የአሠልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 1-2 ወልቂጤ ከተማ

በወልቂጤ ከተማ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሠልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል።


ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ቡድኑ እድገት?

እስካሁን ባሰብነው መንገድ እየሄድን ነው ብዬ አስባለው። ነገርግን በዛሬው ጨዋታ ላይ ቀድመን በጊዜ ነው ግቦችን ያስቆጠርነው። ጎሎቹን በጊዜ ማስቆጠራችን ተጋጣሚያችን ፋሲል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ጉጉት ወደኋላ የማፈግፈግ ነገር ተመልክቻለው። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ታክቲካሊ የለወጥናቸው ነገሮች ቡድናችንን ተጠቃሚ አድርጎታል።

የፋሲል ተከላካዮችን ስህተት ለመጠቀም ስላሰቡበት መንገድ?

ስህተቶቹ የሚጠበቁ ነበሩ። ምክንያቱም የፋሲል ተከላካዮች የብሔራዊ ቡድኑ ተከላካዮች ናቸው። በራስ መተማመናቸው እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ይህ በራስ መተማመናቸው ከመጠን ሲያልፍ ልንጠቀምበት እንደምንችል ተነጋግረን ነበር። ሜዳ ላይም የተመለከትነው ይህንን ነው።

ቡድኑን ለማሳደግ ያደረገው ጥረት እና ጫናውን ለማላቀቅ ስለመሞከሩ?

ቡድኑ ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች ተስማምተውኛል። በተወሰነ መልኩ ወደ እኔ ሀሳብ ለመምጣት የሚቀራቸው ተጫዋቾች አሉ። አብዛኞቹ ወጣቶች ስለሆኑ በስራ የሚለወጡ ናቸው።

የዘንድሮ የቡድኑ እቅድ?

ወደ ቦታው ስመጣ የተሰጠኝ እቅድ ቡድኑን ከአደጋ ክልል አውጥቶ ተፎካካሪ ማድረግ የሚል ነው። ይሄንንም እያሳካነው ነው ብዬ አስባለው። ስለዚህ ጫና የሚፈጥር እቅድ አልተሰጠኝም።

ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ውጤት ስላላገኙበት ምክንያት?

መጀመሪያ እንደተናገርኩት የምንፈልገውን ነገር እናገኛለን የሚል ነበር አካሄዳችን። ሜዳ ላይ ድንገተኛ የሚፈጠሩት ስህተቶቻችን ነገሮችን ውስብስብ አድርጎብናል። ከእረፍት በኋላም የሚቻለውን ሁሉ አድርገን ወደ አሸናፊነት ለመምጣት ጥረት አድርገናል። ነገርግን አልተቻለም። ስለዚህ ቀጣዮቹን ጊዜዎች ማሰብ ነው የሚሻለው።

ውጤቱ ከዋንጫ ፉክክሩ እያሶጣችሁ ነው?

ያሶጣናል ብዬ ሙሉ ለሙሉ መደምደም ባልችልም ፈተናችንን ግን ከበድ ያደርገዋል። ከዚህ ተነስቶ እኔም ሆነ ተጫዋቾቼ ጋር ያለውን ጫና ከፍ ሊያደርግ ይችላል። ከጫና ወቶ ለመስተካከል የክለቡ፣ የደጋፊዎቹ፣ የእኛ እና የአመራሮቹ በአጠቃላይ የሁላችንም ህብረት እና ጥረት ይጠይቃል። ኳስ ጨዋታ ሂደት ነው። ይህንን ሂደት ለመለወጥ ሁሉም ሰው ከጎናችን እንዲሆን ነው የምጠይቀው። እያንዳንዱ ተጫዋች የሚሰማውን ነገር አውቃለው። በዚህ መልክ አልነበረም የመጣነው። በአሸናፊነት ለመውጣት ብዙ ጥረት ለማድረግ ነበር። ግን ሜዳ ላይ ባሰብነው መልክ አልሄደም። ስለዚህ ሁሉም ሰው ከጎናችን ሆኖ ቡድኑ የተሻለ እንዲሆን ድጋፉ አይለየን ነው የምለው።

በመጨረሻ ደቂቃ በሁለት አጥቂ ስለተጫወቱበት መንገድ?

የገቡት ተጫዋቾች የሰጠናቸው ሀላፊነት ነበር። ኦኪኪ ለምሳሌ ወደ መሐል እየመጣ ከአማካዩ ጋር እየተገናኘ እንዲሄድ ነበር ነገርግን እዛ ጋር ለመሆን ያደረገው ነገር ብዙ አልተመቸኝም። የሆነው ሆኖ ያየነውን ነገር ለማስተካከል ጥረት እናደርጋለን። በአጠቃላይ ቅያሪዎቹ ፊት ላይ ለማስተካከል ነበር። ባየነው መልኩ ግን አልተሳካም። የሚቀጥለውን ማሰቡ ይበጃል ብዬ አስባለው።