ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | 16ኛ ሳምንት ምርጥ 11

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መሰረት በማድረግ የሳምንቱን ምርጥ ቡድን እንዲህ አሰናድተናል።

አሰላለፍ 4-2-3-1


ግብ ጠባቂ

ሰዒድ ሀብታሙ – ወልቂጤ ከተማ

ሲልቫይን ግቦሆ በፊፋ ከተቀጣ በኋላ የሠራተኞቹን ግብ የመጠበቅ ኃላፊነት የተሰጠው ሰዒድ ለትችት የሚዳርጉት ስህተቶችን ሲሰራ የነበረ ቢሆንም በሁለተኛው ዙር ራሱን እጅግ አሻሽሎ የመጣ ይመስላል። ቡድኑ ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋራ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ሲሰነዘሩ የነበሩ ስል የግብ ማግባት አጋጣሚዎች በጥሩ ንቃት ፣ ቅልጥፍና እና ብቃት ሲያድን ስለተመለከትን የቡድናችንን በር እንዲጠብቅ አድርገነዋል።


ተከላካዮች

ብርሀኑ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

በመስመር ተመላላሽነት ሚና የሀዲያ ሆሳዕና የቀኝ መስመር ዋና የጥቃት መነሻ ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው ብርሀኑ በሁለተኛው ዙር ቀዳሚ ጨዋታም ሚናውን በአግባቡ ተወጥቷል። የግብ ዕድሎችን በመፍጠር እና ራሱም ሙከራ በማድረግ በግሉ ጥሩ የጨዋታ ቀን ያሳለፈው ብርሀኑ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ሔኖክ አዱኛ ጋር ተፎካክሮ የቦታው ተመራጭ ሆኗል።

ጊት ጋትኩት – ሲዳማ ቡና

በጊት ልክ በጨዋታ ሳምንቱ በተከላካይ ስፍራ ላይ እጅግ አሳማኝ እንቅስቃሴ ያደረገ ሌላ ተጫዋች ማግኘት ይከብዳል። እጅግ ንቁ የነበረው ተጫዋቹ አደጋ የሚጥሉ ኳሶችን በማፅዳት ፣ የኢትዮጵያ ቡናን አጥቂዎች እግር በእግር ተከትሎ በማፈን እና በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ላይ ብልጫ በመውሰድ እንዲሁም የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን እያስጀመረ አሳማኝ ብቃት አስመልክቶናል።

አዲስ ተስፋዬ – አዳማ ከተማ

ከቶማስ ስምረቱ ጋር ጥሩ የኋላ መስመር ጥምረት የፈጠረው አዲስ ከስህተት በመራቅ እና የተጋጣሚ አጥቂዎች ሳጥን ውስጥ በሚገቡባቸው ቅፅበቶች ላይ ከፍ ባለ ትኩረት እና ጥንቃቄ ጥረታቸውን በማክሸፍ የአዳማን የኋላ መስመር ጥንካሬ አስቀጥሏል። ከዚህ በተጨማሪ አዳማ ነጥብ እንዲጋራ ያደረገችው ብቸኛ ግብም የተገኘችው ከአዲስ የግንባር ኳስ ነበር።

መሀሪ መና – ሲዳማ ቡና

በሳምንቱ ጥሩ ብቃት ካሳዩ የግራ መስመር ተከላካዮች ውስጥ መሀሪ መና ከሀዋሳው መድኃኔ ብርሀኔ ጋር በመፎካከር በቦታው ምርጥ ቡድናችም ውስጥ ተካቷል። መሀሪ በማጥቃት ላይ በነበረው ተሳትፎ የኢትዮጵያ ቡናን የቀኝ ክፍል ገፍቶ እንዳይመጣ አቅም ማሳጣት ሲችል እሱም ሳጥን ድረስ በመሄድ የግብ ዕድል በሚፈጥሩ ቅብብሎች ላይ ተሳታፊ ከመሆን ባለፈ የቡድኑን ብቸኛ ግብም አስቆጥሯል።


አማካዮች

ሀይደር ሸረፋ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የሊጉ መሪ ሰበታን በረታበት ጨዋታ የአማካዩ ሀይደር ብቃት እጅግ ድንቅ ነበር። በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ የተዋጣለት ጊዜ ያሳለፈው ሀይደር በቡድኑ የቀጥተኛ አጨዋወት የነበረው ተሳትፎ ጉልህ ሆኖ አልፏል። በዋናነትም ልኬታቸው ለፍፁምነት የቀረቡ ረጃጅም ኳሶቹ ለሰበታ ተከላካዮች ፈተና ነበሩ። በዚሁ ሂደት አማኑኤል ገብረሚካኤል ላስቆጠረው ጎል ጥሩ ኳስ ከረጅም ርቀት ልኮ ቡድኑን መሪ ማድረጉም አይዘነጋም።

አማኑኤል ጎበና – አዳማ ከታማ

አማኑኤልን ከታታሪነት ነጥሎ ማየት ከባድ ነው። ከሳጥን እስከ ሳጥን ያለድካም በመንቀሳቀስ የሚታወቀው ተጫዋቹ በወልቂጤው ጨዋታም ይህንኑ ሲያደርግ ተመልክተናል። በመከላከሉ ላይ ካለው አስተዋፅኦም በላይ የአዳማን የማጥቃት ሂደት በቅብብል ከመጡ ኳሶች ብቻ ሳይሆን ራሱ ከሚያቋርጣቸው ኳሶችም በማስጀመር እና ለተጋጣሚ ሳጥን ቀርቦ በመጫወት የአማካይ ክፍሉን ሚዛን ይጠብቅ የነበረበት ሂደት ጎልቶ ታይቷል።

ወንድምአገኝ ኃይሉ – ሀዋሳ ከተማ

ወንድምአገኝ ለሀዋሳ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ተስፋ የሆነ አማካይ መሆኑን ያሳየበትን ሌላ ብቃት በዚህ ሳምንት አሳይቷል። ሀዋሳ በጅማ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰድበትም ዋነኛው የፈጠራ ምንጭ የሆነው ወንድምአገኝ ከኳስ ውጪ በታታሪነት ከመንቀሳቀስ ባለፈ ኳስ ሲያገኝም ወሳኝ ቅፅበቶች ላይ ልዩነት ፈጥሯል። በዚህም ለብሩክ በየነ ጎል መቆጠር ምክንያት የሆነች ኳስ ለአጥቂው ሲያደርስ ራሱም የህብ ሙከራዎች ያደረገባቸው ቅፅበቶች ነበሩ።

ፍሬው ሰለሞን – ሲዳማ ቡና

በጨዋታ ሳምንቱ ጎልተው ከታዩ ተጫዋቾች መካከል የአጥቂ አማካዩ ፍሬው ግንባር ቀደሙን ይይዛል። የአማካይ መስመሩን ከአጥቂ መስመሩ እንዲያገናኝ ኃላፊነት ተሰጥቶት ወደ ሜዳ የገባው ተጫዋቹ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ካሳየው የተቀዛቀዘ አቋም በተቃራኒ ግልጋሎት ሲሰጥ ነበር። ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታም ለመሐሪ ግብ የሆነ ኳስ ከማመቻቸቱ ባለፈ በተሳሳተ ውሳኔ ቢሻርበትም ግብ ለማስቆጠርም ችሎ ነበር።
በተጨማሪ ለማሸነፊያነት የሚሆኑ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥር ተመልክተነዋል።

ያሬድ ዳዊት – ወላይታ ድቻ

በሁሉም የቀኝ መስመር ቦታዎች የሚጫወተው ያሬድ ወላይታ ድቻ ድሬ ላይ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ለማግኘት የተጠቀመው የማጥቃት አጨዋወት መሠረት ነበር። በተለይ የቡድኑ ዋነኛ መሳሪያ የነበረውን የቆሙ ኳሶች በጥሩ ልኬት ለአጋሮቹ እያደረሰ ኳስ እና መረብ እንዲገናኝ ጥሯል። ጨዋታውን በቀኝ መስመር አጥቂነት ቢጀምርም በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ቀኝ ተመላላሽነት በመቀየር ጥሩ አበርክቶ ለቡድኑ ሲሰጥ ነበር። በዚህም በቅጣት ምቶቹ ዕድሎችን በመፍጠር ፣ ራሱም በመሞከር ቆይቶ የብቸኛዋ ግብ ዕድል መፍጠር ችሏል።


አጥቂ

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ በጉዳት ምክንያት አለመኖሩን ተከትሎ በሰበታው ጨዋታ የመሐል አጥቂ ሆኖ የተጫወተው አማኑኤል በቦታው ሁነኛ አማራጭ እንደሆነ አስመስክሯል። ከአጎሮ በተለየም የተጋጣሚ ተከላካዮችን ለመረበሽ ወደ ግራ እና ቀኝ እየወጣ ክፍተቶች እንዲገኙ ሲያደርግ የነበረበት መንገድም መልካም ነበር። ቡድኑን ከአቻነት ወደ መሪነት የወሰደች ጎልም ለዐይን በሚማርክ መልኩ በስሙ አስመዝግቧል።


አሰልጣኝ

ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

በሊጉ በርካታ ጨዋታዎችን ያሸነፈውን ክለብ የሚመሩት አሠልጣኝ ፀጋዬ ባሳለፍነውም ሳምንት ቤተኛ የሆነላቸውን ድል አግኝተዋል። ያላቸውን የተጫዋች ስብስብ ታሳቢ ያደረገ በሚመስል መልኩ ውጤት ተኮር አጨዋወት የሚከተሉት አሠልጣኙ ድሬዳዋን ያሸነፉበት ጨዋታ ላይ የተጋጣሚን አጨዋወት በመንተራስ የተከተሉት የአጨዋወት ስልት ውጤታማ አድርጓቸዋል። በሁለተኛውም አጋማሽ የተጋጣሚን አጨዋወት አይተው ያደረጉት የአቀራረብ ለውጥ ግብ እንዲያገኙ ከዛም ያገኙትን ግብ አስጠብቀው እንዲወጡ ረድቷቸዋል።

ተጠባባቂዎች

አላዛር ማርቆስ – ጅማ አባ ጅፋር
ቃለአብ ውብሸት ሀዲያ ሆሳዕና
ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ንጋቱ ገብረስላሴ – ወላይታ ድቻ
አብዱልከሪም ወርቁ – ወልቂጤ ከተማ
ቃልኪዳን ዘላለም – ወላይታ ድቻ
ብሩክ በየነ – ሀዋሳ ከተማ