ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በምሽቱ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና በፍሬዘር ካሳ ድንቅ የግንባር ኳስ ከአራት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ወደ አሸናፊነት በመመለስ ደረጃውን ያሻሻለበትን ወሳኝ ድል አስመዝግቧል።

ባህር ዳር ከተማዎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ የስድስት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም አቡበከር ኑሪ ፣ ሰለሞን ወዴሳ ፣ መሳይ አገኘሁ ፣ ፍፁም ዓለሙ ፣ ዓሊ ሱሌይማን እና በረከት ጥጋቡን አስወጥትው በምትካቸው ፋሲል ገ/ሚካኤል ፣ አህመድ ረሺድ ፣ አለልኝ አዘነ ፣ ኦሲ ማውሊ እና ተመስገን ደረሰን ያስገቡ ሲሆን በአንፃሩ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ሁለት ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ሶሆሆ ሜንሳ እና ሳምሶን ጥላሁን ወጥተው በምትካቸው ያሬድ በቀለ እና ግርማ በቀለን አስገብተዋል።

ሁለት የተለያየ መልክ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ እንቅስቃሴ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ባህር ዳር ከተማዎች የተሻለ የነበሩ ሲሆን በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ግን ሀዲያ ሆሳዕና የተሻለው ቡድን ነበር። የባህር ዳር ከተማዎች አንፃራዊ የበላይነት በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ደቂቃዎች ባህር ዳር ከተማዎች ወደፊት በሚደረጉ ቅብብሎች በተደጋጋሚ የሀዲያ ሆሳዕናዎችን ሳጥን ለመጎብኘት ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል። ገና በ2ኛው ደቂቃ ላይ ባህርዳር ከተማዎች በረጅም ከራሳቸው የግብ ክልል የላኩትን ኳስ ወጣቱ ተከላካይ ቃለዓብ ውብሸት በአግባቡ መቆጣጠር አለመቻሉን ተከትሎ ኦሲ ማውሊ ያገኘውን ኳስ ከግራ የሳጥኑ ጠርዝ ወደ መሀል ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ተመስገን ደረሰ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ያሬድ በቀለ ባዳነበት ኳስ ነበር አጀማመራቸውን አድርገዋል።

በአጋማሹ ጫና ፈጥረው መንቀሳቀሳቸውን የቀጠሉት ባህርዳሮች በ11ኛው ደቂቃ ኦሲ ማውሊ ከሳጥን ውጪ ፣ 19ኛ ደቂቃ ፉአድ ፈረጃ እና አለልኝ አዘነ በግሩም ሁኔታ ያሳለፈለትን ኳስ ኦሲ ማውሊ ሳይጠቀምበት የቀረው እንዲሁም በ21ኛው ደቂቃ ላይ ፈቱዲን ጀማል በረጅሙ ወደ ቀኝ ካደላ ስፍራ ያሻማውን የቆመ ኳስ አለልኝ አዘነ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ኳስ እጅግ አደገኛ ሙከራዎች ነበሩ።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች በባህር ዳሮች እንቅስቃሴ መነሻነት ይበልጥ በአጋማሹ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ሸሽተው ሲጫወቱ የነበረ ሲሆን በተወሰኑ አጋጣሚዎች ግን ኳሶች ተቀባብሎ ለመውጣት ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል። በአጋማሹ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከ30ኛው ደቂቃ አንስቶ በነበሩ የተወሰኑ ደቂቃዎች ግን ጥሩ ቅፅበቶችን መፍጠር ችለዋል። ወደ ባህር ዳር ሳጥን ለመድረስ ተግረው ቢቆዩም በ30ኛው ደቂቃ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ሄኖክ አርፊጮ ከቀኝ የተሻማን ኳስ በደረቱ አብርዶ ቢሰጠውም የመታው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ በቀረ ኳስ የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል።

በ34ኛው ደቂቃ ላይ ግን ፋሲል ገ/ሚካኤል የሰራውን ስህተት ተከትሎ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ያገኙትን የማዕዘን ምት አበባየሁ ዮሀንስ በግሩም ሁኔታ ያሻማውን ኳስ ፍሬዘር ካሳ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ በኋላ እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ቀዳሚ መሆን የቻሉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ይበልጥ በመከላከል ሲጫወቱ ባህር ዳር ከተማዎች ደግሞ ወደፊት ገፍተው ለማጥቃት ጥረት አድርገዋል። በአጋማሹ የመጀመሪያ ደቂቃዎች በጉዳት ጨዋታውን መጀመር ያልቻለውን ፍፁም ዓለሙን እና አዲስ ፈራሚያቸውን አደም አባስን በመቀየር ግብ ፍለጋቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ባህርዳር ከተማዎች በ71ኛው ደቂቃ አደም አባስ ካደረጋት ሙከራ በዘለለ የተጠቀጠቀውን የሀዲያ ሆሳዕና መከላከል ለመስብር ተቸግረው ተመልክተናል።

በአጋማሹ በተለይ ተቀይሮ የገባው አደም አባስ በግሉ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲያደርገው ከነበረው ጥረት ባለፈ የባህር ዳር ከተማዎች የማጥቃት ፍላጎት ፍሬያማ መሆን ሳይችል ቀርቷል።

በአጋማሹ ከመከላከል ባለፈ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን አደጋ ለማድረስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ሀዲያዎች በ65ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል ያገኙትን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ ወደ ግብ ቢሞክርም ኳሷ የግቡን አግዳሚ ለትማ የተመለሰችበት እንዲሁም በ83ኛው ደቂቃ ፍሬዘር ካሳ ከቆመ ኳስ የተሻማን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት የሆሳዕናን መሪነት ማሳደግ የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ጨዋታው በሀዲያ ሆሳዕና የ1-0 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ነጥባቸውን ወደ 21 በማሳደግ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ ተሸናፊዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች ደግሞ በተመሳሳይ 21 ነጥብ ወደ 8ኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።