ሪፖርት | ወልቂጤ በፋሲል ላይ የመጀመሪያውን የእርስ በእርስ ድል አስመዝግቧል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በመጀመሪያው አጋማሽ ሦስት ግቦችን ባስተናገደው አዝናኝ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ፋሲል ከነማን 2-1 አሸንፏል።

ሁለቱ ቡድኖች ከመጨረሻ ጨዋታቸው በተመሳሳይ ሁለት ለውጦች አድርገዋል። ፋሲል ከነማ ሚኬል ሳማኬ እና ሱራፌል ዳኛቸውን በይድነቃቸው ኪዳኔ እና ኦኪኪ አፎላቢ ቦታ በመጠቀም በ4-1-4-1 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምሯል። 4-2-3-1ን ምርጫው ያደረገው ወልቂጤ ከተማ ደግሞ አዲስ ፈራሚው አክሊሉ ዋለልኝን እና ከጉዳት የተመለሰው ረመዳን የሱፍን በያሬድ ታደሰ እና አምስት ቢጫ ባለበት ዳግም ንጉሴ ተክቷል።

ፈጠን ባለ ፉክክር የጀመረው ጨዋታ በቶሎ ነበር በሁለቱም ጎሎች በኩል ሙከራዎችን ማሳየት የጀመረው። 2ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ በረከት ደስታ የሰነጠቀለትን ኳስ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ ሰዒድ ሀብታሙ ሲያድንበት 5ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ጌታነህ ከበደ ከጫላ ተሺታ የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብ ሲሞክር ወደ ውጪ ወጥቶበታል። በሂደት ፋሲሎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ወስደው በወልቂጤ ሜዳ ላይ ቅብብሎችን ሲከውኑ እና አልፎ አልፎ አደጋ የሚቃጡ ኳሶችን ወደ ሳጥን ውስጥ ሲልኩ ወልቂጤዎች በበኩላቸው ጠንቀቅ ብለው መቆየትን መርጠዋል።

እንደሌላው ጊዜ ኳስ ለመያዝ ጥረት ያላደረጉት ሰራተኞቹ አብዱልከሪም በግራ በኩል ተጫዋቾችን አታሎ የመለሰለትን ጫላ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ ሳማኬ በቀላሉ በያዘበት ኳስ ወደ ግብ የመድረስ ምልክትን መስጠት ጀምረው ሳይታሰብ ሁለት ተከታታይ ግቦችን አስቆጥረዋል። 17ኛው ደቂቃ ላይ ወልቂጤዎች መሀል ላይ በጥሩ የኳስ ንክኪዎች የጀመሩትን ማጥቃት አብዱልከሪም ወርቁ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ ሚኬል ሳማኬ ሲተፋው ጫላ ተሺታ ደርሶ አስቆጥሮታል። ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ በፋሲል የኳስ ምስረታ ሂደት ላይ ጌተነህ ከበደ ከያሬድ ባየህ የነጠቀውን ኳስ እየነዳ ሳጥን ውስጥ በመግባት በሳማኬ መረብ ላይ አሳርፎታል።

ከግቦቹ በኋላ ፋሲሎች በጀመሩበት መንገድ አጥቅተው መጫወትን ቀጥለዋል። የ25ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ያደረሰውን ኳስ ሙጁብ በቀኝ ከጠባብ አንግል ሞክሮ ሰዒድ ያዳነበት ኳስ ፋሲል ለመመለስ ያደረገው የመጀመሪያው ጥረት ነበር። ጨዋታው ከውሀ ዕርፍት ሲመለስ ፋሲል ከነማ ጫናውን ይበልጥ አጠንክሮ ቀጥሏል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ወልቂጤ በጫላ ፋሲል ደግሞ በበረከት ካረጓቸው ያልተሳኩ ጥረቶች በኋላ ፋሲል ከነማ ልዩነቱን ያጠበበትን ጎል አግኝቷል። 35ኛው ደቂቃ ላይ ሙጂብ እና ሽመክት ከወልቂጤ ተከላካዮች ጋር በግቡ ቅርብ ርቀት ለኳስ ከታገሉ በኋላ ሽመክት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

በሽመክት ግብ የተነቃቁት ፋሲሎች በአጋማሹ በኳስ ቁጥጥር የበላይነት እና አደጋ ዞን ላይ በመገኘት የበላይ ሆነው ቆይተዋል። 41ኛው ደቂቃ ላይ ወደግራ ያደላ የቅጣት ምት አጋጣሚን ሱራፌል ያሻማል ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ግብ ያደረገውን ሙከራ በሰዒድ ድኗል። አዝናኙ አጋማሽ በሁለቱም ግቦች ላይ በተደረጉ ተከታታይ ኢላማቸውን ያልጠበቁ ጥረቶች እና በሳጥኑ መግቢያ ላይ አበባው ቡታቆ በእጁ የነካውን ኳስ ተከትሎ በታየው የፋሲሎች የፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄ እና የአርቢትር ለሚ ንጉሴ ምላሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ፋሲሎች ጫና በመፍጠሩ ካቆሙበት ቀጥለዋል። ኦኪኪ አፎላቢን ቀይረው በማስገባት እና በወልቂጤ ሳጥን ዙሪያ በማጥቃት ወቅት ያላቸውን የተጫዋቾች ቁጥር በመጨመር ለከባድ ሙከራ የቀረቡ ጥረቶችን ከአጫጭር ቅብብሎችም ሆነ ከመሀል በሚጣሉ ረዘም ያሉ ኳሶች ሲፈጥሩ ታይተዋል። በአንፃሩ አማካይ ክፍላቸውን በሁለት ቅያሪዎች ማጠናከርን የመረጡት ወልቂጤዎች የፋሲልን ጫና ተቋቁመው ጌታነህ ከበደን ማዕከል ያደረጉ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን ለመገኘት ፍላጎት እንዳላቸው ታይቷል።

በዚህ እሳቤ ውስጥ ቡድኖቹ በተለይም ፋሲል በየፊናቸው ጥሩ ጥሩ የማጥቃት ሂደቶችን እያሳዩ ሲቀጥሉ ቀዳሚው ከባድ ሙከራ 72ኛው ደቂቃ ላይ ጫላ ተሺታ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ በላከው ኳስ ሲታይ ሚኬል ሳማኪ በጥሩ ሁኔታ አውጥቶበታል። ከቅያሪዎች በኋላ ያለ ተፈጥሯዊ ተከላካይ አማካይ ፋሲሎች ሁሉንም ነገር ወደ ፊት መወርወራቸውን ሲቀጥሉ የወልቂጤዎች ጥንቃቄ ግን አፄዎቹ ወደ ሳጥን በሚጣሉ ረዘም ያሉ ኳሶች እንዲገደቡ አስገድደዋል። 82ኛው ደቂቃ ላይ ወልቂጤዎች የተመኙትን መልሶ ማጥቃት አግኘተው ሳጥን ውስጥ ሲደርሱ ጌታነህ ከአብዱልከሪም የደረሰውን ኳስ አክርሮ መትቶ ሳማኪ በድጋሚ ከባድ ሙከራ አድኗል።

አዝናኙ ጨዋታ እስከመጨረሻው በሙከራዎች ታጅቦ ቀጥሏል። 87ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም 2-1 በሆነ የቁጥር ብልጫ የተፈጠረውን የመልሶ ማጥቃት ዕድል ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ሞክሮ ወደ ላይ ሲነሳበት ወዲያው ሱራፌል በሌላኛው ግብ ላይ ከርቀት የሞከረው ከባድ ኳስ በግቡ አግዳሚ ተመልሷል። ሆኖም ወልቂጤዎች የፋሲልን ጥቃቶች ለመቋቋም ያደረጉት ጥረት እስከመጨረሻው ተሳክቶላቸው ጨዋታውን አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

ወልቂጤ ከተማ ፋሲልን በአራተኛ የእርስ በእርስ ግንኙነት ለመጀመሪያ ጊዜ መርታት ሲችል ነጥቡን 24 በማድረስ ወደ ስድስተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል ፤ ፋሲል ከነማ ከመሪው ጋር ያለው ልዩነት ወደ አስር ነጥብ ከፍ እንዲል ተገዷል።

ያጋሩ