“ወጣት ላይ ያለኝ ዕምነት በፍፁም የሚሸረሸር አይደለም…
“እኔ ጩኸቴን የምጨርሰው ልምምድ ሜዳ ነው…
“መጨረሻ አካባቢ ፈትኖን ነበር…
ህይወቱ በሙሉ ከእግርኳስ ጋር የተቆራኘ ነው። እግርኳስን በጥልቀት ከሚረዱ ወጣት አሰልጣኞች ተርታ ይመደበል። ከተጫዋችንት ጀምሮ እስከ አሰልጣኝነት በዘለቀው ህይወቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በስፖርት ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪውን ይዟል። በወጣት የማመን እሳቤ ያለው አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ በተለያዩ ክለቦች በማሰልጠን ያለፈ ቢሆንም በ2011 ኢትዮጵያ መድንን ለማሰልጠን ተረክቦ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማስገባት ቢቃረብም በአንድ ነጥብ አንሶ ህልሙ ሳይሳካ ቀርቷል። ዘንድሮ ዳግመኛ ወደ መድን የተመለሰው አሰልጣኝ በፀሎት የክለቡ የስምንት ዓመታት ምኞት እንዲሳካ አስችሏል። ሰከር ኢትዮጵያ በመድን ቆይታው እና በሌሎች ጉዳዮች ዙርያ ከአሰልጣኙ ጋር ቆይታ አድርጋ እንደሚከተው አቅርባዋለች።
ከሦስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ መድንን ተረክበህ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማሳደግ ከጫፍ ደርሰህ ነበር ፤ ያንን ጊዜ እንዴት ታስታውሰዋለህ ?
“በመጀመርያ አመሰግናለው። ያው እንግዲህ 2011 የመድን ዋና አሰልጣኝ የመሆን ዕድል አግኝቼ ነበር ፤ በዛው ዓመት የነበረው ቡድን ታስታውሱታላቹሁ በጣም ጥሩ ቡድን ነነር። በኳስ ቁጥጥሩም በማጥቃቱ ሂደት በመከላከሉም መልካም የሚባል ሲያሸንፍ አሳማኝ በሆነ ምክንያት የሚያሸንፍ ፣ በዲሲፒሊኑም ጥሩ የሚባል ቡድን ነበር። እውነት ለመናገር የሁሉም ሰው ዕምነት መድን በዚህ ዓመት ይገባል የሚል ነበር። ግን በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ የሚባለው የውድድሩ ፎርማት በተለይ ከሜዳ ውጪ በነበሩ ጨዋታዎች ላይ እግርኳሳዊ ያልሆኑ አስቸጋሪ ነገሮች ይፈጠሩ ስለነበረ ተፅዕኖው ቀላል አልነበረም። ያኔ ተበላሽቶብናል ፤ አልተሳካልንም። በመጨረሻም በአንድ ነጥብ ልዩነት ሳናልፍ ቀርተናል። በወቅቱ የነበረው ጥንካሬ ይመስለኛል በመድን ቤት በድጋሚ ተመልሼ እንድሰራ ከሁለት በኋላ ዕድል እንዳገኝ የረዳኝ። ዘንድሮም ጠንካራ ጥሩ ኳስ የሚጫወት በዲሲፒሊንም የተሻለ ቡድን ለመገንባት ጥረት አድርገናል። ምን አልባት ከዛኛው ውድድር የዘንድሮው የሚለየው በአንድ ቦታ መቀመጫህን አድርገህ በአብዛኛው የአንተን ብቃት ተፅእኖ ያሚያሳይ ውድድር መሆኑ ነው። በጥሩ ሁኔታ አጠናቀን ዕቅዳችንን አሳክተናል።
በአሰልጣኝነት ዘመን ከፍም ብለህ ዝቅም ብለህ ሰርተሀል ኢትዮጵያ መድንን ለፕሪሚየር ሊጉ ለማቅረብ ጫፍ ያደረስክበት እና ያልተሳካበት ጊዜን ስታስበው ትቆጫለህ ?
“በትክክል በጣም የምቆጭበት ነው። በእግርኳስ ማሸነፍ መሸነፍ ሌሎች ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ሆኖም በ2011 ቡድን በጣም ጠንካራ አሳማኝ ቡድን ስለነበረ ከረጅም ዓመት በኋላ መድንን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንዲመለስ የነበረው ጉጉት የክለቡ ቦርድ ፍላጎት እኔም የዛ ታሪክ አካል ለመሆን ከፍተኛ ተነሳሽነት ነበርኝ ፤ ያው ይህ መሆን ባለመቻሉ በጣም ይቆጨኝ ነበር። አሁን ደግሞ ያንን ዕድል አግኝቼ በመሳካቱ በጣም ደስተኛ ነኝ።
ዳግም ከሦስት ዓመት በኋላ ቡድኑን ስትረከብ በውል ስምምነትህ ውስጥ መድንን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እመልሰዋለው ብለህ ተስማምተህ ነበር ?
“አዎ በትክክል ፤ ስምምነት ውስጥ አለ። ምክንያቱም መድን ጋር ስትመጣ አንድ ነገር ላይ ብቻ ነው የምትዋዋለው። የክለቡ የበላይ አካሎች ፕሪሚየር ሊግ መግባት ዋና ዓላማቸው ነው። ክለቡ የሚመጥነው ቦታ መቀመጥ እንዳለበት ይታመናል። ስለዚህ ውሉ ላይ ምንም የተለየ ነገር የለም ማሰሪያው ዓመቱ መጨረሻ ላይ መድንን ፕሪሚየር ሊግ ማስገባት የሚል አለው። ያው በስምምነታችን መሠረት ዕቅዱን አሳክተናል።
አሰልጣኝ በፀሎት ያለፉትን አራት ዓመታት በተለያዩ ክለቦች ስታሰለጥን አብረውህ የሚጓዙ ተጫዋቾች አሉ ይህ ከምን ዕሳቤ ነው ?
“ትልቁ ነገር ምን መሰላቹሁ የጨዋታ እሳቤ (ፍልስፍና) ነው የሚያስገድደኝ። ይህ ማለት አንተ በምትፈልገው ደረጃ እና ለምትጫወተው የአጨዋወት ዘይቤ የምትፈልገውን ስታስብ የመጀመርያ ምርጫህ ተጫዋች ነው። ከዛ አንፃር ነው የሚሳሙኝን ፣ በምፈልገው ደረጃ የሚጫወቱልኝ ልጆች ነው የምመርጠው ይህ ደግሞ ሥራህን ያቀልልሀል። ለዚህም ነው አንዳንድ ልጆችን በሄድኩበት ይዤ የምሄደው። ሌላ የተለየ ነገር የለውም። የመጀመርያውም የመጨረሻውም ከጨዋታዬ ዘይቤ ጋር ስለሚሄዱ ከዚህ ከየተነሳ ነው ተጫዋች የምመርጠው።
ብዙ ጊዜ ከተስፋ ቡድን ጥሩ አቅም ኖሯቸው ወደ ዋናው ቡድን የማደግ ፣ የመጫወት ዕድል ያላገኙ ወጣቶችን በቡድንህ ውስጥ በርከት አድርገህ በመሰብሰብ ትታወቃለህ። ይህ በወጣት የማመን ሀሳብህ ከምን የመነጨ ነው ?
“ይህ የአመለካከት ጉዳይ ነው ። የኔ አመለካከት ከሌላ ሰው ተለይቷል ብዬ አላስብም። ነገር ግን ወጣት ላይ ዕምነት አለኝ። ልምድ ባላቸው አላምንም ለማለት ሳይሆን ወጣት ተጫዋቾች ዕድል ከተሰጣቸው መስራት ይችላሉ ብዬ ስለማምን ነው። ወጣት ሲባል ደግሞ ዝም ብሎ ወጣት ሳይሆን አቅም ያላቸውን መያዝ እፈልጋለው። በወጣት አምናለው ስለዚህ ከየትኛውም ሊግ ይሁን ወጣቶችን የማየት ዕድል መስጠት እፈልጋለው። ከምንም በላይ እነርሱ ሰርተው ተሻሽለው ትልቅ ደረጃ ሲደርሱ ማየት በጣም ስለሚያረካኝ እና ስለሚያስደስተኝ የዛ ፍላጎት ይመስለኛል ብዙ ጊዜ እነርሱ ላይ ትኩረት አድርጌ የምሰራው ፤ እነርሱም አያሳፍሩኝም ውጤታማ አድርገውኛል።
በጨዋታ ወቅት ብዙ ከማያወሩ ለተጫዋቾች ነፃነት ከሚሰጡ አሰልጣኞች መካከል ትመደባለህ ይህ እንዴት ታያዋለህ ?
“እንግዲህ እኔ ጩኸቴን የምጨርሰው ልምምድ ሜዳ ነው። እውነት ለመናገር ልምምድ ሜዳ በጣም ነው የምጮኸው ሁሉም ነገር ማለቅ ያለበት ልምምድ ሜዳ ነው ብዬ አምናለው። በጨዋታ ወቅት በራስ መተማመናቸውን ላለማሳጣት በራስ መተማመናቸው እንዲዳብር ነፃነት እሰጣለው። የኔ ትኩረት በአንዳንድ ነገሮች ክፍተቶችን ካሉ እዛ ላይ የመሙላት ሥራ ነው የምሰራው ከዛ ውጭ መጮህ መቆጣት የተለየ ነገር ማሳየት አልፈልግም።
ጥያቄዎቼን ወደ ቡድንህ እንቅስቃሴ ልመለስ እና መድን ወደ መጨረሻው አካባቢ ለምን በሚታወቅበት አጨዋወት መጨረስ አልቻለም? የተጫዋች ለውጦች በዝተው ነበር ?
“አንደኛው በጣም ድካም ነበር። ወደ መጨረሻው አካባቢ ጉዳቶችን በብዛት እያስተናገድን ነበር። ሁለተኛው ዙር ላይ ተሻሽሎ የዕረፍት ቀን ተጨመረ እንጂ የመጀመርያው ዙር በጣም አድካሚ ነበር። በዚህ ምክንያት ልጆች ድካም እየተሰማቸው ነበር። ሌላው ከሥነ ልቦናው አንፃር ወደ ሊጉ ለመግባት እየተቃረብክ ስትመጣ ጉጉት መኖሩ እንደገና በጣም ወጣት ከመሆናቸው አንፃር ያላውን ጫና ለመቋቋም ተቸግረው ነበር። በዚህ የተነሳ መጨረሻ አካባቢ ፈትኖን ነበር። የተጫዋችም ለውጥ የበዛው ከዚህ መነሻነት ነው።
የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ላይ የተፈጠረው ነገር ምንድነው ?
“በጣም የሚገርመው ከመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በፊት በነበሩ ጨዋታዎች ጎል አልተቆጠረብንም። እስከ ሰባተኛው ሳምንት ድረስ አንድ ጎል ነው ከቆመ ኳስ የገባብን ከዛ ውጪ አልተሸነፍንም ነበር። ስምንተኛው ጨዋታ የምናረጋግጥበት ነው። እንደገና በአንፃራዊነት የምንገጥመው ቡድን ወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኝ ነው ፤ የሰጠነው ግምት ይመስለኛል። በተጨማሪም ጨዋታው ጠዋት መሆኑ አልፎ ተርፎም ከመጓጓት እንቅልፍ አለመተኛት ፣ ከሥነ ልቦናው ጋር ተያይዞ ጫናን ያለመቋቋም በአጠቃላይ ቡድኔ ወርዶብኝ ነበር። በተሰሩ ስህተቶች ሁለት ጎል ገባብን ይህን መቀልበስ የምንችልበትን በተደጋጋሚ ጎል ማስቆጠር የምንችልበትን አጋጣሚ ሳንጠቀም ቀርተናል። ቀጣይ የመጨረሻ ጨዋታ አሁንም ዕድሉ በእጃችን ስለነበር ሳምንቱን ትኩረት ያደረግነው በዋናነት ሥነ ልቦናው ላይ ነው። ልጆቹም በጨዋታው የሚችሉትን ነገር አደረጉ ፤ ጎሉን ካስቆጠርን በኋላ ግን ተመልሰው በራስ መተማመን ከመጫወት ይልቅ ያንን ለማስጠበቅ አስበው በማፈግፈጋቸው የተወሰነ ፈተናዎች ነበሩ። ይመስለኛል ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት በነበረው ጨዋታ መሸነፋችን በራሱ ተፅእኖ ነበረው። የሚገርመው እስከዛ ጨዋታ ድረስ ሁለት አገባን ሦስት የሚያጠቃ ቡድን እንጂ የሚከላከል ቡድን አልነበረም። ያው ይሄ ተፈጠረ ውጤቱን ይዘን ልንወጣ ችለናል።
ኢትዮጵያ መድንን ከስምንት ዓመት በኋላ ዳግም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መመለስህ በአሰልጣኝ ዘመንህ ትልቅ ስኬት ነው ማለት ይቻላል ?
“በትክክል በመጀመርያ ኢትዮጵያ መድን ትልቅ ክለብ ነው። የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ ከመሰረቱ ክለቦች አንዱ ነው። በአፍሪካ ኮፌዴሬሽን ካፕ ተሳትፎው ታሪካዊ ክለብ ነው። ትልልቅ ስመጥር የሆኑ ተጫዋቾችን ያፈራ ለብሔራዊ ቡድን ያስመረጠ አንጋፋ ክለብ ነው። በታዳጊ ወጣቶች ላይ የሚሰራ ከዚህ በተጨማሪ በተመረጡ አቅም ባላቸው ከተሞች ላይ ፕሮጀክት ለማቋቋም እንደ ሀገር ሰፊ ሥራ እየሰራ ያለ ቡድን ነው። የዚህን ታሪካዊ ክለብ ህልም ማሳካት እና ዳግም ከስምንት ዓመት በኋላ ወደ ሚመጥነው ሊግ እንዲመለስ ማድረግ የሚፈጥርብህ ስሜት ቀላል አይደለም። ስለዚህ ወደሚመጥነው ሊግ እንዲመለስ በማድረግ የዚህ ታሪክ አካል በመሆኔ በጣም ደስ ብሎኛል።
ያለፉትን አራት ዓመታት በአንድ ክለብ ከአንድ ዓመት ያልበለጠ ቆይታ ነበርህ ። በቀጣይ ቆይታህ እንዴት ነው ?
“ክለብ የመቀያየሩ ጉዳይ የኔ ጉዳይ አይደለም። እንደሚታወቀው አብዛኛው በዚህ ሀገር የሚሰጠው የኮንትራት ዘመን አነስተኛ ነው። ቅድም እንደተባለው ያለፉት አምስት ዓመታት የተሰጠኝ ኮንትራት ለአንድ ዓመት ብቻ ነው። አሁን ግን ከመድን ጋር ያለፈው ታሪክ ተቀይሮ በቀጣይ አብሬ ነው የምቆየው ፤ ስለዚህ ያነገር አይኖርም ብዬ ነው የማስበው።
በቀጣይ በፕሪምየር ሊጉ በወጣት የማመን እሳቤህ ይቀጥላል ?
“በትክክል ! በወጣት የማመኔ ነገር ከውስጤ የሚወጣ አይደለም ፤ በቀጣይም ይቀጥላል። የማስተካከል ሥራዎች እንሰራለን። ለምሳሌ ያሉብን ክፍተት ባሉበት ቦታዎች ላይ የማደራጀት ሥራ ይሰራል። የውድድሩ ደረጃ ከፍ ከማለቱ አንፃር እንጂ አሁንም ወጣት ላይ ያለኝ እምነት በፍፁም የሚሸረሸር አይደለም።
ለስኬትህ የምታመሰግናቸው አካላት ካሉ…
“በመጀመርያ ስኬቴ እዚህ ለመድረሴ በነገር ሁሉ የረዳኝን የረዳኝን ፈጣሪ አመሰግናለው። በመቀጠል በእኔ የአሰልጣኝ ነት ህይወቴ ውስጥ ኮርስ በመሰጠት፣ በማሰልጠን ያላቸውን ልምድ በማካፈል የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ ብዙ ሰዎች አሉ እነርሱን አመሰግናለው። ተጫዋቾቼ እንደ አሰልጣኝ ብቻ ሳይሆን በጥሩ መከባበር በዲሲፒሊን ለኔ ያላቸው ነገር በጣም ጥሩ ነው እነርሱን አመሰግናለው። የአሰልጣኝ ቡድን አባላቶቼ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። አካባቢውን ነፃ ለሥራ ምቹ እንዲሆን በማድረግ እኔን በመደገፍ ምክትሌ ሀሰን በሽር ፣ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ አንተነህ በዙርያዬ ያሉ አባላትን አመሰግናለው። ከዚህ በተጨማሪ የቦርድ አባላት ከኋላችን በመሆን ውድድሩን በመከታተል ትልቅ ድጋፍ አድርገውልናል ፤ እነርሱን በጣም ማመስገን እፈልጋለው።”