ወደ ከፍተኛ ሊጉ ለማደግ አስራ ስድስት ቡድኖች የሚያሳትፈው የ2014 የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር የሚደረግበት ከተማ እና ቀን ይፋ ሆኗል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አወዳዳሪነት የሚከናወነው የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን በሰላሳ አምስት ክለቦች መካከል በሦስት ምድብ ተከፍሎ በስድስት ከተሞች ከታህሳስ 8 ጀምሮ ሲደረግ የነበረ ሲሆን የምድብ ጨዋታዎችም በያዝነው ሳምንት መጨረሻ መጋቢት 29 ይጠናቀቃሉ፡፡ የአንደኛው ዙር ውድድር በሶዶ ፣ ቡራዩ እና አሰላ ከተሞች ሲደረግ የነበረ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ደግሞ በቢሾፍቱ ፣ ወልቂጤ እና አሰላ ከተሞች ናቸው ሲደረጉ የሰነበቱት፡፡
በቀጣይ ከየምድቦቹ የሚያልፉ በጥቅሉ አስራ ስድስት ክለቦችን አሳትፎ ስድስቱን ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚያሳልፈው የማጠቃለያ ውድድር በድሬዳዋ ከተማ አስተናጋጅነት ከሚያዝያ 29 ጀምሮ እንዲደረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አሳውቋል፡፡ እስከ አሁን ከምድብ ሀ አራዳ ክፍለ ከተማ ፣ ቡሌ ሆራ እና ድሬዳዋ ፓሊስ ፣ ዱከም ከተማ እና ቦዲቲ ከተማ ያለፉ አምስቱ ክለቦች ናቸው፡፡ከምድብ ለ ጅንካ ከተማ የምድቡ ቻምፒዮን በመሆን ሲያልፍ ሆለታ ከተማ እና ሐረር ከተማም በደረጃ ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመሆን ማለፋቸው ሲረጋገጥ ቀሪ ሁለት አላፊ ክለቦች በነገው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ላይ ይለያሉ፡፡
ከምድብ ሐ አረካ ከተማ ፣ ሮቤ ከተማ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሲያልፉ ሁለት የቀሩ ቡድኖች ሐሙስ እና ዓርብ በሚደረጉ ጨዋታዎች የሚለዩ ይሆናል፡፡ እስከ አሁን አስራ አንድ ክለቦች ሲታወቁ ቀሪ አምስቱ በያዝነው ሳምንት ከተለዩ በኋላ ከሦስቱ ምድብ የተሻለ ነጥብን ይዞ ስድስተኛ ደረጃ ያጠናቀቀ አንድ ጥሩ ቡድን ወደ ማጠቃለያው ይሻገራል፡፡