ፈጣን እድገት እያሳየ የሚገኘው ወጣቱ ተከላካይ ቃለአብ ውብሸት

👉”በፕሮጀክት እና በሰፈር ስጫወት የአጥቂ መስመር ተጫዋች ነበርኩ”

👉”ከልጅነቴ እንደ አርዐያ አድርጌ የወሰድኩት ተጫዋች…”

👉”አሠልጣኞቼ የሚነግሩኝን ነገር በመስማቴ እና በደንብ በመስራቴ ነው እዚህ የደረስኩት”

👉”ያሉብኝን ብዙ ክፍተቶች አስተካክዬ በብሔራዊ ቡድን ሀገሬን ማገልገል እሻለው”

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማሮውን ሀዋሳ ላይ በማድረግ በድሬዳዋ ዘልቆ በአሁኑ ሰዓት በአዳማ የሁለተኛ ዙር ውድድሩን እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። እስካሁን በተደረጉት የጨዋታ ሳምንታት በርከት ያሉ ወጣት ተጫዋቾችን የተመለከትን ሲሆን የዛሬው እንግዳችን ደግሞ ከሁሉም በላይ የተሻለ የጨዋታ ዕድል በማግኘት ቡድኑን በሚገባ እያገለገለ የሚገኝ ወጣት ነው። እንግዳችን ድፍረት፣ አካላዊ መፈርጠም፣ እርጋታ፣ ቅልጥፍና፣ ቦታን እና አደጋን የማንበብ ክህሎት እንዲሁም ትኩረት በሚፈልገው የተከላካይ መስመር ላይ በወጥነት በመጫወት ገና ብዙ ያልተጓዘው የእግር ኳስ ህይወቱን በጠሩ ሁኔታ እያስኬደ ይገኛል። ወቅታዊ ብቃቱ ምርጥ የሆነው እንግዳችን የሀዲያ ሆሳዕናው የመሐል ተከላካይ ቃልዓብ ውብሸት አበበ ነው።

ቃለዓብ ተወልዶ ያደገው ከአዲስ አበባ 230 ኪሎ ሜትሮችን ርቃ በምትገኘው ሆሳዕና ከተማ ልዩ ስሙ ማረሚያ ሰፈር በሚባለው ቦታ ላይ ነው። እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እግር ኳስን በሰፈር ውስጥ በጨርቅ ኳስ በመጫወት እንደጀመረ የሚናገረው ቃለዓብ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ የእግር ኳስ ፍቅር በውስጡ እንዳደረበት ሳይሸሽግ ይመሰክራል። ፍቅሩን ለማስታገስም በሰፈር እና በትምህርት ቤት ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ረጅሙን መንገድ ‘ሀ’ ብሎ ጀምሯል። “ከልጅነቴ ጀምሮ እግር ኳስ የመጫወት ፍላጎት ስለነበረኝ ሰፈር ውስጥ በጣም እጫወት ነበር። በምማርበት ትምህርት ቤትም ውድድሮች ሲኖሩ ሳላቅማማ እሳተፍ ነበር። ትንሽ አደግ ስል ደግሞ እዛው ሰፈሬ ውስጥ እንደ ፕሮጀክት አይነት ቡድኖች ነበሩ ፤ እነሱ ጋር ገብቼ የተሻለ ስልጠና በመውሰድ ራሴን አጎልብቻለው።”

ባደገበት ማረሚያ ሰፈር በሚገኙት ተስፋ እና ግሪን ስታር ፕሮጀክቶች በድምሩ ስድስት ዓመታት የሰራው ተጫዋቹ በመቀጠል ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ከ20 ዓመት በታች ቡድን አምርቷል። “ሦስት ሦስት ዓመት በሁለቱ ፕሮጀክቶች ከሰራሁ በኋላ የትውልድ ከተማዬን የዕድሜ ቡድን ተቀላቅያለው። 2012 የመጀመሪያ ወራት ላይ የከተማውን ሁለተኛ ቡድን መቀላቀል የቻልኩት የሆነ ውድድር ተዘጋጅቶ ነበር። ወደ 30 የምንሆን ልጆች ተመርጠን ነው ወደ ቡድኑ የገባነው። ቡድኑን ከተቀላቀልኩ በኋላ ራሴን በሚገባ እያጎለበትኩ መታየት ጀመርኩ። እንደ አጋጣሚ በቀጣዩ ዓመት በቢጫ ቴሴራ ተይዤ ነበር። አንድ ዓመት በሁለተኛው ቡድን ባሳየሁት ጥሩ እንቅስቃሴ አሠልጣኝ አሸናፊ እያለ እኔን ጨምሮ አምስት ልጆች በቢጫ ቴሴራ በዋናው ቡድን ተይዘን ነበር። በዛው የከተማዬን ዋናውን ቡድን ተቀላቅዬ ቀጠልኩ።”

እንደ ሜዳ ላይ ደፋርነቱ ሳይሆን ከሜዳ ውጪ ቁጥብ እንደሆነ የሚነገርለት ቃለዓብ የዝግጅት ክፍላችን የሚያቀርብለትን ጥያቄ በአጭር ቃላት መመለሱን በመቀጠል ስለእግር ኳስ አርዐያው ተከታዩን ብሎናል። “የእኔ አርዐያ ዓይናለም ኃይሉ ነው። አይናለምን በጣም ነው የምወደው። በጣምም ነው የማከብረው። ከልጅነቴም እንደ አርዐያ አድርጌ የወሰድኩት ተጫዋች እሱን ነው።”

ዓምና በቢጫ ቴሴራ ተይዞ በመጀመሪያው ዙር ውድድር ብዙም የጨዋታ ዕድል ሳያገኝ ቆይቶ የክለቡ አንጋፋ ተጫዋቾች ከክፍያ ጋር ተያይዞ በገቡበት እሰጣ ገባ ምክንያት ከቡድኑ ሲገለሉ በሊጉ የመጫወት ዕድል ያገኘው ቃለዓብ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታውን ስላደረገበት አጋጣሚ ይህንን ያስታውሳል። “እንዳልኩት በሁለተኛው ቡድን ባሳየሁት ጥሩ ብቃት 2013 ላይ ዋናውን ቡድን ተቀላቅዬ ነበር። ዓምና በክለባችን በተፈጠረው ችግር ምክንያት ደግሞ ሀዋሳ ላይ በተደረጉት የመጨረሻዎቹ ሳምንታት መርሐ-ግብሮች የጨዋታ ዕድል ተሰጠኝ። የመጀመሪያ ጨዋታዬም በሀገራችን ከሚገኙ ትልቅ እና ብዙ ደጋፊ ካላቸው ክለቦች መካከል አንዱ ከሆነው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነበር። በዛ ጨዋታ የመስመር ተከላካይ ሆኜ እንዳገለግል ነበር የተደረኩት። ስሜቱ በጣም ደስ የሚል ነበር። አሪፍ ነገርም አሳይቼ የወጣው ይመስለኛል።”

ዓምና አራት ጊዜ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች (ከኢትዮጵያ ቡና እና ጅማ አባ ጅፋር ጋር) የተጫወተው ተጫዋቹ ዘንድሮ የበለጠ ጎልብቶ ሀዲያ ጨዋታ ባለው ቁጥር አስገዳጅ ነገር ከሌለ ውጪ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የማይጠፋ ሥም ባለቤት እየሆነ መጥቷል። በስብስቡ ከ1000 ደቂቃዎች በላይ ግልጋሎት ከሰጡ የቡድኑ ስምንት ተጫዋቾች መካከልም አንዱ ሆኗል። ከዚህም መነሻነት በአጭር ጊዜ ይሄንን ያህል እድገት የማሳየቱን እና ምርጥ ብቃት ላይ የመገኘቱን ሚስጥር በተመለከተ “እግዚአብሔር ይመስገን። ምንም ሚስጥር የለውም። አሠልጣኞቼ የሚነግሩኝን ነገር በመስማቴ እና በደንብ በመስራቴ ነው እዚህ የደረስኩት። በተጨማሪም ከእኔ የተሻለ ልምድ ያላቸው የቡድን አጋሮቼ የሚመክሩኝን ነገር በደንብ እሰማለው። እኔም ደግሞ የማገኛቸውን ዕድሎች ዐይኔን ሳላሽ በአግባቡ ለመጠቀም እሞክራለው። እነዚህ ነገሮች ተደራርበው ጥሩ ብቃት እንዳሳይ ያደረጉኝ ይመስለኛል።” በማለት ይናገራል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በበላይነት ከሚመራው አክሲዮን ማኅበር ባገኘነው ይፋዊ የተጫዋቹ እድሜ 19 ዓመት ከ 25 ቀን ላይ የሚገኘው ቃለዓብ ገና በለጋ እድሜው በዚህን ያህል ደረጃ ቡድኑን ማገልገሉ የብዙዎችን ቅንድብ በግርምት ወደ ላይ የሰቀለ ነው። ራሱን ለማሳደግ ከቡድን የልምምድ መርሐ-ግብሮች በተጨማሪ ለብቻው ልምምድ እንደሚሰራ የሚናገው ተጫዋቹ በአብዛኛው የተከላካይ ቦታ የሚፈልገውን የጥንካሬ ሥራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ ይገልጻል።

እግር ኳስን በአጥቂ መስመር የጀመረው ቃለዓብ ወደ ተከላካይ መስመር የተለወጠበትን ሂደት በአጭሩ አጫውቶናል “በፊት ተከላካይ አልነበርኩም። በፕሮጀክት እና በሰፈር ስጫወት የአጥቂ መስመር ተጫዋች ነበርኩ። በፕሮጀክት ተስፋ በተባለ ቡድን ሲያሰለጥነኝ የነበረው እሸቱ ነጋ ነው አጨዋወቴን በማየት ተከላካይ እንድሆን ያደረገኝ። ይህ ለእኔ ጥሩ አጋጣሚ ነው። ይህ ቦታ በጣም ነው የተመቸኝ። የተከላካይ ተጫዋች ሆኜም ነው የምዘልቀው።”

1 ሜትር ከ 85 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው እና 70 ኪሎ የሚመዝነው ቀልጣፋው ተከላካይ በሦስትም ሆነ በአራት የተከላካይ ጥምረት ከበለራዎቹን ግልጋሎት እየሰጠ ይገኛል። ተከላካዮች ተቀዳሚ ሥራቸው የሆነውን ኳስ የማጨናገፍ፣ የማፅዳት እና የመመከት ሥራን ከመከወኑ በተጨማሪ ዘመናዊ እግር ኳስ የሚጠይቀውን የኳስ ምስረታ ሂደት በምቾች የሚከውነው ተጫዋቹ በእድገቱ ላይ ትልቅ አሻራ ያሳረፉበትን ሰዎች ስም ከጠቀሰ በኋላ ዘንድሮ የተሻለ የመጫወቻ ዕድል የሰጠውን አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በአጭር ቃላት አመስግኗል። “በእኔ የእግር ኳስ ዕድገት ብዙ ሰዎች አስተዋጽኦ ነበራቸው። በዋናነት አላምረው ካሣ፣ እሸቱ ነጋ፣ ወንዱ ማቲዮስ፣ አሸናፊ ከበደ እና ደግነት ትልቅ ነገር አርገውልኛል። ስለሙሉጌታ ምህረት ምን እንደምል አላውቅም። ከእሱ ጋር በመስራቴ በጣም ዕድለኛ ነኝ። በጣም ላመሰግነው እወዳለው።”