ሪፖርት | ሰበታ ከተማ በመጨረሻም ነጥቡን ሁለት አሀዝ አድርሷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በዕለቱ ሁለተኛ በነበረው ጨዋታ የሊጉ ግርጌ ላይ ሆነው መከላከያን የገጠሙት ሰበታ ከተማዎች በ87ኛው ደቂቃ ዴሪክ ንሲምባቢ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ድል በማስመዝገብ ከሊጉ ግርጌ ለጊዜውም ቢሆን ተላቀዋል።

መከላከያዎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ያለ ግብ በአቻ ውጤት ጨዋታውን ያጠናቀቀውን ስብስብ በዛሬው ጨዋታም ሲጠቀሙ በአንፃሩ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ የተሸነፉት ሰበታ ከተማዎች ደግሞ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ በጨዋታው የትኩረት ማዕከል የነበረውን ሰለሞን ደምሴን አስወጥተው በምትኩ ምንተስኖት አሎን በመጠቀም ጨዋታውን አድርገዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ሁለት አጥቂዎችን ከፊት በመጠቀም ኳሶች ወደ መስመር በማውጣት እና ከመስመር መነሻቸውን ባደረጉ ተሻጋሪ ኳሶች ለማጥቃት ያደረጉት ጥረት እምብዛም ፍሬያማ ሲሆኑ አልተመለከትንም።

ቀዝቃዛ መልክ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሙከራዎች ረገድም ብዙ የታደለ አልነበረም ፤ በአጋማሹ ከመስመር ከሚነሱ ኳሶች ባለፈ በተወሰነ መልኩ ኳስ የመቆጣጠር ፍላጎት የነበራቸው ሰበታ ከተማዎች በአጋማሹ በተለይም በ23ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር በጌቱ ሀይለማርያም አማካኝነት ያሻሙትን ኳስ ዱሬሳ ሹቢሳ ከመከላከያ ተከላካዮች በላይ በመዝለል ሞከራት ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችባቸው ኳስ በአጋማሹ ያደረጓት አደገኛ ሙከራ የነበረች ሲሆን ከዚህ ባለፈ ግን በተለይ ዱሬሳ ሹቢሳ እና ሃይለሚካኤል አደፍርስ በተሰለፉበት የግራ መስመር በኩል የተሻለ የማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል።

በአንፃሩ በአጋማሹ በመከላከሉ ረገድ የተሻሉ የነበሩት መከላከያዎች በማጥቃቱ ረገድ ግን የነበራቸው አፈፃፀም ደካማ ነበር በዚህ ሂደት እንደ ወትሮው ሁሉ ቡድኑ ዕድሎችን ለመፍጠር የቢኒያም በላይን ምትሀት ሲጠባበቅ ተመልክተናል ፤ በ18ኛው ደቂቃ ቢኒያም በላይ ከግራ መስመር ሰብሮ ያቀበለውን ኳስ ተሾመ በላቸው ያመከናት እንዲሁም በ29ኛው ደቂቃ ቢኒያም በላይ ወደ ግራ ካደላ አቋቋም ያሻማውን የቅጣት ምት ኳስ ተሾመ በላቸው በትከሻው በመሸረፍ የሞከራት እና ምንተስኖት አሎ ያዳነበት ኳስ በአጋማሹ የተመለከትናቸው ተጠቃሽ አጋጣሚዎች ነበሩ።
ከወራጅ ቀጠናው ለመላቀቅ ሙሉ ሦስት ነጥብ ያስፈልጋቸው የነበሩት ሰበታዎች በሁለተኛው አጋማሽ ከጅማሮ አንስቶ የተሻለ የማጥቃት ፍላጎትን በማሳየት ሲጫወቱ ተመልክተናል ፤ በዚህም አውንታዊ ለውጦችን በማድረግ ሆነ የመስመር ተከላካዮቻቸውን ይበልጥ ወደ ፊት በማስጠጋት በተጋጣሚ ሜዳ በቁጥር በዝተው በማጥቃት ግብ ለማግኘት ጥረዋል።

ወደ መከላከያ ሳጥን ሲቃረቡ የሰበታ ከተማዎች ማጥቃት ጥራት እንደሚጎድለው የታዘብን ሲሆን በአጋማሹ በ64ኛው ደቂቄ ሳሙኤል ሳሊሶ በቀጥታ ከቆመ ኳስ የሞከረው እንዲሁም በ75ኛው ደቂቃ ዘካርያስ ፍቅሬ ከሳጥን ውጭ ሞክሮ በሁለቱም አጋጣሚዎች ክሊመንት ቦዬ ሊያድንባቸው ችሏል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር አጋማሹን ይበልጥ ጥንቃቄን አክለው የጀመሩት መከላከያዎች የሜዳውን የመጨረሻ 30 ሜትሮችን ጠቅጠቅ ብለው በመከላከል አጋማሹን አሳልፈዋል ፤ በአጋማሹ ግሩም ሀጎስ በ73ኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ከላካት ውጭ ወደ ሰበታ የግብ ክልል ለመድረስ የተቸገሩት መከላከያዎች ከጨዋታው አንድ ነጥብ ለማግኘት ያሰቡ ይመስል ነበር።
በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ጥረታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ሰበታዎች በተለይም በ83ኛው ደቂቃ ዘላለም ኢሳያስ ከቆመ ኳስ ያሻማውን ኳስ ዴሪክ ንሲምባቢ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት ቢሞክርም ክሊመንት ቦዬ በግሩም ሁኔታ አድኖበታል።

ጨዋታ በአቻ ውጤት ለመጠናቀቅ በተቃረበበት ወቅት 87ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ በገባው
ፍፁም ገ/ማርያም ድንቅ ጥረት ወደ ግራ መስመር የወጣውን ኳስ ሃይለሚካኤል አደፍርስ ወደ ውስጥ ሲያሻማ ዴሪክ ንሲምባቢ ተንሸራቶ በማስቆጠሮ ለቡድኑ እጅግ ወሳኝ የሆነች ግብን ማስቆጠር ችሏል።

በዚህችም ግብ አማካኝነት ጨዋታው በሰበታ ከተማ 1-0 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ድል ያስመዘገበው ሰበታ ነጥቡን ወደ 12 በማሳደግ ወደ 15ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ መከላከያዎች ደግሞ በነበሩበት 11ኛ ደረጃ ላይ ረግተዋል።