ቅድመ ዳሰሳ | አርባምንጭ ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከነገ የሊጉ ጨዋታዎች ውስጥ ሁለተኛው የሚሆነውን ጨዋታ በዳሰሳችን ቃኝተነዋል።

ነገ ምሽት የሚደረገው ይህ ጨዋታ በሊጉ የሰንጠረዥ ወገብ በታች ባሉ ደረጃዎች ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ነው። እስከ ሰባተኛ ደረጃ ከፍ የማለት ዕድልን ይዘው የሚገቡት አርባምንጮች ከወራጅ ቀጠናው መራቅ ዋና አላማቸው ነው። በቀጠናው ውስጥ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ ግን የዚህ ጨዋታ ውጤት ይበልጥ ያስፈልገዋል። ቦታውን ለድሬዳዋ አስረክቦ ቀና ለማለት አርባምንጭን የመርታት ፈተና የሚጠብቀው የመዲናዋ ክለብም ይሁን አርባምንጭ በመጨረሻ አምስት ጨዋታዎቻቸው አንድ ድል ብቻ ማሳካታቸው ያመሳስላቸዋል።

ካደረጋቸው 16 ጨዋታዎች አስሩን በአቻ ውጤት ያጠናቀቀው አርባምንጭ ከተማ አሁንም በመከላከል ጥንካሬው ላይ ተመስርቶ ሽንፈትን ማስወገድ መቻሉ በሰንጠረዡ ይበልጥ እንዳይንሸራተት የረዳው ይመስላል። ወደ ራስ ሜዳ ተስቦ ለተጋጣሚ ክፍተት ባለመስጠት ለረጅም ደቂቃዎች መጫወት የሚያውቁበት አዞዎቹ የማጥቃት ሂደታቸው እና የፊት መስመራቸው ስልነት ግን ከኋላ ካለው ጥንካሬ ጋር የሚመጣጠን አልሆነም።

ለዚህም በመጨረሻው ጨዋታ አዲስ ፈራሚው አህመድ ሁሴንን ወደ አሰላለፍ በማምጣት ፊት ላይ ከሀቢብ ከማል ጋር በማጣመር እና እስካሁን ሲገለገሉበት የነበረው 4-4-2ን ወደ 3-5-2 በመቀየር ፊት ላይ በተሻለ ቁጥር ለማጥቃት ሞክረዋል። ሆኖም ማስተካከያዎቹ የታሰቡትን ጎሎች አላመጡም። በእርግጥም ቡድኑ የኋላውን ጥንካሬ ሳይቀንስ የሚያስቆጥረውን የግብ መጠን ለመጨመር የሚያደርገው ጥረት ስኬት ጊዜ የሚወስድ ይመስላል። ይሁን እንጂ በነገውም ጨዋታ በተሻለ ድፍረት የመስመር ተመላላሾቹን ወደፊት የሚገፋ በቀጥተኛ እና ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ለማጥቃት የሚሞክር አርባምንጭ ከተማ ይጠበቃል።

አዲስ አበባ ከተማ የኋላ መስመር ጥንካሬው እና አጠቃላይ የመከላከል አደረጃጀቱ በነገው ተጋጣሚው ልክ ባይሆንም ወደ ግብ የመድረስ ስኬቱ ግን በርቀት የተሻለ ነው። በቅርብ ጨዋታዎች እየታየ ያለበት ችግር የፊት መስመር ተጫዋቾቹ ጊዜውን ያልጠበቀ እና በስሜት የሚደረግ ውሳኔ ነው። የፍፁም ፣ ሪችሞንድ እና እንዳለ ጥምረት ተመስርተው ለሚመጡም ሆነ በቀጥታ ለሚላኩ ካሶች የተመቸ ይመስላል። ነገር ግን ተጫዋቾች የመጨረሻ የግብ ዕድል ተፈጥሮላቸው በሳጥን ውስጥ ሲገኙ በጥራት የመጨረስ ወይንም የተሻለ ቦታ ላይ ለሚገኝ ለጓደኛ አመቻችቶ የማቀበል አማራጮችን የሚወስኑበት መንገድ ተዛብቶ እየተመለከትን ነው።

ይህ ከጉጉት ጋር የሚያያዝ ቢሆንም እንደ ባህር ዳሩ ጨዋታ በርካታ ዕድልን በማይሰጠው አርባምንጭ ሳጥን ውስጥ የግብ ዕድሎችን ለፍሬ የማብቃት ስኬታቸው እጅግ መሻሻል ይኖርበታል። ከዚህ አንፃር አሰልጣኙ ፊታቸውን ወደ ሌሎች አማራጮች ሊያዞሩ ሲችሉ አዲስ ፈራሚው እና ተቀይሮ በመግባት ጥሩ የተንቀሳቀሰው መሀመድ አበራ ሌላኛው አዲስ የማጥቃት መሳሪያቸው ይሆናል ተብሎ ይገመታል። በተጨማሪነትም ግን የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎቹ ክፍተት ለማግኘት በሚፈተኑነት የነገው ጨዋታ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ግብ ማስቆጠርም ይጠበቅባቸዋል።

በነገው ጨዋታ የአዲስ አበባ ከተማው አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከቅጣት መልስ ቡድኑን እንደሚያገለግል ሲጠበቅ የሸዋስ በለው እና ሳዲቅ ተማም ጉዳት ላይ ይገኛሉ። በአርባምንጭ በተማ በኩሉ የጉዳት እና ቅጣት ዜና እንደሌለ ሰምተናል ።

ይህንን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የሚመሩት ባህሩ ተካ ሲሆኑ ኢያሱ ካሳሁን እና ባደታ ገብሬ በረዳትነት ኤፍሬም ደበሌ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በእስካሁኑ ሦስት ግንኙነታቸው አርባምንጭ ከተማ ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናው አንዴ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ አርባምንጭ ስድስት አዲስ አበባ ደግሞ ሦስት ግቦችን አስመዝግበዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል ተሾመ

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ዘሪሁን አንሼቦ – ኢያሱ ለገሰ – ሳሙኤል አስፈሪ

ሙሉቀን አዲሱ – ቻርለስ ሪባኑ – ኤሊያስ አህመድ

እንዳለ ከበደ – መሀመድ አበራ – ፍፁም ጥላሁን

አርባምንጭ ከተማ (3-5-2)

ሳምሶን አሰፋ

ወርቅይታደል አበበ – በርናንድ ኦቼንግ – አሸናፊ ፊዳ

ሙና በቀለ – አቡበከር ሸሚል – እንዳልካቸው መስፍን – አንዷለም አስናቀ – ፀጋዬ አበራ

አህመድ ሁሴን – ሀቢብ ከማል