡ ወደ ላይ ለመምጣትም ስለሆነ የሚገባውም ቡድን አንድ አንድ ስለሚባል በጣም ቻሌንጅ የሚጠይቅ ነው፡፡በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ደግሞ ደግሞ ስትመጣ ዕድል ይፈልጋል እንደ ሱፐር ሊግ አይደለም ፤ በጣም ዕድል ይፈልጋል። አንዳንድ አሰልጣኞች ያው ሞክረውክ የማይሆን ከሆነ ቶሎ ያባሩሀል። ተጫዋችን ደግሞ በተደጋጋሚ ስትሞክረው ነው አቅሙን የምታየው። አሁን እኔን የሚያውቁ አሰልጣኞች ተደጋጋሚ ዕድል ይሰጡኛል፡፡ፐርፎርማንስ ይወጣል ይወርዳል ይሄ የሚያጋጥም ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የእግርኳስ ሂደት ነው። ግን አሰልጣኝ የሚያውቅህ ከሆነ አይቶህ በቀጣይ ያስተካክላል ብሎ ያስባል። አንዳንድ አሰልጣኞች ደግሞ አንድ ዕድል ብቻ ሰጥተው ያንን ዕድልህን ለቀጣይ እንዳትጠቀም ያደርጉሀል። አንተ ደግሞ ችሎታህን የምታሳድገው ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ስታደርግ ነው፡፡ በእግርኳሱ ደግሞ የልምምድ ጀግና እና የጨዋታ ጀግና የሚባልም አለ እና ሜዳ ላይ ተደጋጋሚ ዕድል አለማግኘቴ ነው እንጂ የተሻለ ነገር አለኝ፡፡

በሰበታ የነበረህን ስኬት አሁንም ኤሌክትሪክን በማስገባቱ ረገድ ሲደገም በውስጥህ ምን ተፈጠረ ?

“አዎ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ በፊትም ኤሌክትሪክን አውቀዋለሁ ጥሩ ክለብ ነው ፤ ጥሩ ቤት ነው፡፡ እኔ አሁን በክለቡ ብዙ ጊዜ አሳልፋለሁ ብዬ አስባለሁ። ከክለቡ ጋር በጣም ደስ ብሎኛል። አሁን ራሱ ከቤሰቦቼ ጋር ራሱ ቻምፒዮን ከሆንም በኋላ ራሱ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኹኝ ነው። ስለዚህ ክለብ ለማንም መናገር አልችልም ያው የሚያውቀው ያውቀዋል ፤ የማያውቀውም በታሪክ ሊሰማ ይችላል፡፡ በጣም ጥሩ ክለብ ነው፡፡ ለታዳጊዎችም ለሁሉም ማለት ይቻላል እስከ ፕሪምየር ሊግ ድረስ ያደረሰ ክለብ ነውና በጣም ደስ የሚል ቡድን ነው። ምንም ዓመት ሙሉ ምንም ነገር ሳይጎልብን እንደ ቤተሰብ እንደ ወንድም ቀርበው ሁሉን ነገር ሲያደርጉልን ነበር ፣ ሲያማክሩን ነበር፡፡የምንፈልገውን ነገር ቀርበው ስንጠይቃቸው ነበር። እንደ ወንድም እንደ አባት እየሆኑልን እነሱም በጣም ደስ የሚል ቤት ነውና በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፡፡

ከፍተኛ ሊጉን በተሻለ በፕሪምየር ሊጉም ቢሆን የመጫወት ዕድሉ ነበረህ የሁለቱ ሊጎች ልዩነት ምን ይመስላል ?

“ቅድም እንዳልኩህ ነው። በከፍተኛ ሊግ አንዴ ለመውጣት ነው የምትጫወተው። ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ብቻ ስለሆነ ያንን ለማሳካት በጣም ቻሌንጅ ይጠይቃል ብዬሀለው፡፡ ፕሪምየር ሊግ ስትሄድ ደግሞ ለመቆየት ነው የሚባል ነገር አለ። ከፍተኛ ሊግ ለመግባት ስለምትጫወት ፕሪምየር ሊግ ለመቆየት የሚል አዕምሮ ሁሉም ውስጥ መኖሩ ነው ልዩነቱ፡፡