ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ምህዳሩን በማስፋት ለደቡብ ሱዳኑ ቡድን ትጥቅ ለማቅረብ ስምምነት ፈፅሟል።
መቀመጫውን በጁባ ከተማ ያደረገው የደቡብ ሱዳኑ ማለኪያ ሶሻልና ባህላዊ ቡድን ኢትዮጵያ ከሚገኘው ትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሪ ጋር የሦስት አመት ስምምነት ዛሬ ከሰዓት ተፈራርሟል። ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ ውጭ ምርታቸውን ማሻገር የቻሉት ጎፈሬዎችን ወክለው ባለቤቱ አቶ ሳሙኤል መኮንን ሲገኙ ከማለኪያ ሶሻልና ባህላዊ ቡድን ደግሞ ጆሴፍ ሳሙኤል ቦሌ በሚገኘው የጎፈሬ ዋና ቢሮ ተገኝው የስምምነት ፊርማ አኑረዋል።
ስምምነቱን በተመለከተ በቅድሚያ ማብራራያ የሰጡት አቶ ሳሙኤል ስምምነቱ ለሦስት ዓመት የተደረገ መሆኑን ገልፀው በአመት ለቡድኑ እስከ 10,000 ማልያ ለሽያጭ የሚቀርቡ መሆኑን እና በዚህም እስከ $50,000 ማግኘት እንደሚችሉ አመላክተዋል። አቶ ሳሙኤል ይህም ሀገራችን ለገባችበት የምንዛሬ ችግር የበኩሉን መፍትሔ እንደሚያበረክት ገልፀው ለድርጅታቸውም ደግሞ አንድ እርምጃ ወደፊት ማራመድ የሚስችል ስምምነት መሆኑን ገልፀዋል። የጎፈሬ ባለቤት የማልያው ቁጥሩ በየአመቱ ሊጨምር የሚችል መሆኑንን በስምምነቱ እንደተካተተ ጨምረው ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይ የደቡብ ሱዳኑ ማለኪያ ሶሻልና ባህላዊ ቡድን ሀላፊ ጆሴፍ ሳሙኤል እንዳሉት በስምምነቱ እጅግ ደስተኛ እንደሆኑ እና ኢትዮጵያ ሁለተኛ ቤታቸው እንደሆነ ገልፀው ትናንት የተደረገውን የሸገር ደርቢ እንደተመለከቱ ቡድናቸው ጠንካራ እንደሆነ እንዳሰቡ እና በቀጣይ መጥተው የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚጫወቱ ቃል ገብተዋል። ከጎፈሪ ጋር ያደረጉት ስምምነት በእግር ኳሱ ብቻ የሚወሰን ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ማለኪያ ስፖርት ቡድን ያሉትን የቮሊ ቦል፣ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን፣ የቅርጫት ኳስ እና የቦክስ ስፖርት ቡድን ሊያካትት እንደሚችል ገልፀዋል። ይህ ስምምነት የትጥቅ ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊያን እርስ በእርስ እንድንገናኝ የሚደርግ ሲሆን ስምምነቱ በትጥቅ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን እንደ ስካርቭ እና ቦርሳ የመሳሰሉት የተለያዩ ቁስቁሶች ያካተተ ነው ብለዋል።
በስተመጨረሻ የጎፈሪ ስራ አስኪያጅ እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል ስምምነቱ በየአመቱ የሚለዋወጥ እንደሆነ ተናግረው ጎፈሪ ማሸነፍ ልማድ ነው በሚል መፈክሩ አሁንም ወደ ፊት ይጓዛል ካሉ በኋላ በቀጣይም ሌላ ስምምነት ይፋ የምናደርግ ይሆናል ብለው ጥቆማ ሰጥተዋል።