የመጨረሻው የትኩረታችን ክፍል የሚሆነው በጨዋታ ሳምንቱ የታዘብናቸው ሌሎች ትኩረት የሳቡ ጉዳዮች ይሆናሉ።
👉 የአቻ ሳምንት
16ኛ የጨዋታ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር የመጀመሪያ የአዳማ የጨዋታ ሳምንት አምስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁበት ነበሩ። ይህም በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ በርካታ አቻ የተመዘገቡበት የጨዋታ ሳምንት ያደርገዋል።
ከአቻ ውጤት መብዛት ጋር በተያያዘ የተያዩ ምክንያቶችን መጥቀስ ቢቻልም በተለይ ሁለተኛው ዙር ውድድር ቡድኖች ይበልጥ በጥንቃቄ ጨዋታቸውን ሊያደርጉ እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ የጨዋታ ሳምንት ነበር ማለት ይቻላል። በተጨማሪነት ቡድኖች በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ያስፈረሟቸውን ተጫዋቾች መጠቀም ከመጀመራቸው ጋር ተያይዞ የውህደት ችግር ምናልባት በጨዋታዎቹ ውጤት ላይ ተፅዕኖ ሳያሳድር እንዳልቀረ ይገመታል።
የአቻ ውጤቶቹ መበራከት ከእነዚህ ምክንያቶች ጋር የተያያዘ ከሆነ በቀሪ አስራ አምስት ሳምንታት ጨዋታዎች ላይም ሙሉ ሦስት ነጥብ አሳክቶ የመውጣት ክብደት በስፋት ሊታይ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው።
👉 የአዳማ ከተማ የመጫወቻ ሜዳ ጉዳይ
ለቀጣዩቹ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ሊጉን የማስተናገድ ኃላፊነቱን የተረከበችው አዳማ ውድድሮቹን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ማካሄዷን ጀምራለች።
ከሌሎች ስታዲየሞች አንፃር በመጠን አነስተኛ የሆነው ይህ ስታዲየም የመጫወቻ ሳሩ እጅግ ጥሩ የሚባል እንደሆነ በመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት የታዘብነው ጉዳይ ሲሆን ሌላው ትኩረት የሚስበው ጉዳይ የመጫወቻ ሜዳው ስፋት ጉዳይ ነው።
ለወትሮው ሊጉ ሲካሄድባቸው ከተመለከትናቸው ስታዲየሞች በመጠን አነስ የሚለው የአዳማው የመጫወቻ ሜዳ ለቡድኖች የጨዋታ ፍላጎት አንፃር ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህም እንደ ወላይታ ድቻ እና አርባምንጭ ከተማ ያሉ ሜዳውን አጥብበው ለመከላከል ለሚሹ ቡድኖች የአዳማ ከተማው ሜዳ ይበልጥ ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው የሚችል ሲሆን በተቃራኒው እንደ ኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከተማ ያሉ ቡድኖች በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሜዳውን አስፍተው መጫወት መፈለጋቸውን ተከትሎ የአዳማው ሜዳ ተግዳሮት ሊሆንባቸው ይችላል።
👉 ፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ ቁጥር ባለው ደጋፊ ታጅቦ ተመልሷል
የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ውድድር ከ28 ቀናት ዕረፍት በኋላ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጅማሮውን አድርጓል።
በአዲስ የውድድር ቅርፅ መካሄድ ከጀመረ ሁለተኛ ዓመቱ ላይ በደረሰው ውድድሩ አዳማ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊጉን የማስተናገድ ኃላፊነትን ያገኘች ሲሆን ውድድሩም በርካታ ቁጥር ባላቸው ደጋፊዎች ታጅቦ ተጀምሯል።
በተለይም አዳማ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ በስታዲየሙ በግራ ወገን ከሚገኘው ጎል በስተጀርባ በተወሰነ መልኩ ክፍት ከነበሩ የመቀመጫ ስፍራዎች ውጪ አብዛኞቹ የመቀመጫ ክፍሎች በደጋፊዎች ተሞልተው የተመለከትን ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ባደረጓቸው ጨዋታዎች እንዲሁ በቁጥር በርከት ያሉ ደጋፊዎች ጨዋታዎቹን ሲታደሙ ታይቷል።
በጨዋታ ሳምንቱ ከተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች አምስቱ በአቻ ውጤት በተጠናቀቁበት በዚሁ የጨዋታ ሳምንት ከአንድ ጨዋታ በስተቀር በሁሉም ጨዋታዎች ግቦችን የተመለከትን ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰበታ ከተማ ያደረጉት እና አራት ግቦች የተቆጠሩበት ጨዋታ በሳምንቱ በርካታ ግብ የተስተናገደበት ጨዋታ ነው።
👉 አዲሱ የቤትኪንግ መለያ
ከተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አንስቶ የሊጉን የስያሜ መብት የገዛው “ቤትኪንግ” የተሰኘው የስፖርት ውርርድ ተቋም በሊጉ ተካፋይ ለሆኑ ቡድኖች በራሱ ወጪ መለያዎችን አሰርቶ በስጦታ መልክ ለክለቦች ለማበርከት የገባው ቃል ከዚያት በኋላ ተግባራዊ ሆኖ ተመልክተናል።
ተቋሙ ከኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ውጪ በሊጉ ለሚካፈሉ 14 ቡድኖች ያሰራቸው አዳዲስ ንድፍ ያላቸው በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ የሚጠቀሙባቸው ሁለት ዓይነት የቀለም አማራጭ ያላቸው መለያዎች እንዲሁም ቦርሳዎች ከዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አንስቶ በክለቦች ጥቅም ላይ ሲውሉ ታይቷል።
ከአዲሱ መለያ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ሲያነጋግር የነበረው ጉዳይ አብዛኞቹ የሊጉ ክለቦች ከሀገር በቀሉ “ጎፈሬ” የስፖርት ትጥቅ አምራች ጋር የስፖርት ትጥቅ አቅርቦት ስምምነት የመፈፀማቸው ጉዳይ ነበር። በጉዳዩ ዙርያ ሀሳባቸውን የሰጡት የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ የቤትኪንግን አርማ በመለያው ላይ እንዲሰፍር ፍቃድ የሰጡት 14 ክለቦች በምርጫቸው የተሰራውን መለያ በ”ጎፈሬ” ከተመረተላቸው ትጥቅ ጎን ለጎን ጥቅም ላይ የሚውል ስለመሆኑ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። በመሆኑም ክለቦች ከዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አንስቶ በእንግሊዙ የትጥቅ አምራች ኩባንያ “UMBROO” የተመረቱትን መለያዎች ቁጥር እና የተጫዋቾች ስም አፅፈው መጠቀም ጨምረዋል።
ከመለያ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ውዥንብሮች የነበሩ ሲሆን ባደረግነው ማጣራት ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ከ”ጎፈሬ” ጋር ለመጪዎቹ ጥቂት አመታት የሚቆይ የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ያላቸው ሲሆን የተቀሩት ቡድኖች ደግሞ ከተቋሙ መለያዎችን ገዝተው እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ ችለናል ፤ ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ በቀረበላቸው መለያ ደስተኛ ባለመሆናቸው በ”ጎፈሬ” መለያ ሊቀጥሉ እንደሚችሉም እንዲሁ ተገንዝበናል።
በተያያዘም “ጎፈሬ” የተሰራውን መለያ መጠቀማቸውን የቀጠሉት አንዳንድ ቡድኖች ደግሞ በ”ቤትኪንግ” ከተሰራው መለያ ካሶተኒውን ነጥለው ሲቀሙም እንዲሁ አስተውለናል።
እንደ ወላይታ ድቻ ላሉ በትጥቅ እጥረት ሲሰቃዩ ለነበሩ ክለቦች መፍትሄ የሰጠው አዲሱ የ”ቤትኪንግ” መለያ በጥሩ ንድፍ እና ጥራት የተሰራ መሆኑንም እንዲሁ ታዝበናል።
👉 የመጨረሻዋ ደቂቃ ቅጣት ምት ጉዳይ
ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ቡና አንድ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ በተጨማሪ ደቂቃ የተፈጠረው ሁነት ትኩረትን የሚስብ ነበር።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ በነበረው ተጨማሪ ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች አበበ ጥላሁን ይገዙ ቦጋለ ላይ የኢትዮጵያ ቡና ሳጥን አካባቢ በሰራው ጥፋት የቅጣት ምትን ያገኛሉ። የተገኘውን የቅጣት ምት ለመምታት የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ዝግጅት ቢያደርጉም ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የመሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ቅጣት ምቱን ሳያስመቱ ጨዋታው ተጠናቋል በሚል ሂደቱን ያቋረጡበት መንገድ በጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች አንደኛው ነበር።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ያነጋገረናቸው የቀድሞ ዳኛ እንደነገሩን ከሆነ ዳኛው የጨዋታው (ተጨማሪ ደቂቃውን) ጨምሮ ተጠናቋል ብሎ በሚያንበት ጊዜ ጨዋታውን የማቋረጥ መብት በህግ የተሰጠው ስለመሆኑ እና ዳኛው ተወቃሽ የሚሆነው ባቋረጠው የጨዋታ ሂደት ሳይሆን ተገቢውን ደቂቃ ማጫወት ካልቻለ ብቻ እንደሆነም አያይዘው አስረድተውናል።
👉 ፕሪምየር ሊጉ የራሱን የቴሌቪዥን ቻናል አግኝቷል
ከተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አንስቶ ፕሪሚየር ሊጉ በዲኤስቲቪ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እያገኘ ይገኛል። አሁን ደግሞ ሊጉ የራሱ የሆነ አዲስ ቻናል አግኝቷል። ባሳለፍነው ሳምንት በይፋ የተበሰረው በዲኤስቲቪ ቻናል ቁጥር 240 ላይ የሚገኘው ልዩ የተሰኘው አዲስ ቻናል ከዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አንስቶ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ማስተላለፍ የጀመረ ሲሆን ከዚህ ባለፈ አዳዲስ የአማርኛ ይዘቶችም እንደሚኖሩት ይጠበቃል።