የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በአዳማ ከተማ ጅማሮውን ባደረገው የሊጉ ሁለተኛ ዙር ውድድር የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች በሁለተኛው ድህረ ፅሁፋችን ተመልክተናቸዋል።

👉 ተከላካዮች በግብ አስቆጥሪነት

በጨዋታ ሳምንቱ በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች በድምሩ አስራ አምስት ግቦች የተቆጠሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ በተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች ከመረብ ያረፉ ነበሩ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰበታ ከተማን ሲረታ የመሀል ተከላካዩ ፍሬምፖንግ ሜንሱ ከቅጣት ምት መነሻውን ያደረገን ኳስ ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ጨዋታ በረከት ሳሙኤል የሰበታን የአቻነት ግብ ከማዕዘን ምት መነሻ ባደረገ ኳስ አስመዝግቧል።

የሀዲያ ሆሳዕናው ወጣት የመሀል ተከላካይ ቃለዓብ ውብሸት እና የባህርዳር ከተማው ፈቱዲን ጀማል ከማዕዘን የተሻማን ኳስ በግንባር ገጭተው ሲያስቆጥሩ አዲስ ተስፋዬ በእንቅስቃሴ ከክፍት ጨዋታ የተሻማን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ እንዲሁም መሀሪ መና በተመሳሳይ በእንቅስቃሴ የተገኘን አጋጣሚ ወደ ግብነት በመቀየር ግብ ማስቆጠር ችለዋል።

ግብ የማስቆጠር ደመነፍስ ያላቸው የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች እጥረት ባለበት እግርኳሳችን የተከላካይ መስመር ተሰላፊ ተጫዋቾች በዚህ መጠን ግብ ሲያስቆጥሩ መመልከት ትኩረትን የሚስብ ነው።

👉 አማኑኤል ገ/ሚካኤል አሁንም አስቆጥሯል

የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለተኛው ዙር ጅማሮ ሰበታ ከተማን ሲረታ ወሳኟን ግብ ያስቆጠረው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ነበር።

በጨዋታው የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ አለመኖሩን ተከትሎ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ለወትሮው ከሚጫወትበት የመስመር አጥቂነት ሚና ይልቅ በፊት አጥቂነት በጀመረበት የሰበታ ከተማው ግጥሚያ አማኑኤል ከወትሮው በተሻለ በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የመጨረሻ ውሳኔዎችን ከፍ ባለ የራስ መተማመን ሲያሳልፍ ተመልክተናል።

በሁለተኛው አጋማሽ በ79ኛው ደቂቃ በከነዓን ማርክነህ ተቀይሮ እስኪወጣ ድረስ የተሻለ የጨዋታ ጊዜን ያሳለፈው አማኑኤል በ56ኛው ደቂቃ ሀይደር ሸረፋ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ አጋማሽ ያደረሰውን ኳስ ከሁለቱ የሰበታ ከተማ የመሀል ተከላካዮች ጋር ታግሎ በግሩም ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል። ግቧ ቡድኑን ዳግም መሪ ያደረገች መሆኗ ደግሞ ዋጋዋን ከፍ ያደርገዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከሱፐር ስፖርት ጋር ቆይታ ያደረገው ተጫዋቹ በንግግሩ ውስጥ ይስተዋልበት የነበረው የራስ መተማመን እጅግ የሚያስገርም ነበር። በንግግሩም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሌም ቢሆን ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን እንደመሆኑ በሁለተኛው ዙር ወደ ግብ አስቆጣሪነት በመመለስ የተሻለ ነገር ለቡድኑም ሆነ ለራሱ ስለማድረግ እንደሚያልም እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ዘንድሮ ዋንጫ እንደሚያነሳ በልበ ሙሉነት ሲናገር አድምጠናል።

ከአስራ አንድ ወራት በኋላ በሊጉ ወልቂጤ ከተማ ላይ የመጀመሪያ ግቡን በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረው አማኑኤል በዚህ የራስ መተማመን መጫወቱን ከቀጠለ በቀጣይ በግብ አስቆጣሪነቱ እንደሚዘልቅ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

👉 የሰለሞን ደምሴ እና አቡበከር ኑሪ ጉዳይ

በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ሰበታ ከተማዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 በተሸነፉበት ጨዋታ የሰበታው ግብ ጠባቂ ሰለሞን ደምሴ በእግርኳስ ህይወቱ በመጥፎ ጎኑ ከሚያስታውሳቸው ቀናቶች አንዱን አሳልፏል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን የቅዱስ ጊዮርጊሱን ጨዋታ ጨምሮ በአራት ጨዋታዎች (የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎችን በተከታታይ) በቋሚ ተሰላፊነት የጀመረው ግብ ጠባቂው ሰለሞን በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ከተቆጠሩት ሦስት ግቦች ሁለቱ በቀጥታ በእሱ ጥፋት የተገኙ ነበሩ። ፍሬምፖንግ ሜንሱ ያስቆጠራት የመጀመሪያ ግብ ስትቆጠር የተሻማውን የቆመ ኳስ ለመቆጣጠር የሰራው የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ለግቧ መነሻ ሲሆን አዲስ ግደይ ያስቆጠራት ሦስተኛ ግብም ስትቆጠር ሱሌይማን ሀሚድ ከመስመር ያሻማውን ኳስ መቆጣጠር አለመቻሉን ተከትሎ አዲስ ግደይ ግቧን በቀላሉ አስቆጥሯል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም በተፈጠረው አጋጣሚ ክፉኛ ያዘነው ወጣቱ ግብ ጠባቂው ሜዳ ላይ ተደፍቶ ሲያለቅስ የተመለከትንበት መንገድ ልብ የሚነካ ነበር።

ሰበታ ከተማ በ2011 የውድድር ዘመን ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድቡ የበላይ ሆኖ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሲያድግ በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ይመራ በነበረው ስብስብ ውስጥ እጅግ ቁልፍ ሰው የነበረው ወጣቱ ግብ ጠባቂ ቡድኑ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ካደገ ወዲህ ግን ያለው አበርክቶ እጅግ አነስተኛ ሆኗል።

ግብ ጠባቂው ቡድኑን በደንብ ማገልገል በሚችልበት በዚህ ዕድሜው በተጠባባቂነት እንዲያሳልፍ መገደዱን ተከትሎ የተጫዋቹ የራስ መተማመንም ሆነ የሜዳ ላይ ብቃቱ የመውረዱ ነገር የሚያጠያይቅ አይሆንም። በመሆኑም አሰልጣኞች በተለይም ወጣት ግብ ጠባቂዎችን የሚጠቀሙበት መንገድ ከጨዋታ ደቂቃ እና ከኃላፊነት ክብደት እንዲሁም በስህተቶች ውስጥም ቢሆን እነዚህን ግብ ጠባቂዎች ከመጠበቅ አንፃር ሊታይ ይገባል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ከዚህ ቀደም ብቅ ብለው እንደጠፉ ሌሎች ተጫዋቾች እነዚህን ገና ወደ ፊት ብዙ የሚጠበቅባቸውን ተጫዋቾች ልናጣ እንችላለን።

በተመሳሳይ ባህር ዳር ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር አንድ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማዎች ሲመሩ ቢቆዩም አዲስ አበባ ከተማዎች የባህር ዳር ከተማው ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑሪ ከቡድን አጋሩ ሰለሞን ወዴሳ ወደ ኋላ የተመለሰለትን ኳስ በአግባቡ መቆጣጠር አለመቻሉን ተከትሎ በተገኘች ግብ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

አቡበከር በተመሳሳይ ቡድኑ በቅዱስ ጊዮርጊስ በተሸነፈበት የመጀመሪያው ዙር ጨዋታም በተመሳሳይ ቡድኑን ዋጋ ያስከፈለች ስህተት የፈፀመ ሲሆን ተጫዋቹ መሰል ስህተቶችን ከጨዋታው ለመቀነስ ጠንክሮ መስራት ይኖርበታል።

👉 ሙጂብ ዳግም በፋሲል ከነማ

በፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ዘንድ አብዝቶ የሚወደደው ሙጂብ ቃሲም ዳግም በፋሲል ከነማ መለያ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር አንድ አቻ ሲለያይ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ተሰልፎ መጫወት ችሏል።

አዳማ ከተማን ለቆ በ2009 የክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ፋሲል ከነማን የተቀላቀለው ተጫዋቹ በፋሲል በነበረው ቆይታ ከጥሩ የመሀል ተከላካይነት ወደ ድንቅ አጥቂነት በመሸጋገር በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በሊጉ ከአቡበከር ናስር ቀጥሎ ሁለተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ማጠናቀቁ አይዘነጋም። ታድያ ይህን ተከትሎ በበርካታ ክለቦች ሲፈለግ የነበረው አጥቂው ወደ አልጄሪያው ጄ ኤስ ካቢሊ ማምራቱ አይዘነጋም።

በአልጄሪያ የነበረው ቆይታ በተለያዩ ምክንያቶች አለመሳካቱን ተከትሎ ከሳምንታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ከፋሲል ከነማ ጋር ልምምድ ሲሰራ የቆየው አጥቂው እስከ ውድድር ዘመኑ መጠናቀቂያ ድረስ ወደ ቀድሞ ቤቱ የሚመልሰው ስምምነት መፈፀሙን ተከትሎ በክለቡ መለያ የመጀመሪያውን ጨዋታ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ማድረግ ችሏል።

በጨዋታው እሱን ተክቶ ዐፄዎቹ ቤት የደረሰው ነገርግን በሚጠብቀት ልክ ቡድኑን ማገልገል ካልቻለው ኦኪኪ አፎላቢ ጋር ተጣምሮ የጀመረው ተጫዋቹ በመጀመሪያው ጨዋታ ቀዝቃዛ የሜዳ ላይ ጊዜን አሳልፏል። ከቡድኑ የማጥቃት ሂደት ተነጥለው የነበሩት ሁለቱ አጥቂዎች ጥምረታቸው የነበረው ተሳትፊነትም ብዙ የሚቀረው ሆኖ ታይቷል።

በሊጉ ሁለተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆኑት ፋሲል ከነማዎች የግብ ምንጫቸው ከተለያዩ ተጫዋቾች እና የመጫወቻ ቦታዎች እንደነበሩ በመጀመሪያው ዙር የተመለከትን ሲሆን አሁን ደግሞ የሙጂብ ቃሲም መምጣት በተከታታይ ሁለተኛ የውድድር ዘመን የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እየጣረ ለሚገኘው ቡድን ተጨማሪ ጉልበት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 የያሬድ ዳዊት አስደናቂ ክሮሶች

ወላይታ ድቻ ድሬዳዋ ከተማን 1-0 አሸንፎ በወጣበት ጨዋታ ወላይታ ድቻን በአምበልነት እየመራ ወደ ሜዳ የገባው ያሬድ ዳዊት እጅግ አስደናቂ የጨዋታ ቀንን አሳልፏል።

ያሬድ ከዚህ ቀደም በመስመር ተከላካይነት ሆነ በመስመር ተመላላሽነት ቡድኑን ሲያገለግል የቆየ ሲሆን በዚህኛው ጨዋታ ግን ይበልጥ ወደፊት ተገፍቶ በመስመር አጥቂነት ጨዋታውን ጀምሮ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ በተመላላሽነት የተሰጠውን ኃላፊነት ተወጥቷል።

በጨዋታው በተለይም የማጥቃት አቅሙ በቆሙ ኳሶች ተገድቦ ለነበረው የወላይታ ድቻ ቡድን የያሬድ አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አልነበረም። እጅግ የተመጠኑ እና ለታለመላቸው ግለሰብ የሚደርሱ አስደናቂ ኳሶችን ከቆሙ ኳሶች ሲያሻማ የነበረው ተጫዋቹ ቃልኪዳን ዘላለም ላስቆጠራት የማሸነፍያ ግብ መነሻ የነበረችውን ኳስ ወደ ሳጥን ያደረሰውም እሱ ነበር። ከዚህ ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ ልኮ ፍሬው ጌታሁንን የፈተነበት አጋጣሚን ጨምሮ በአንተነህ ጉግሳ በግንባር የተሞከሩ የድቻ ኳሶችም መነሻቸው የያሬድ እግር ነበር።

በሊጉ እስካሁን በወላይታ ድቻ መለያ በ13 ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎን ማድረግ የቻለው ያሬድ ዳዊት እስካሁኑ በሊጉም አንድ ግብን በስሙ ማስመዝገብ ችሏል።

👉 እንዳለ ደባልቄ ?

በተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን ቡናማዎቹ ቤት የደረሰው እንዳለ ደባልቄ በኢትዮጵያ ቡና አሁን ድረስ በሚፈለገው ልክ ቡድኑን እያገለገ አይገኝም። በዚህም በተደጋጋሚ ከደጋፊዎች የሚሰነዘሩ ተቃውሞዎች ማዕከል ሲሆን እየተመለከትን እንገኛለን። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም በተመሳሳይ ቡድኑ ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ በ65ኛው ደቂቃ በሚኪያስ መኮንን ተቀይሮ እስከወጣበት ደቂቃ ድረስ በተለይ በሁለተኛ አጋማሽ የተቃውሞ ድምፆችን ሲያስተናግድ ተመልክተናል።

ብዙዎች በተለይ ተጫዋቹ ሜዳ ላይ በሚሰለፍባቸው ጨዋታዎች የቡድኑ ሁነኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው አቡበከር ናስር ከዘጠኝ ቁጥርነት ይልቅ ከግራ መስመር እንዲነሳ የመገደዱ ሁኔታ ከእንዳለ አነስተኛ የሜዳ አበርክቶ ጋር ተዳምሮ ከተጫዋቹ የመጀመሪያ ተመራጭነት በተቃራኒው ሲቆሙ እንመለከታለን።

በተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን አሰልጣኝ ካሳዬ አዲስ አበባ ላይ ከተደረገ አንድ የሊግ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በሰጡት አስተያየት እንዳለን በዘጠኝ ቁጥርነት የሚጠቀሙበት መሰረታዊው ጉዳይ ተጫዋቹ ጀርባውን ለጎል ሰጥቶ በመጫወት ረገድ የተሻለ በመሆኑ እና ይህም የቡድኑን እንቅስቃሴ በማስቀጠል ረገድ ካለው ሚና አኳያ እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጧል።

በ2012 የውድድር ዘመን በተለይ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት የቡድኑን የፊት መስመር ይመራ የነበረው እንዳለ ደባልቄ በሂደት ቦታውን ለአቡበከር ናስር አስረክቦ ወደ ተጠባባቂነት ለመውረድ የተገደደ ሲሆን ከዚያ ወዲህም በቋሚነት ብዙም ተሳትፎ ሲያደርግ አልተመለከትንም ።

በዘንድሮ የውድድር ዘመን በ10 ጨዋታዎች ላይ የመሰለፍ ዕድል ማግኘት የቻለው ተጫዋቹ በ5 ጨዋታዎች ተቀይሮ የወጣ ሲሆን አንድ ጊዜ ደግሞ ተቀይሮ በመግባት ጨዋታን አደርጓል። በድምሩም 729 የጨዋታ ደቂቃ ያሳለፈ ሲሆን በዚህም በግቦች ላይ ያለው ተሳትፎ በአንድ ጎል ብቻ የተወሰነ ሆኗል።

አጠቃላይ ቁጥሮቹ የሚያሳዩት ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ቡና ያለ በቅብብሎች ተጋጣሚ ሳጥን በቁጥር በርክቶ ለመድረስ ለሚፈለግ ቡድን የዘጠኝ ቁጥር ተጫዋቹ በጎል ያለው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው። በመሆኑም ተጫዋቹም በፍጥነት የራስ መተማመኑን በማሻሻል በጎሎች ላይ ያለውን አበርክቶ ማሳደግ ካልቻለ ነገሮች በአስቸጋሪነታቸው መቀጠላቸው የሚቀር አይመስልም።