በቀድሞ የግብ ዘቡ ዳንኤል አጄይ በቀረበበት ክስ በፊፋ እግድ ተላልፎበት የነበረው ሰበታ ከተማ በመጨረሻም ዕግዱ ተነስቶለታል።
በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጪ ባሉ ነገሮች አሉታዊ ዜናዎች የበረከቱበት ሰበታ ከተማ የቀድሞ ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄይ ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ክስ አቅርቦበት በእግር ኳሱ የበላይ አካል ፊፋ የዕግድ ውሳኔ ተላልፎበት እንደነበር አይዘነጋም። 2010 ላይ ጀማ አባ ጅፋርን በመቀላቀል የኢትዮጵያን እግር ኳስ የተዋወቀው ጋናዊው ግብ ጠባቂ በመጣበት ዓመት የሊጉን ዋንጫ ከቡድኑ ጋር በግሉ ደግሞ የኮከብ ግብ ጠባቂነት ክብርን አግኝቶ ነበር። ሁለት ዓመታትን ለጅማ ግልጋሎት ሰጥቶ በኮቪድ-19 በተሰረዘው የውድድር ዓመት (2012) ወደ ሰበታ ከተማ ያመራው ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር ከተለያየ በኋላ ዓምና ግማሽ ዓመት ወደ ድቻ ቤት ጎራ ብሎ እንደነበር አይዘነጋም።
ተጫዋቹ ከሰበታ ከተማ ጋር ከተለያየ በኋላ የደሞዝ ጥያቄዎቹን ሲያቀርብ የነበረ ሲሆን ለእግርኳስ የበላይ አካል ባቀረበው ክስም ሰበታ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ ዝውውር እንዳያከናውን ታግዶ ነበር። ክለቡ ያለፉትን ሳምንታት ተጫዋቹ የጠየቀውን ጥያቄ ከመለሰ በኋላም በትናንትናው ዕለት ፊፋ ዕግዱን ማንሳቱን በላከው ደብዳቤ ማስታወቁን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ምንዳ ነግረውናል።
ፊፋ ዕግዱን ሙሉ ለሙሉ ከማንሳቱ በፊት ቢስማክ አፒያን ጨምሮ ሌሎች ተጫዋቾችን እንዴት ሊያስፈርም ቻሉ ብለን ለጠየቅነው ጥያቄ ደግሞ የክፍያ ሂደቱ ቀድሞ በመጀመሩ እና መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት ሂደቱ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መገኘቱን ተከትሎ ዝውውሩ እንደተመዘገበ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምላሽ አግኝተናል።