የ17ኛ ሳምንት ሁለተኛ የምሽት ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ሰበታ ከተማ መከላከያን አንድ ለምንም ከረታ በኋላ አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ተከታዮን አስተያየት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ብርሀኑ ደበሌ – ሰበታ ከተማ
ስለ ደስታ አገላፃቸው
ማሸነፍ በጣም ናፍቆን ነበር። ጎሉም የመጨረሻ ደቂቃ የተገኘ በመሆኑ ምን አልባት አሸናፊ ከሆንን በኋላ ቡድኑን ወደ ፊት ለማስቀጠል መነሻ ይሆናል ከሚል ስሜት እንጂ ገና ብዙ ይቀረናል። ገና እታችኛው እርከን ነው ያለነው። ስለዚህ ያ ደስታ ያንን የሚያመላክት ነው።
ከአስር በላይ ነጥብ መያዛቸው በስነ ልቦናው ስለሚኖረው ጠቀሜታ
አዎ ምን አልባት ማሸነፍ ስትጀምር በማሸነፍ ውስጥ ሆነህ ያንን ለማስቀጠል ትንሽ ከፍ ሊያደርግህ ይችላል። በውስጥህ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ትንሽ አቅም እንዲኖርህ ስለሚያደርግ ማሸነፋችን ለቀጣይ ጥሩ መነሳሳት ይፈጥራል።
ስለ ኃይለሚካኤል አደፍርስ
ኃይለሚካኤል ገና ወጣት ልጅ ነው። ከፊቱ የሚነበበው ወደፊት ትልቅ ተጫዋች ይሆናል ተብሎ የሚታሰብ ድንቅ ተጫዋች ነው። የመከላከል ስራውን በአግባቡ ይወጣል። ወደፊትም ጫና በመፍጠር አንብቦ የሚጫወት ጎበዝ ልጅ ነው። ወደ ፊትም ለሀገራችን ተስፋ የሚሆን ነው።
ለመስመር ተከላካዮቹ ስለተሰጠ ሚና
የተሰጠው ሚና በሁለቱም በኩል ጥሩ ነው። ጌቱ ትንሽ አናሳ ሆነ እንጂ የነበረው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው። አንዳንዴ ኳሱ ተበላሸ እንጂ ጥሩ አካሄድ አለው። በተረፈ ግን የኃይለሚካኤል እጅግ በጣም የሚደንቅ ነው። ለጎሏም መገኘት የኃይለሚካኤል እንቅስቃሴ አስተዋፆኦ ነበረው።
ድሉን ለማን ያበረክቱታል
ይህን ድል ለመላው የሰበታ ከተማ ህዝብ እና በቅርቡ እንደ እናቴ ለማያት ካረፈች ሦስተኛ ቀኗ ለሆነው አክስቴ ለእርሷ መታሰቢያ ቢሆን ደስ ይለኛል።
አሰልጣኝ ዩሐንስ ሳህሌ – መከላከያ
ጨዋታውን መቆጣጠር ስላልቻሉበት ምክንያት
እነርሱ ከእኛ የተሻሉ ነበሩ። የተሻለ ቡድን አሸንፏል።
ስለ የተጫዋች ለውጥ
የመሐል ተጫዋችን ወደ ኋላ ወስደህ ስታጫውት ቦታው ክፍት ይሆናል። የመሐል ተከላካይ በአሁኑ ሰዓት ስለሌለን የግድ አማካይ ተጫዋችን ወደ ኋላ ወስደን አጫውተናል። በዚህም መሐሉ ክፍት ይሆናል። ይህ ብቻ ምክንያት ሊሆን አይችልም። እነርሱ ከእኛ የተሻሉ ነበሩ።
በአጥቂ እና በአማካይ መካከል ስለነበረው መራራቅ
ምክንያት መሆን ይችላል። ዞሮ ዞሮ አጠቃላይ ምክንያት መሆን አይችልም። እነርሱ ዛሬ የተሻሉ ስለነበር አሸንፈዋል። ቡድኑን ማቀናጀት አለብን አዲስ የገቡ አራት ልጆች አሉ። ግን ትንሽ ምክንያት ነው። ሙሉ ምክንያት አይደለም። ግን በማንኛውም መንገድ እነርሱ ከእኛ በተሻለ በማጥቃትም በመከላከልም የተሻሉ ነበሩ። መሐል ሜዳ ላይ ኳሱን በመቆጣጠር ወደ ጎልም በመሞከር የተሻሉ ስለነበር አሸንፈዋል።
ሽንፈቶች በመጡ ቁጥር ስጋት ስለመኖሩ
ከጨዋታው በፊት እንደተናገርኩት ሁሉም ነጥብ ይፈልጋል። እኛም ሦስት ነጥብ ፈላጊ ነን። ስለዚህ ቀላል እና ከባድ ጨዋታ የሚባል የለም። የሚመራ ቡድን ወይም ከታች ያለ ቡድን አለ አይባልም። በአሁን ሰዓት ብዙ ቡድኖች ተጫዋቾቻቸውን ቀይረዋል። አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው ቀላቅለዋል። እራሳቸውን አጠናክረዋል። ስለዚህ የሁለተኛው ዙር ጨዋታ ሁልጊዜ ከባድ ስለሚሆን ሰርተህ መምጣት አለብህ።