“ዝቅ ከማለት ነው ከፍታ የሚገኘው” ቢንያም ካሳሁን
“ሁለም በፍቅር በመከባበር የሚሰራ በመሆኑ ውጤታማ አድርጎናል” ያሬድ ዳርዛ
ቢኒያም ካሳሁን ይባላል ፤ ትውልዱ ዳንግላ ከተማ ነው። በክልል ፕሮጀክት ውድድር ወቅት ባሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ከ17 ዓመት በታች አሰልጣኝ ታዲዮስ መልማይነት ኢትዮጵያ ቡናን በመቀላቀል እስከ ተስፋ ቡድን መጫወት ችሏል። ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ቢችልም በኋላ ላይ ተቀንሶ በአንደኛ ሊግ ለዳንግላ ከተማ ለስድስት ወር ተጫውቶ ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ቢያጋጥሙትም አሰልጣኝ በፀሎት ወደ ገላን ከተማ አምጥቶት ለአንድ ዓመት አብሮት ከሰራ በኋላ ዘንድሮ በመድን ቤት ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል።
ሌላኛው ባለ አስተዋፆኦ አጥቂው ያሬድ ዳርዛ ይባላል ፤ ትውልዱም የእግርኳስ ጅማሬውም ወላይታ ነው። ሀዋሳ ላይ በተካሄደው የፕሮጀክት ውድድር ወላይታን በመወከል ተጫውቷል። በማስከተል በአንደኛ ሊግ ተሳትፎ ካደረገው ወላይታ ሶዶ ጋር ኮከብ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ቡድኑን ወደ ከፍተኛ ሊግ ማሳደግ ችሏል። በ2012 አርባምንጭ ከተማን በመቀላለቀል ለአንድ ዓመት ቆይታ አድርጎ ወደ ኢኮስኮ ፣ ወላይታ ድቻ ፣ ወልድያ አቅንቶ ዘንድሮ ደግሞ ኢትዮጵያ መድንን በመቀላቀል የምድቡ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ጥሩ የውድድር ዓመት አሳልፏል።
ሶከር ኢትዮጵያም ሁለቱን ወጣት ተጫዋቾች ጋር ያደረገችውን ቆይታ እንደሚከተለው አሰናድታዋለች።
ቢንያም ካሳሁን…
የውድድር ዘመኑ ምን ይመስል ነበር?
“ከዝግጅት ጀምሮ መድንን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማስገባት ላይ ነበር ትኩረት አድርገን ስንሰራ የቆየነው። ከሞላ ጎደል በአሰልጣኛችን የሚሰጠንን ልምምዶች ጨምሮ መድንን ወደ ሊጉ ለመመለስ በጣም ለፍተን ነበር። ፈጣሪም ረድቶን መጨረሻ ላይ ክለቡ ለዓመታት ሲመኘው የቆየውን ህልም አሳክተን ውጤታማ ሆነን አጠናቀናል።
በከፍተኛ ሊግ ውድድር ብዙ ጊዜ ከተስፋ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን የማደግ ዕድል ያላገኙ ወጣቶች እየታዩበት ነው። የከፍተኛ ሊግ ውድድር አቅምህን እንድታሳይ ረድቷሀል ?
“ከፍተኛ ሊግ በጣም ጠንካራ ውድድር ነው ፤ ብዙ ወጣቶች ይበዙበታል። ፉክክሩም ቀላል አይደለም። ይህ ደግሞ ራስህን እንድታሳይ አቅምህን አውጥተህ በተሻለ ደረጃ ለመቅረብ ያግዝሀል። እኔንም በዚህ በኩል በከፍተኛ ሊግ ሁለት ዓመት መጫወቴ ራሴን እንዳሳይ ረድቶኛል ብዬ አስባለው።
ከኢትዮጵያ ቡና የወጣሁት በምን መንገድ ነው ብለህ ታስባለህ ?
“ከኢትዮጵያ ቡና የወጣሁት ያው በወቅቱ የመጣው አሰልጣኝ እኔን ብዙ አያቀኝም ነበር። ምክንያቱም እርሱ ሌላ ቦታ በነበረበት ወቅት ነው እኔ ኢትዮጵያ ቡና የነበርኩት በዚህ መሀል በተፈጠረ ክፍተት እንጂ ሌላ ነገር አይደለም።
ከኢትዮጵያ ቡና ከቀቅክ በኋላ መልሶ ለማንሰራራትና እንድትሻሻል የረዳህ… የቡድኑ አጨዋወት ፣ አሰልጣኝ ወይስ ሌላ ምክንያት ?
“በመጀመርያ ደረጃ ከኢትዮጵያ ቡና ከወጣሁ በኋላ ወደ ዳንግላ ከተማ በማምራት በአንደኛ ሊግ ለስድስት ወር ስጫወት ቆይቻለው። ዳንግላ ወደታች ወርዶ ብዙ ተስፋ ቆርጬ ባለሁበት ሁኔታ ነው አሰልጣኝ በፀሎት ወደ ገላን ይዞኝ የመጣው። የነበረኝን የጨዋታ መንገድ በብዙ መንገድ እንድሻሻል የረዳኝ እርሱ ነው። ለብዙዎቻችን ተጫዋቾች የእርሱ የጨዋታ መንገድ ያለንን አቅም እንድናወጣ በራስ መተማመናችንን ጨምሮ በነፃነት እንድንጫወት በጣም አግዞናል።
ከተስፋ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ካደጉ በኋላ ሲቀነሱ ተስፋ የሚቆርጡ አሉ በዚህ መልኩ ምን መልዕክት አለህ ?
“ወጣትነት ፈተና ነው። ለወጣት ዕድል የሚሰጡ አሰልጣኞች መብዛት አለባቸው። ገና ጀማሪ ነን ፤ ብዙ የሚቀረን ነገር ቢኖርም በወጣት ማመን ያስፈልጋል። አንዳንዴ በእግርኳስ መውጣት በመውረድ ይኖራል። እኔ ቅድም እንዳልኩህ ብዙ ተስፋ ቆርጬ ነበር። ግን አሰልጣኝ በፀሎት የእግርኳስን መጀመርያ አስተምሮኝ በብዙ ነገር ለውጦኝ እዚህ ደርሰናል። ስለዚህ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም ሁሌም ጥረት ከተደረገ የተሻለ ደረጃ ይደረሳል። በዚህ አጋጣሚ ለአሰልጣኝ በፀሎት ትልቅ ምስጋና አለኝ።
በቀጣይ በፕሪሚየር ሊጉ ራስህን ለማሳየት በምን መልኩ መዘጋጀትን ታስባለህ ?
“በእግርኳሱ በጣም ገና ብዙ ከሚቀራቸው ዳዴ ከሚሉት ጀማሪ ህፃን ልጅጆች ውስጥ ነኝ። ብዙ መማር ማወቅ መስራት ያለብን ነገሮች አሉ። ይህን ደግሞ ከታላላቆቻችን ራሳችንን ዝቅ አድርገን መስራት ይገባል። ዝቅ ከማለት ነው ከፍታ የሚገኘው። ሁል ጊዜም ብዙ ነገር ይቀረኛል በማለት ራስን በማሳመን አሰልጣኞችን በመታዘዝ ራስን በመጠበቅ ጠንክሮ መስራት አለብን። ሁልጊዜ አሰልጣኛችን መወዳደር ያለባቹሁ ከራሳቹሁ ጋር ነው እያለ ይነግረናል። ውድድሩን ከራሴ ጋር አድርጌ ካባለፈው ማንነቴ ራሴን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ነው ሁልጊዜ የምሰራው።”
ያሬድ ዳርዛ…
መድን ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲመለስ ማስቻላችሁ የስኬቱ ምድነው ትላለህ ?
“በመጀመርያ ፈጣሪ ነው የረዳን። በማስከተል ህብረታችን አንድነታችን ነው። ቋሚም ሆነ ተቀያሪ የሚያኮርፍ የለም ፤ ሁለም በፍቅር በመከባበር የሚሰራ በመሆኑ ውጤታማ አድርጎናል።
በግልህ ስምንት ጎሎችን አስቆጥረህ ጥሩ ዓመት አሳልፈሀል። በሌሎች የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ያልተሳካልህን ዘንድሮ እንደ አዲስ አንሰራርተህ ልትታይ የቻልከው በምንድን ነው ?
“ጎልቼ እንድወጣ የቡድኑ አጨዋወት እገዛ አድርጎልኛል። እኔም በግሌ ጠንክሬ ሰርቼ ነበር። በዛ ነው ራሴን ቀይሬ የመጣሁት። አርባምንጭ ያልተሳካልኝ እንደሄድኩ ጉዳት አጋጠመኝ በዚህም እንደተፈለገው መሆን አልቻልኩም። ኢኮስኮ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ ኮቪድ መጥቶ ውድድሩ ተቋረጠ እንጂ ጥሩ ነገር እያደረኩ ነበር። ወላይታ ድቻ እንደመጣው ከሲዳማ ቡና ጋር በነበረ የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ተጎድቼ አንድ ሁለት ወር ቁጭ አልኩኝ። ከጉዳቴ ስመለስ አሰልጣኝ ተቀየረ እኔም እንድቆይ አልተፈለገም ፤ አቅሜን ለማሳየት ሳልችል ወጣው። ዘንድሮ አሰልጣኝ በፀሎት እየመከረኝ በራሴ ላይ መሻሻል በማሳየት ጥሩ የውድድር ዓመትን አሳልፌያለሁ።
ጎሎችን በማስቆጠር ያለህ ጥንካሬ እንዳለ ሆኖ ከአጨራረስ ውስንነት የተነሳ የማትጠቀምባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ታዝበናል ይህ ምክንያቱ ምንድነው ? በቀጣይስ ይህንን ክፍተት ለማሻሻል ምን ታስባለህ ?
“እውነት ነው ማስተካከል ያለብኝ ነገር ነው። ይህ የሆነው ግን ቡድኔን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለማሳደግ ካለኝ ጉጉት የመጣ ነው። ብዙ ጊዜ ጎል ከእኔ የሚጠበቅ በመሆኑ ነው። ሌላው የጎል መጠኔን ከፍ አድርጌ ለማሳደግ ማሰቤ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሊፈጠሩ ችለዋል። በቀጣይ ዓመት ራሴን አሻሽዬ በደንብ ሰርቼ እመጣለው ብዬ አስባለው።”