ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

በአስር ነጥቦች ተለያይተው የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና የሚያደርጉትን የነገ ፍልሚያ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው 18 ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ያሳኩት ድሬዳዋ ከተማዎች የናፈቃቸውን ሦስት ነጥብ ለማግኘት በነገው ጨዋት እንደሚጥሩ ሲታሰብ በተቃራኒው ያለፉትን ዘጠኝ ጨዋታዎች አንድም ሽንፈት ያላስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት የሚያደርጉትን ጉዞ ለማጠናከር ወደ ሜዳ መግባታቸው እሙን ነው።

በሁለተኛው ዙር አሠልጣኝ ሳምሶን አየለን ሾመው ወደ ውድድር የገቡት ድሬዎች በእንቅስቃሴ ደረጃ መጠነኛ መሻሻል ቢያሳዩም በመጀመሪያው ዙር የነበረባቸውን ክፍተት አሁንም እንዳላረሙ በወላይታ ድቻው ጨዋታ በሚገባ አስተውለናል። በ16 ሳምንታት ጨዋታዎች ሦስት አሠልጣኞችን እና 27 ተጫዋቾችን የቀያየረው ቡድኑ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ህመም ያለበት ይመስላል። ከሁሉም የባሰው ክፍተቱ ደግሞ የአማካይ እና የአጥቂ መስመሩን የሚያገኛኝ ተጫዋች ማጣቱ ነው። በድቻው ፍልሚያ 59% የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በመያዝ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርጉም የግብ ዕድል መፍጠሪያ የመጨረሻ ኳሶችን ለአጥቂዎች የሚልክ ሁነኛ ሰው ባለመኖሩ ሲቸገሩ ነበር። ጭራሽ ችምችም ብሎ የሚከላከለውን ድቻን ማስከፈት ከባድ መሆኑ እየታወቀ ሦስት ተመሳሳይ የአጨዋወት ባህሪ ያላቸው (ለተከላካይ አማካይነት የቀረበ) አማካዮችን አጣምረው ጨዋታውን መቅረባቸው በላይኛው ሜዳ ጥራት እንዳይኖረው እና የኳስ ቁጥጥሩ ለኳስ ቅጥጥር ብቻ እንዲሆን አድርጓል። በጨዋታውም ሁለት ብቻ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገው ከሜዳ ወጥተዋል። በንፅፅር የቀኝ መስመር ተከላካዩ እንየው ካሣሁን እንዲሁም አዲሱ ፈራሚ አማረ በቀለ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ወደ ሳጥን ሲልኩ ነበር። በነገውም ጨዋታ አጥቦ የሚጫወተውን የሲዳማ ስልት ለመፈተን በሁለቱ መስመሮች ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀሳቸው አይቀርም።

በሁሉም የጨዋታ ምዕራፎች ጠንካራ የሚመስለው ሲዳማ ቡና በበኩሉ ወቅታዊ ብቃቱ ምርጥ ነው። ከላይ እንደገለፅነውም በ7ኛው ሳምንት በፋሲል ከነማ ከደረሰባቸው አሰቃቂ ሽንፈት በኋላ ሦስት ነጥብ ተነጥቀው አያውቁም። በመጨረሻ ጨዋታቸው በቡና ስም ከሚጠራው ሌላኛው ክለብ ጋር አቻ ሲለያዩም ጥሩ ተንቀሳቅሰው ነበር። እርግጥ በኳስ ቁጥጥሩ ከፍተኛ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ቡና ኳስ ይዞ ወጥመድ ውስጥ ሲገባላቸው በፈጣን ሽግግር የሜዳውን ስፋት እና ጥልቀት በመጠቀም ጥቃት ለመሰንዘር ይሞክሩ ነበር። ቡድኑ በከፍተኛ ግብ አስቆጠቀሪነት የሚፎካከር አጥቂ ቢኖረውም የሥልነት ችግር ይታይበታል። እንዳልነው ይገዙ ጥሩ አበርክቶ ለቡድኑ ቢኖረውም ከእሱ በላይ የተሻለ አጥቂ ቢኖር የተሻለ ግቦችን ያገኝ ነበር። በጨዋታውም አንድ ጎል ከጨዋታ ውጪ በሚል ቢሻርባቸውም በፈጣን ሽግግር የፈጠሯቸው ዕድሎች ግብ ብቻ ሳይሆን ግቦችን አግኝተው እንዲወጡ የሚያስችሉ ነበሩ። በነገው ጨዋታም ድሬዳዋ ከተማ የኳስ ብልጫ ለመውሰድ ፍላጎት ማሳየቱ ስለማይቀር ተመሳሳይ አጨዋወት በመከተል ድል ለማግኘት መታተራቸው የማይቀር ይመስላል። በዋናነት ደግሞ የመጨረሻ ኳሶችን በማመቻቸት ድንቅ የሆኑት ፍሬው ሰለሞን እና ዳዊት ተፈራ ዘግየት ያሉ ሩጫዎችን በፍፁም ቅጣት ምት ክልሉ በማድረግ የሚፈጥሩት አማራጭ ለድሬ ተከላካዮች ፈተና የሚሰጥ ነው።

ሰባት ሰባት ግብ አስቆጣሪ ተጫዋቾች ያሏቸው ሁለቱ ቡድኖች በየመንገዳቸው የነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ እጅግ ያስፈልጋቸዋል። በደረጃ ሰንጠረዡ የወራጅ ቀጠና በአንድ ደረጃ እና ነጥብ ብቻ ከፍ ብለው የሚገኙት ድሬዎች ከአስጊው ቀጠና ፈቅ ለማለት ማጥቃት ላይ የተመረኮዘ አጨዋወት መከተላቸው የማይቀር ሲሆን ሲዳማ ቡናም የወቅቱን የሊጉ አሸናፊ ፋሲል ከነማ ደረጃ ለመረከብ እና ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለውን ልዩነት እያጠበቡ ለመምጣት ድል ተኮር አጨዋወት መከተሉ አይቀርም። ይህንን ተከትሎ ጨዋታው ክፍት እና ከሳጥን ሳጥን የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ሊኖርበት እንደሚችል ይገመታል።

ድሬዳዋ ከተማ በነገው ጨዋታ ወጣቱን ተከላካይ ሚኪያስ ካሣሁንን ብቻ በጉዳት የማያገኝ ሲሆን ሲዳማ ቡና ግን ምንም የቅጣት እና የጉዳት ዜና የለበትም። አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌም የውድድር አጋማሹ ትልቁ ፈራሚያቸው የሆነውን ሳልዓዲን ሰዒድን መጠቀም እንደሚችሉም ተጠቁሟል።

9 ሰዓት የሚጀምረውን ጨዋታ ዮናስ ካሣሁን ከረዳታቸው ሸዋንግዛው ተባበል እና ሻረው ጌታቸው እንዲሁም ከአራተኛ ዳኛው ሚካኤል ጣዕመ ጋር በመሆን እንደሚመሩት ታውቋል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና እስካሁን በሊጉ አስራ ሰባት ጊዜ ተገናኝተዋል። ከእነዚህ ግንኙነቶች ሲዳማ ቡና ዘጠኙን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሁለት ጊዜ ብቻ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ ረቷል። ቀሪዎቹ ስድስት የእርስ በርስ ግንኙነት በበኩላቸው በአቻ ውጤት ተፈፅመዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-3-3)

ፍሬው ጌታሁን

እንየው ካሣሁን – መሳይ ጻውሎስ – አውዱ ናፊዩ – አማረ በቀለ

አቤል ከበደ – ዳንኤል ደምሴ – ብሩክ ቃልቦሬ

አብዱረህማን ሙባረክ – ማማዱ ሲዲቤ – አብዱለጢፍ መሐመድ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ተክለማርያም ሻንቆ

ደግፌ ዓለሙ – ጊት ጋትኩት – ያኩቡ መሐመድ – መሐሪ መና

ዳዊት ተፈራ – ሙሉዓለም መስፍን – ፍሬው ሰለሞን

ብሩክ ሙሉጌታ – ይገዙ ቦጋለ – ሀብታሙ ገዛኸኝ