ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የሊጉ 17ኛ ሳምንት ነገም ሲቀጥል ሁለተኛውን ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን አንስተናል።

ከድል ጋር ከተራራቁ አራት ጨዋታዎች ያለፏቸው ባህር ዳር እና ሆሳዕና ነገ ምሽት እርስ በእርስ ይገናኛሉ። ተከታታይ አቻዎች እያስመዘገበ የሚገኘው ባህር ዳር 7ኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ ከውድድሩ በፊት ከተሰጠው የዋንጫ ፉክክር ግምት እጅግ የራቀ ነው። በሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ያን ያህል ደከማ የማይባለው ሀዲያ ሆሳዕናም ከወረጃ ቀጠናው ሦስት ነጥብ ርቀት ላይ ብቻ ነው የሚገኘው። የነገው ጨዋታ ከሁለቱ ተጋጣሚዎች ማን ወደ ድል መንገድ ቀድሞ ይመለሳል የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ እንደሆነም ይጠበቃል።

በመጨረሻ አራት ጨዋታዎቹ ሦስት ግቦችን ብቻ ያሳካው የባህር ዳር ከተማ የማጥቃት መንገድ በተለይም በአዲስ አበባው ጨዋታ ተዳክሞ ይታይ ነበር። ኳስ መስርቶ ከሜዳው ለመውጣት ውጥኑ ያለው ቡድኑ ይህንን ለማድረግ የተጋጣሚን ጫና ተቋቁሞ በስኬታማ ቅብብሎች አደጋ መፍጠር ወደሚችልበት የሜዳ ክፍል የሚደርስበት ፍጥነት ዝግ ያለ ነበር። በዚህም መነሻነት የፊት አጥቂው ዓሊ ሱሌይማን በቂ አቅርቦት ሳያገኝ ተነጥሎ ስንመለከተው ቡድኑም የመጨረሻ ዕድል ለመፍጠር ከኳስ ምስረታው ሂደት ይልቅ የፍፁም ዓለሙን የግል ጥረቶች የሚጠብቅ ይመስል ነበር። በዚህ ላይ በኋላ መስመሩ ላይ የሚታየው የመናበብ ችግር እና ግለሰባዊ ስህተቶች የጣና ሞገዶቹን ዋጋ አስከፍሏል።

ሀዲያ ሆሳዕናም እንዲሁ የማጥቃት አጨዋወቱ ተደካሞ ሰንብቷል። በጨዋታ ከአንድ በላይ ግብ ያስቆጠረበትን ጊዜ ለማግኘት ወደ ኋላ አምስት ጨዋታዎችን ተጉዘን ሊያውም በደካማው ጅማ 4-2 የተረታበትን ጨዋታ ነው የምናገኘው። በሦስት ተከላካዮች በሚጀምር አሰላለፍ የሚጠቀሙት ነብሮቹ ታታሪ የመስመር ተመላላሾችን ቢይዙም የግራ እና ቀኝ እንቅስቃሴያቸውን በዓላማ በመከወን ለቡድኑ የግብ መፍጠሪያ መሳሪያ በማድረጉ በኩል ድክመት ይታይባቸዋል። በተለይም በሜዳው ቁመት በሚደረጉ ሩጫዎች ዘግይተው ወደ ሳጥን የሚደርሱ አማካዮች የጎል አበርክቶት ከዋና አጥቂዎቹ ተፅዕኖ ጋር አብሬ መቀነስ ጋር ተዳምሮ የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ቡድኑ የግብ ፊት ውሳኔዎች እንዲዳከሙ ምክንያት ሆኗል።

ከዚህ አንፃር የነገው ጨዋታ በሁለት ደካማ የማጥቃት ጉልበት ባለቸው ቡድኖች መካከል የሚደረግ ነው ማለት ይቻላል። እዚህ ላይ ባህር ዳር ከተማ ኦሴይ ማዉሊን ከጉዳት መልስ ማግኘቱ ተጫዋቹ ግብ ከማስቆጠር ባለፈ ለሌሎች ክፍተት በመፍጠር በኩል ካለው ጥንካሬ አንፃር ባህር ዳርን ተጠቃሚ ሊያደርገው ይችላል። የፍፁም ዓለሙ እና ተስፋዬ አለባቸውን ፍልሚያ በሚጠበቅበት በነገው ጨዋታ የሀዲያ ሆሳዕና የቀኝ መስመር ጥቃት መነሻ የሆነው ብርሀኑ በቀለ ከቅጣት ከሚመለሰው አህመድ ረሺድ ጋር የሚያደርገውን ፍልሚያም ያስመለክተናል። በአቀራረብ ደረጃ ለውጥ ላያደርግ የሚችለው ሆሳዕና ፈጠን ባሉ ጥቃቶች በተለይም ከቀኙ ወገን በሚነሱ ኳሶች የመጨረሻ ዕድሎችን የማግኘት ዕድል ይኖረዋል። በባህር ዳር በኩል በቅብብሎች የመውጣት ዕቅዱ እንዳለ ሆኖ ለፈጣን ሽግግር የሚመቹ ቅፅበቶች ሲኖሩ ቡድኑ ወደ ግብነት መቀየር የሙያስችል የጨዋታ ዕቅድ እንደሚኖረው ይገመታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ነገ በሊጉ ለአራተኛ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል። ከዚህ ቀደም በነበሩ ሦስት ጨዋታዎች ባህር ዳር ከተማ ሁለቴ ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ አንድ ጊዜ 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለው ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ፍሬዘር ካሳ – ቃለአብ ውብሸት – ሄኖክ አርፌጮ

ብርሃኑ በቀለ – ሳምሶን ጥላሁን – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረእየሱስ ተክለብርሃን – ኢያሱ ታምሩ

ሀብታሙ ታደሠ – ባዬ ገዛኸኝ

ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ፋሲል ገብረሚካኤል

መሳይ አገኘሁ – መናፍ ዐወል – ፈቱዲን ጀማል – አህመድ ረሺድ

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ፉዐድ ፈረጃ

አብዱልከሪም ኒኪማ – ፍፁም ዓለሙ – ዓሊ ሱለይማን

ኦሲ ማውሊ

ያጋሩ