ቅድመ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ሰበታ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የነገ ምሽቱን ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን በዳሰሳችን ቃኝተናል

ሁለቱ ቡድኖች ላለመውረድ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአስር ነጥቦች ልዩነት ኖሯቸው ሲገናኙ መከላከያ ከአካባቢው ለመራቅ ሰበታ ደግሞ ነፍስ ለመዝራት ይገናኛሉ። ከመጨረሻ አምስት ጨዋታዎቹ በአንዱ ብቻ ድል ያጣጣመው መከላከያ 11ኛ ደረጃ ላይ ይቀመጥ እንጂ የነጥብ ስብስቡ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ካሉት ክለቦች የራቀ አይደለም። የነገው ጨዋታ ከጦሩ በላይ እጅግ የሚያስፈልገው ሰበታ ከተማ ግን ከአስር በታች ነጥቦች የያዘ ብቸኛው የሊጉ ክለብ እንደሆነ ቀጥሏል።

መከላከያ በሁለቱኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ከአርባምንጭ ከተማ ነጥብ ሲጋራ በማጥቃቱ ረገድ የተቀዛቀዘ ብቃት ነበረው። አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በሰጡት አስተያየትም ጉዳዩን ከአዲስ ፈራሚዎች መዋሀድ ጋር አያይዘውታል። በእርግጥም በውድድር መሀል በሚደረጉ ዝውውሮች ቡድኖች የመዋሀድ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል። ችግሩ ግን ሦስት እና ከዛ በላይ አዲስ ተጫዋቾችን አሰላለፍ ውስጥ ለሚያካትተው ቡድን ከፍ ማለቱ አይቀርም። በእርግጥ ውድድሩ በተቀራረበ ቀናት ውስጥ መደረጉ ከነገው ጨዋታ በፊት ለመከላከያ የተለየ የውህደት ዕድልን ባይሰጠውም የፈራሚዎቹ የዚህ ቀደም ልምድ እና ጠንካራ የመከላከል መዋቅር ካለው አርባምንጭ ፍፁም ተቃራኒ የሆነው የተጋጣሚያቸው የመከላከል ብቃት ተሻሽለው እንዲቀርቡ በር ሊከፍት ይችላል።

በከባድ ጨዋታ ዙሩን የጀመሩት ሰበታዎች ዘጠነኛ ሽንፈታቸውን ሲያስተናግዱ ያልተመጣጠነ አቀራረብ ነበራቸው ማለት ይቻላል። በእርግጥ በቡድኑ ተሰላፊዎች ዘንድ የቁጭት እና ነገሮችን የማስተካከል ፍላጎት ይንፀባተቅ ነበር። በዚህም መነሻነት ከኳስ ጋር ገፍቶ በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ የመግባት ምልክትን ቢሰጥም በሽግግሮች ወቅት የነበረው ቅልጥፍና ግን ከተጫዋቾችቹ ከፍ ያለ ተነሳሽነት ጋር የተራራቀ ነበር። ወደ ማጥቃት ሲሸጋገር ዝግ ባለ የኳስ ምስረታ ሂደት ለተጋጣሚው የመደራጀት ዕድል የሚሰጥ እና ኳስ ሲነጠቅ ደግሞ ወደ መከላከል ቅርፁ ሳይመለስ ጥቃት የሚደርስበት ሰበታ የዛ ጨዋታ መልኩ ነበር። በዚህ ላይ ግለሰባዊ ስህተቶች ሲታከሉ ደግሞ ቡድኑን ይበልጥ ችግር ላይ ጥሎታል።

ከላይ የተነሱት የሰበታ ከተማ ድክመቶች ወደ ቀጥተኝነት ለቀረበው የመከላከያ አቀራረብ ምቾት ሊሰጥ ይችላል። የጦሩ የቆሙ ኳሶች አጠቃቀም ሊፈጥር ከሚችለው ልዩነት ባለፈ ከቢኒያም በላይ ጋር መስመር በሚነሱ ኳሶች የሰበታን ተከላካዮች ጀርባ የማግኘት ዕድል ይኖረዋል። መሀል ላይ ቅብብሎችን በማቋረጥም ሆነ በተከላካይ መስመሩ ጥንካሬ ደግሞ የሰበታዎችን የኳስ ፍሰት ማወክ ብዙ ላይቸግረው ይችላል። ይህንን ለመተግበር ግን ጦሩ በመጨረሻው ጨዋታ ያሳየውን የመናበብ እና እንደቡድን በተመሳሳይ ፍሰት የማጥቃት ድክመቱን ማረም የግድ ይለዋል።

ሰበታ ከተማ ለነገውም ሆነ ቀጣይ ጨዋታዎች በቅድሚያ ግለሰባዊ ስህተቶቹን መቀነስ አስፈላጊው ይሆናል። የቆሙ ኳሶችን በሚከላከልበት ወቅት የቡድኑ ስትራቴጂ እና አተገባበሩ የመስተካከል ነገሩም እጅግ አንገብጋቢ ይመስላል። ከዚህ በተረፈ ግን ኳስ መስርቶ ለመውጣት የሚያስበው ሰበታ በራሱ ሜዳ ላይ ሲቆይ ብዙ ክፍተት የማይሰጠው የነገ ተጋጣሚውን ማስከፈት ዋና ፈተናው ይሆናል። የአሰልጣኝ ብርሀኑ ደበሌ ቡድን ተጨዋቾቹ ላይ ከሚነበበው ስሜት ውጪ የሜዳውን ስፋት በግል ብዙ መጥፎ ባልሆኑ የመስማር ቱከላካዮቹ በመጠቀም በነገ ተጋጣሚው ሳጥን ዙሪያ በጠሩ ቅብብሎች የመገኘት አቅሙ ይዞ የሚወጣውን ውጤት የመወሰን አቅም ይኖረዋል። ሰበታ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ድልቅ ሆነው የሚውሉት የነዱሬሳ ሹቢሳ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ምርጥ ብቃት ላይ መሆንም ከየትኛውም ጊዜ በላይ ያስፈልገዋል።

በነገው ጨዋታ መከላከያ አምበሉ አሌክስ ተሰማን በጉዳት የሚያጣ ሲሆን አዲሱ ጊኒያዊ አጥቂ ባዳራ ናቢ ሲላን በስራ ፍቃድ ምክንያት ጨዋታው ያልፈዋል። ከዚህ ውጪ አዲሱ አቱላ እና ገናናው ረጋሳ መጠነኛ ልምምድ መጀመራቸው ተሰምቷል። ሰበታ ከተማ ግን ያለ ጉዳት እና ቅጣት ዜና ጨዋታውን ያደርጋል።

ተከተል ተሾመ ይህንን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል። የጨዋታው ረዳት ዳኞች ማዕደር ማረኝ እና እያሱ ካሳሁን ሲሆኑ ዮናስ ካሳሁን በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ከዚህ ቀደም ሁለቱ ቡድኖች የሰባት ጊዜ የግንኙነት ታሪክ አላቸው። መከላከያ 4 ጊዜ ሲያሸንፍ ሰበታ ከተማ አንድ አሸንፎ በቀሪዎቹ ሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። መከላከያ 8 ፤ ሰበታ 5 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-4-2)

ክሌመንት ቦዬ

ግሩም ሀጎስ – ኢብራሂም ሁሴን – አሚን ነስሩ – ዳዊት ማሞ

ብሩክ ሰሙ – ኢማኑኤል ላርዬ – ምንተስኖት አዳነ – ቢኒያም በላይ

እስራኤል እሸቱ – ተሾመ በላቸው

ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)

ምንተስኔት ዓሎ

ጌቱ ኃይለማርያም – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

በኃይሉ ግርማ – ቢያድግልኝ ኤሊያስ

ዱሬሳ ሹቢሳ – ሳሙኤል ሳሊሶ – ቢስማርክ አፒያ

ዴሪክ ኒስባምቢ