የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት ጎሎችን በማስቆጠር ኢትዮጵያ ቡናን ረምርሟል።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር አንድ ለአንድ የተለያዩት ቡናማዎቹ 2 ነጥብ ከጣሉበት ጨዋታ አምስት ለውጦችን በጉዳት እና በተለያዩ ምክንያቶች አድርገዋል። በዚህም ወንድሜነህ ደረጄ በገዛኸኝ ደሳለኝ፣ ኃይሌ ገብረትንሣኤ በሥዩም ተስፋዬ፣ አቤል እንዳለ በሚኪያስ መኮንን፣ ዊልያም ሰለሞን በታፈሠ ሰለሞን እንዲሁም እንዳለ ደባልቄ በተመስገን ገብረኪዳን ተተክተው ጨዋታውን ቀርበዋል። ሰበታ ከተማን ሦስት ለአንድ ረተው ለዛሬው ጨዋታ የተዘጋጁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው በግብ ብረቶቹ መሐል ቻርለስ ሉክዋጎን በባህሩ ነጋሽ እንዲሁም በግራ ተከላካይ ቦታ ሱሌይማን ሀሚድን በያሬድ ሀሰን ምትክ አሰልፈው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
በደማቅ የደጋፊዎች ድባብ ሞቅ ብሎ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና በጊዜ ከፍተኛ ፉክክር ማስተናገድ ይዟል። አንድ ደቂቃ በቅቱ ሳይሆንም አቡበከር ናስር ከመሐል ሜዳ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ሳይቆጣጠር የቀረውን ኳስ አግኝቶ በቀጥታ ወደ ግብ ልኮ የመጀመሪያ ሙከራ ሰንዝሯል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሌላ የተጫዋች ስህተት ተፈጥሮ እጅግ ግልፅ የግብ ዕድል ተገኝቶ መክኗል። በዚህም የአብስራ ተስፋዬ ሥዩም ተስፋዬን ተጭኖ የተቀበለውን ኳስ መረብ ላይ አሳረፈው ተብሎ ቢጠበቅም በአስቆጪ ሁኔታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ብዙዎች ከጨዋታው አስቀድሞ እንደገመቱት ኢትዮጵያ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ በፈጣን አጨዋወት የቡናን የኳስ ፍሰት በማጨናገፍ የግብ ዕድሎችን ለማግኘት ሲጥሩ ተመልክተናል። በ34ኛው ደቂቃም በጠቀስነው መንገድ የአብስራ አማኑኤል ላይ ጫና በማሳደር የተረከበውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ራሱን ነፃ አድርጎ ለቆመው ሀይደር ሰጥቶት አምበሉ የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሰንዝሯል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ዳግም የቡናማዎቹን የግብ ክልል ለመጎብኘት ያመሩት ፈረሰኞቹ ጎል አግኝተው መሪ ሆነዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ቸርነት ጉግሳ ከቀኝ መስመር በሩቁ ቋሚ ያሻገረውን ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል ተቆጣጥሮ መሬት ለመሬት ወደ መሐል ሲልከው አቤል ያለው በድንቅ ሁኔታ ኳሱን ይዞ በመዞር በሞክሼው (አቤል ማሞ) መረብ ላይ አሳርፎታል። አጋማሹም በቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ለምንም መሪነት ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ መሪዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተለመደ ድንቅ አጀማመራቸውን አድርገው ሁለተኛ ግብ አግኝተዋል። የመሐል ተከላካዩ አበበ ጥላሁን ያስረዘመውን ኳስ የአብስራ ከነጠቀ በኋላ የደረሰው ሀይደር ጥሩ ኳስ ለቸርነት አቀብሎት ቸርነት ኳሱን ከግብ ጠባቂው በላይ በመላክ ግብ አድርጓታል። ጨዋታው ከቁጥጥራቸው ውጪ እየሆነባቸው የመጣው የአሠልጣኝ ካሣዬ ተጫዋቾች ሁለተኛ ግብ ካስተናገዱ በኋላ ኳሱን በሚገባ መቆጣጠር ቢችሉም አንድም የሰላ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ መንቀሳቀስ ቀጥለዋል። ይባስ በ57ኛው ደቂቃ አማኑኤል በግራ መስመር በፈጠረው ሌላ አጋጣሚ ሦስተኛ ግብ ሊያስተናግዱ ተቃርበው ነበር።
የሚፈልጉት ያገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሁለተኛው ጎል በኋላ የማጥቃት ሀይላቸውን ጋብ አድርገው ጨዋታውን መቆጣጠር ላይ ትኩረት ሰጥተው ተጫውተዋል። በዚህም አዲስ ጉልበት ቀይረው በማስገባት ከኳስ ውጪ ያላቸውን መታተር ጨምረዋል። ኢትዮጵያ ቡናዎች በተቃራነው ባለው ደቂቃ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ውጥን በመያዝ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ቢያስገቡም አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ እንኳን ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊገባደድ ስምንት ደቂቃዎች ሲቀሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ የመዓዘን ምት አግኝቶ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። የመዓዘን ምቱን ሔኖክ አዱኛ ሲያሻማው ፍሪምፖንግ ሜንሱ በግንባሩ ከመረብ ጋር አዋህዶታል። ጨዋታው በሦስቱ ግቦች ተጠናቀቀ ተብሎ ቢጠበቅም አዲስ ግዳይ ራሱ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምራ ራሱ አዲስ የማሳረጊያው ጎል አድርጎታል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሉን ተከትሎ የሊጉን መሪነት በ37 ነጥቦች ሲያጠናክር ሦስት ነጥብ ያስረከበው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 21 ነጥብ ቢኖረውም የግብ ዕዳ በመጨመሩ ከደረጃ አጋማሹ ቦታ ወደ ዘጠነኛ ደረጃ ሸርተት ብለዋል።