የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 0-1 ሀዲያ ሆሳዕና

የምሽቱ ጨዋታ በሀድያ ሆሳዕና አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለቱ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል
አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ጨዋታውን በታሰበው ልክ ስለመሄዱ

“ዛሬ ልጆቼ ከሌላው ቀን የተሻሉ ነበሩ። በተለይ በመጀመርያው አርባ አምስት ጨዋታውን ጨርሰን ሁለተኛው አርባ አምስት ላይ የታክቲክ ለውጥ አድርገን ውጤቱን ለመገልበጥ ነበር አቅደን የገባነው ይህንንም ልጆቹ ተግብረውታል። ነገር ግን ከዕረፍት በፊት ሦስት ያለቀለት ኳስ ወደ ጎልነት መቀየር አለመቻላችን ዋጋ አስከፍሎናል። በተረፈ ግን ጥሩ እንቅስቃሴ ለእኛም ለሀድያም ነበር ማለት እችላለው።

እንቅስቃሴን ወደ ውጤት ለመቀየር ስለመቸገር

“ትክክል ነው። በእኛ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ክለቦችም የሚታይ ነው። ሰሞኑን ስንሰራ የቆየነው ለምሳሌ በአዲስ አበባ ጨዋታ ብዙ የጎል ሙከራዎች አልነበሩም። ያንን አስተካክለን ነው ዛሬ የቀረብነው በተቻለ መጠን የተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሞክረናል ግን ወደ ግብ መቀየር አለመቻላችን ነው ዋጋ ያስከፈለን በቀጣዩ ጨዋታ አስተካክለን እንቀርባለን።

ስለተከታታይ የግብ ጠባቂዎች ስህተት

“ያው እኛ ጋር ያሉ ግብ ጠባቂዎች በአብዛኛው ወጣቶች ናቸው። ለወጣቶቹ ዕድል መስጠት የፈለግነው ለብሔራዊ ቡድን አስተዋፆኦ ለማድረግ ካለን ፍላጎት እንጂ ልክ እንደሌሎች ቡድኖች ልምድ ያላቸው ግብ ጠባቂዎች ማምጣት ይቻላል። እነዚህን ግብ ጠባቂዎች ከነስህተታቸው እየጠበቅን እያረምን ሥልጠና እየሰጠን መሄድ አለብን። የግብ ጠባቂ ችግር በሀገራችን መሠረታዊ ችግር ነው። በጣም የጎላ ችግር ባይፈጠርም ያሉብን ችግሮች እያረምን ልጆቹን እየተንከባከብን እየጠበቅን ልንሄድ ይገባል።

በመከላከል አደረጃጀት ስለተፈጠረው ክፍተት

“በመከላከል አደረጃጀታችን ብዙ ችግር አልነበረብንም። ግን አንዱ የነበረው ችግር ከቅጣት ምት ፣ ከማዕዘን ምት የሚላኩ ኳሶችን በአግባቡ መከላከል አለመቻላችን አንዱ የተከላካዮቻችን ክፍተት ነው። ይሄንንም እናስተካክላለን።”

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀድያ ሆሳዕና

ጨዋታውን እንደታቀደው ስለመሆኑ

“በሚገባ ያቀድነው ሦስት ነጥብ ነበር። አሁን ካለንበት ደረጃ ለመሻሻል ግዴታ ሦስት ነጥብ ስለሚያስፈልገን በአግባቡ አሳክተናል።

በአማካይ ክፍል ላይ ስለተወሰደባቸው ብልጫ

“በእርግጥ ብልጫ ለመውሰድ ፈልገናል ግን እነርሱ ይዘውት የመጡት አጨዋወት ከእኛ ተሽሎ ስለነበር ብልጫ ወስደዋል። አጋጣሚ ሆኖ ቀድመን ጎል አስቆጠርን የያዘውን አስጠብቀን መጨረስ ነበር የፈለግነው። መጀመርያም ግቤ ሦስት ነጥብ ስለነበር ተሳክቶልኛል። አሁን የሚያስፈልገው ሦስት ነጥብ ነው። እያዳበርን ደግሞ እያሻሻልን እንሄዳለን።

በጨዋታው በተቃራኒ ቡድን ትኩረት የተደረገባቸው ተጫዋቾች ስለመኖራቸው

“በፍፁም እኛ ፉአድንም ፍፁምንም ሌሎችንም ተጫዋቾች በአንድ ላይ እንደ ቡድን ማሸነፍ ያለብን በምድነው እንጂ አንድ ተጫዋች ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን አይደለም። በሌሎች በቡድን አንድነት እንደ ቡድን ተጫውተን ነው ያሸነፍነው። የሚያሳየውም እርሱን ስለሆነ የተለየ ለግለሰብ ያቀድነው ነገር የለም።

በወጣት ላይ ስላለው ዕምነት

“በእርግጥ መጀመርያ ሲመለመሉ ይሄን ሊግ ቀድመን ስለምናቀው መጫወት ይችላሉ ብለን አስበን ነው። እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም አሉ። አጋጣሚ ወጣቶች ስለሆኑ በተሰጣቸው ዕድል አንዳንዱ ቀድሞ ተረድቶ የምትፈልገውን የሚያደርግ አለ እነዚህ ልጆች ግን ቀድመው ተረድተው እያደረጉልኝ ነው። መጀመርያም ሲያዙ ዕምነቱ ነበረኝ ለዛ ነው የማጫውታቸው።”