የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ የአሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው እና ሰበታ ከተማ የተመለከተውን ጉዳይ ሲመረምር ቆይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ክረምት ላይ አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን በሦስት ዓመት ውል በመንበሩ የሾመው ሰበታ ከተማ መጋቢት 9 በፃፈው ደብዳቤ አሠልጣኙ ቡድኑን ለቀው ወደ ክለቡ ጽህፈት ቤት መጥተው ሪፖርት እንዲያቀርቡ ካደረገ በኋላ በቃል ለጊዜው በስራ ገበታቸው እንዳይገኙ ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታወቃል። አሠልጣኙ በቃል የተነገራቸው ትዕዛዝ አግባብ ያለው አለመሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ውሳኔ እንዲሰጣቸው አቤቱታ ማቅረባቸውንም ዘግበን ነበር።
የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አመልካች ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ክለቡ መልስ እንዲሰጥ ጠይቆ የውጤት ማጣቱን ተንተርሶ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ተደርጎ የሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴዎቹ በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች በመጠመዳቸው ውሳኔ መስጥት አለመቻሉን ክለቡ ገልፆ ነበር። ክለቡ ኮሚቴው እስኪሰበሰብ እና ውሳኔው እስከሚሰጥ ድረስ የአሠልጣኙ ደሞዝ እንደሚከፈል መጠቆሙን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ቢመለከትም ከሥራ ሀላፊነታቸው በቃል ያገለላቸው መሆኑን በማረጋገጡ ምክንያት ውሳኔ ማሳለፉን የአሠልጣኙ ህጋዊ ጠበቃ አቶ ብርሃኑ በጋሻው ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀውልናል።
በውሳኔውም ሰበታ ከተማ አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን በውሉ መሠረት ወደ አሠልጣኝነት ቦታው መልሶ እንዲያሰራ ተመላክቷል። የፍትህ አካሉ ክለቡ ይህንን ውሳኔ በ7 ቀናት ውስጥ ተፈፃሚ እንዲያደርግ ነገርግን ይግባኝ የማለት መብት እንዳለውም በዛሬው ዕለት አሳውቋል።