“የምንችለውን በቁርጠኝነት እና በተቆርቋሪነት አድርገናል” አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ (ለገጣፎ ለገዳዲ)

“ረጅም ጊዜ ስላለን ቡድኑን በተሻለ ለማወቀር የሚከብደን አይመስለኝም…

“ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በጣም ያስፈልጋሉ…

“ከኪሳችን አውጥተን መሸፈን ያለብንን ከኪሳችን አውጥተን ነበር የምንሸፍነው…

የ2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲስ ስምን ይዞ ብቅ ይላል ፤ ለገጣፎ ለገዳዲ። ለገጣፎ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ስር ሲወዳደር ቆይቶ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ ዕርከን ለመወዳደር በቅቷል። በስፖርት ሥልጠና የማስተርስ ዲግሪ ባለቤት የሆነው አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ ደግሞ የክለቡ የዚህ ታሪክ አካል ሆኖ እናገኘዋለን። የአሁኑ አሰልጣኝ በክለብ ደረጃ እግርኳስን መጫወት ባይችልም ለወረዳ እና ትምህርት ቤቶች ተጫውቶ አሳልፏል። ለገጣፎን በተለያዩ ወቅቶች በረዳት አሰልጣኝነት ሲመራ የቆየ ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት አጋማሸ የአሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙን መሰናበት ተከትሎ ወደ ዋና አሰልጣኝነት መንበር መምጣት ችሏል። ኃላፊነቱን ከተረከበ በኋላም በዘንድሮው የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ለገጣፎ ለገዳዲ የምድብ ለ የበላይ በመሆን አጠናቆ ለላይኛው የሊግ ዕርከን እንዲበቃ ማድረግ ችሏል፡፡ በዚህ ስኬት መነሻነት ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኙ ጥላሁን ተሾመ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች፡፡


ክለቡን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አሳድገሀል። አንተ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት በተለያየ የኃላፊነት ቦታ አብረህ ከቡድኑ ጋር ረጅም ቆይታን አድርገሀል። ለዚህ ውጤት መምጣት የአንተ ቆይታ የረዘመ መሆኑ የሰጠው ጥቅም ይኖር ይሆን?

“በለገጣፎ ለገዳዲ ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች ከምስረታው ጀምሮ ሰርቻለሁ። ከ2011 ጀምሮ ደግሞ በምክትል አሰልጣኝነት ስሰራ ነበር፡፡ አምና 2013 መሀል ላይ ነበር የዋና አሰልጣኝነት ኃላፊነት የተሰጠኝ። ከዛ በኋላ ዋና አሰልጣኝ ሆኜ አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር ያሳለፍነው ፤ ውጤት በማጣት። ከዛ ዘንድሮ 2014 ሰፊ ዕቅድ ይዘን የሚያስፈልጉኝን ልጆች ክለቡ ውስጥ የነበሩ ነባር ልጆችንም ሰባስበን በመስራት ለማደግ በጣም ለፍተናል። ሰበታ በገባበት ሰዓት ከጫፍ ደርሰን ሁለተኛ ሆነን ጨርሰናል፡፡በማይሆኑ ነጥቦች ነበር ስንጥል የነበርነው ፤ ግን የምንችለውን በቁርጠኝነት እና በተቆርቋሪነት አድርገናል፡፡ ዘንድሮም የፋይናንስ ችግሮች ነበሩብን ፤ እነሱን ሁሉ ተቋቁመን አሁን ለውጤት ደርሰናል፡፡ጥሩ ስኬት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ይህንን ስኬት ከክለብህ ጋር ያጣጣምክበት የውድድር ዓመቱ ጉዞ በአንተ ዕይታ እንዴት ነበር ?

“ከፍተኛ ሊግ በጣም ከፍተኛ ፉክክር እና ውድድር ያለበት ነው፡፡ ያልተጠበቁ ቡድኖች ሲመሩ ነበር። ለምሳሌ ቡራዩ ዘንድሮ ነው ያደገው ፤ ለረጅም ጊዜ እስከ አንደኛው ዙር በሁለተኛው ዙርም ሲመራ ነበር ፤ ብዙ ነጥብ ሰብስቦ ከባድ ነበር፡፡ የመለማመጃ ሜዳዎች ሰበታ ላይ ብዙም የተመቻቸ አልነበረም። የእኛ ዕቅድም አላማም ስለነበረበት የልምምድ ሜዳ እስከ ሁለት ሺህ ብር ተከራይተን ስንሰራ ነበር፡፡ምክንያቱም ማድረግ የነበረብን ነገሮች ስለነበሩ የሚከፈለውን ከፍለን ተጫዋቾቻችንም የተሻለ ስብዕና ያላቸው ፣ ወጣቶች ናቸው ኮቺንግ ስታፉም ጥሩ ነው ተግባብተን በአንድነት በህብረት የሰራነው ሥራ ነው፡፡ በአጠቃላይ ስኬታማ ዓመት ነው ያሳለፍነው፡፡

አሁን ለገጣፎ ወደ ትልቁ የሊግ ዕርከን አድጓል በቀጣይ ዓመት በትልቁ ሊግ ለመታየት እና ተፎካካሪ ለመሆን ያለው አቅም እስከምን ድረስ ነው ? ያንተስ በዋና አሰልጣኝነት የመቀጠል ዕድል ?

“አንዳንድ ውሳኔዎች ያው የክለቡ ውሳኔዎች ናቸው የሚሆኑት። ገና ረጅም ጊዜ ስላለን ቡድኑን በተሻለ ለማወቀር የሚከብደን አይመስለኝም ፤ በጣም ረጅም ጊዜ አለን። አዲስ እንደ መሆናችን መጠን ከተለያዩ ክለቦች ልምድ እንወስዳለን። ልምድ ወስደን የተለያዩ ውጤታማ ሊያደርጉን የሚችሉ ግብአቶችንም ክቡር ከንቲባውም ተናግረዋል። በተለያየ አቅጣጫ የፋይናንስ ድጋፍ ለማሰባሰብ ዕቅዶች ስላለን በዛ መሰረት የሚሄድ ይሆናል ፤ ስለ እኔ ግን እዚህ ላይ ሆኜ እንዲህ ነው ማለት አልችልም፡፡

ወላይታ ድቻ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያድግ አብረውት ካደጉ ተጫዋቾች ጋር ረጅሙን ጊዜ ተጉዞ ተፎካካሪ በመሆን ነበር የቀጠለው በክለቡ ከቆየህ በዚህ መልኩ የመሄድ ዕቅዱ አለህ ? ወይንስ እንደ አዲስ ቡድኑን የማዋቀሩ ሀሳብ አለህ ?

“እጅግ በጣም የተሻሉ ልጆች አሉኝ። አሁን በእኔ ቡድን ውስጥ ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያስገቡ የተሻሉ ሆነው የጨረሱ ልጆች አሉን። እነዚህ ልጆች ደግሞ የሚቀጥሉ ሆነው ግን የልምድ እጥረቶች ነበሩብን። በከፍተኛ ሊጉ ላይ ስንጫወት ልምድ የማጣት ልጆች የማረጋጋት ችግሮች ነበሩ ፤ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በጣም ያስፈልጋሉ፡፡ስለዚህ በቀጣይ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች መቀላቀላችን አይቀርም። በሚያስፈልገን ቦታዎች ላይ ልምዳቸውን የሚያካፍሉ በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ የሚሰሩ ስራዎች ላይ ስለሚያስፈልጉ ቡድናችን ውስጥ ቢኖሩ ክፋት የለውም። አሁን ግን ቡድኑን ውጤታማ ያደረጉ ተጫዋቾች ከእኔ ጋር ይቀጥላሉ ብዬ ነው የማስበው፡፡

ዘንድሮ ክለቡ ለማደጉ የስኬቶቹ ምስጢር ምንድነው ?

“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሲፈቅድ ነው ሁሉም ነገር የሚሆነው ፤ እግዚአብሔር ረድቶኛል፡፡ ሌላው የሰበሰብኳቸው ልጆች ታማኝ እና ሀቀኛ ናቸው፤ ፍቅር ፣ አንድነት እና ህብረት አለን። ተነጋግረን ነው የምንሰራው ሁሉንም ነገር። በግልፅ ነበር የምንሰራው። ኮቺንግ ስታፎችም ከእኔ ጋር ተደማምጠን ነው ስንሰራ የነበረው። ከኪሳችን አውጥተን መሸፈን ያለብንን ከኪሳችን አውጥተን ነበር የምንሸፍነው። ይሄ የእኛ አንድነት እና ህብረታችን ደግሞ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ረድቶናል፡፡”