ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ወልቂጤ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የነገ ቀዳሚ መርሐ-ግብር የሆነው ፍልሚያ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ካለፉት አራት ጨዋታዎች ተመሳሳይ አራት ነጥብ ያገኙት ፋሲል ከነማ እና ወልቂጤ ከተማ በሁለተኛውን ዙር ጅማሮ ካጋጠማቸው የአቻ ውጤት ወደ ድል ለመምጣት የሚያደርጉት ጥረት ትኩረት የሚስብ መሆኑ አይቀሬ ነው። ወጥ ብቃት ማሳየት የተሳነው የወቅቱ የሊጉ ባለክብር ፋሲል ከነማ ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን የአስር ነጥብ ልዩነት ለማጥበብ እና በዋንጫ ፉክክሩ ለመዝለቅ ወደ ሜዳ ሲገባ በደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ ደግሞ የውድድር ዓመቱ ስድስተኛ ድሉን በማሳካት በጊዜያዊነት ወደ ስድስተኛ ደረጃ ከፍ ለማለት እንዲሁም በእንቅስቃሴ ደረጃ ያለውን መሻሻል በውጤት ለማሳጀብ ብርቱ ትግል እንደሚያደርግ ይገመታል።

ባሳለፍነው ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር አንድ ለአንድ አቻ የተለያየው ፋሲል ከነማ በጨዋታው ያሳየው የሁለቱ አጋማሾች ብቃት ትንሽ የሚያሳማው ነው። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት መሐከል የሌለው እንደነበር አስተውለናል። የቡድኑ አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ከወትሮ በተለየ የአማካይ መስመር ተጫዋች ቀንሰው ሁለት አጥቂ አሰልፈው በጀመሩት ጨዋታ ላይ ሙጂብ እና ኦኪኪ የታሰበውን ያክል ውህደት ሳይፈጥሩ ተነጥለው ነበር። እርግጥ አሠልጣኙ ይህንን ክፍተት ተመልክተው በሁለተኛው አጋማሽ ለውጦችን በማድረግ መጠነኛ መሻሻል በሜዳው የላይኛው ክፍል ለማድረግ ቢጥሩም በእስካሁኖቹ 16 ጨዋታዎች ካስመዘገቡት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሁለተኛ ትንሽ የተመዘገበበት (በ8ኛ ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር ካስመዘገቡት እኩል ሁለት) የጨዋታ ቀን አሳልፈው ከሜዳ ወተዋል። በተለይ ከላይ የጠቀስናቸው አጥቂዎች ተመሳሳይ የጨዋታ ባህሪ ከመከተላቸው ጋር ተያይዞ የአማካይ መስመሩ ከአጥቂ ክፍሉ ጋር የሚገናኝበት ድልድል በአግባቡ መሰራት ይሻል። በነገው ጨዋታ ባለፈው ከታየው ጉልህ ክፍተት መነሻነት ይህ ስህተት ይቀረፋል ተብሎ ይጠበቃል። በጨዋታው ሀዲያ ወደ ጎንም ሆነ ወደፊት ችምችም ብሎ ያለ ኳስ ከመታተሩ ጋር በተገናኘ በግል ብቃታቸው ጨዋታን መወሰን የሚችሉት የዐፄዎቹ ተጫዋቾች ክፍተት አጡ እንጂ ተፅዕኗቸው ውጤት ያስገኝ ነበር። የነገው ተጋጣሚያቸው ወልቂጤ ግን ያን ያህል ግጥግጥ ብሎ የሚከላከል ስላልሆነ የቀደመ ብቃታቸውን ሊያሳዩ እና ቡድናቸውን ሊጠቅሙ ይችላሉ።

አሠልጣኝ ተመስገን ዳናን በመንበሩ ከሾመ በኋላ በእንቅስቃሴ ደረጃ መጠነኛ መሻሻል ያሳየው ወልቂጤ ከተማ በፍላጎት በመጫወት፣ ኳስን በመቆጣጠር እና በአደገኛ ቦታዎች ተሽሎ በመገኘት ረገድ ጥሩ ቢመስልም የወጥነት ችግር ይስተዋልበታል። ቡድኑ በቀድሞ አሠልጣኙ ጻውሎስ በመጨረሻ 4 ጨዋታቸው ስድስት ግብ አስቆጥሮ አስራ አንድ ግቦችን ሲያስተናግድ በአዲሱ አሠልጣኝ ደግሞ በመጀመሪያ አራት ጨዋታቸው አራት ጎል አስቆጥሮ በተመሳሳይ አራት ግብ በማስተናገድ ሚዛናዊ መስሏል። የሆነው ሆኖ ከላይ የገለፅነው የወጥነት ችግር ግን በአራቱ ጨዋታዎች ከተመዘገቡት የአቻ፣ድል እና ሽንፈት ውጤቶች ባለፈ በእንቅስቃሴ ደረጃም በጉል እየታየ ነው። በመጨረሻው የአዳማ ፍልሚያም እንኳን በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ አቀራረብ በመከተል ባለሜዳዎቹን ቢፈትኑም በሁለተኛው አጋማሽ ግን ያንን አጨዋወት ማስቀጠል ሳይችሉ ለአዳማ መነቃቃት እጅ ሰጥተው ታይተዋል። ምንም ቢሆን ምንም ግን በነገው ወሳኝ ጨዋታ የቡድኑን ከግማሽ በላይ ግብ ያስቆጠሩት ጌታነህ ከበደ እና ጫላ ተሺታ ለፋሲል ተከላካዮች የራስ ምታት መሆናቸው አይቀርም። ከዚህ ውጪ በወራጅ ቀጠናው ከሚገኙ ክለቦች ውጪ ዛሬ አራት ግብ ተቆጥሮበት ከተረታው ኢትዮጵያ ቡና ጋር በጣምራ ብዙ ግብ ያስተናገደ ሁለተኛው ክለብ የሆነው ወልቂጤ ወሳኞቹን የፋሲል የወገብ በላይ ተጫዋቾች መቆጣጠሪያ መላ ነገ መዘየድ የግድ ይለዋል።

ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ክለብ የሆነው ፋሲል በሁለቱ መስመሮች በኩል ጥቃት ለመሰንዘር ተቀዳሚ ዕቅድ እንደሚኖረው ይታሰባል። በተለይ ደግሞ ወልቂጤ ከተማ አጥቦ ስለሚጫወት በሁለቱ መስመሮች ክፍተት እንደሚያገኝ ይገመታል። በተቃራኒው ሠራተኞቹ እንደ ቅፅል ሥማቸው በላይኛው የሜዳ ክፍል የፋሲልን የኳስ ምስረታ እያጨናገፉ የጎል ማግባት አጋጣሚ ብዙም ከግቡ ሳይርቁ ለመፈለግ እንደሚታትሩ ቀድሞ መናገር ይቻላል። ከዚህ ውጪ ግን ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ለመቆጣጠር ከሚኖራቸው ፍላጎት መነሻነት የመሐል ሜዳው ፍትጊያ ጨዋታውን የመወሰን ሀይል ይኖረዋል።

ፋሲል ከነማ በጉዳትም ሆነ በቅጣት ምክንያት ነገ የሚያጣው ተጫዋች የሌለ ሲሆን ወልቂጤ ከተማ በበኩሉ የመሐል ተከላካዩ ዳግም ንጉሴን በአምስት ቢጫ ምክንያት አያገኝም። በመጨረሻው የዝውውር ቀን ያስፈረመው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አማካይ ኤዲ ኢሞሞ ኒጎዬም በጨዋታው ተሳትፎ እንደማይኖረው ተመላክቷል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ሦስት ጊዜ ተገናኝተው ሦስቱንም ጨዋታ ፋሲል ከነማ በተመሳሳይ 1ለ0 በሆነ ውጤት ረቷል።

ግምታዊ አሠላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)

ሚኬል ሳማኪ

ዓለምብርሃን ይግዛው – አስቻለው ታመነ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ሀብታሙ ተከስተ

ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው – በረከት ደስታ

ሙጂብ ቃሲም

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ሰዒድ ሀብታሙ

ተስፋዬ ነጋሽ – ዮናስ በርታ- ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

በሀይሉ ተሻገር – ሀብታሙ ሸዋለም – ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ

አብዱልከሪም ወርቁ – ጌታነህ ከበደ – ጫላ ተሺታ