ከሃያ ወራት በፊት በዚሁ አምድ ላይ ስለ ትግል ፍሬ ቡድን የግል ትዝታዬን አጋርቻችሁ ነበር፡፡ ትግል ፍሬ ልጅነቴን ያጣፈጠልኝ፣ በወርቃማው የአገሪቱ እግርኳስ ዘመን አንጋፋውን የአዲስ አበባ ስታዲየም የሁለተኛ ቤቴ ያህል እንዳደርግ የስቻለኝ፣ የጽኑ ደጋፊነትን ጸጋ ያደለኝ፣ በርካታ ወዳጆች ያፈራልኝ፣ ለጉልምስናዬ ተነግሮ የማያልቅ ትውስታዎች ያስቀመጠልኝ፣…..ቡድን ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር ይህ በ1970ዎቹ መባቻ ጎምርቶ በዚያው አስርት እኩሌታ የከሰመው ትግልፍሬ ባለውለታዬ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ባቀረብኹት የትግል ፍሬ ትዝታዬ ያላነሳኋቸውን አንዳንድ ነጥቦች በዚህኛው ክፍል ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡
ይኸው፦
በእግርኳስ ተመልካችነት ህይወቴ እጅጉን በቅርብ ሆኜ የተከታተልኹት፣ በጣምም ወድጄ የደገፍኩት ቡድን ቢኖር የትግል ፍሬ እግርኳስ ቡድን ነው። የያኔው ትግል ፍሬ በአካል ብቃቱ- ጠንካራ የሆኑ፣ በአልሸነፍ-ባይ ወኔ የዳበረ ስነ-ልቦና ያላቸው፣ በቡድን ሥራ ከፍተኛ መግባባትና ውህደት ላይ የደረሱ ተጫዋቾች የሞሉበት፥ በቴክኒካዊ ክህሎት ከፍተኛ አድናቆት ያተረፉ፣ በመልካም ሥነምግባራቸው የተወደዱና የተከበሩ የምርጥ ስብዕና ባለቤት የሆኑ ሰዎች የገነቡት ቡድን ነበር። ትግል ፍሬ በሁለት ቡድኖች የተዋቀረ አደረጃጀት ነበረው፡፡ በአወቃቀር ተዋረዱ ቀደሚውን ስፍራ ስለሚይዘው እና የ1972ቱን የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ድል ስለተጎናጸፈው ቡድን ትዝታዬን ስለማጋራቴ መግቢያዬ ላይ ጠቀሻለሁ፡፡ ዛሬ ስለ ሁለተኛው ቡድን አወሳለሁ፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስፖርትን ለብዙሃኑ የማዳረስ ተልዕኮ በሚል መነሻ ምክንያት በ1971 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስንና ሌሎች ህዝባዊ መሠረት የነበራቸውን ቡድኖች ሲያፈርስ በምትካቸው የመጡት በርካታ ቡድኖች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ትግል ፍሬ አንዱ ነው። ( የያኔውን አዲስ የቡድኖች አመሠራረት አንድ ቀን ሰፋ አድርጌ መፃፌ አይቀርም። በቅርቡም ሊሆን ይችላል፡፡)
የትግል ፍሬ ተጫዋቾች የተመረጡት በተለያዩ ፋብሪካዎች፣ ህንፃ ኮንስትራክሽን እና አውራ ጎዳና ያገለግሉና ለቡድኖቹም ይጫወቱ ከነበሩ ሰራተኞች ነበር። የትግል ፍሬ ሁለተኛው ቡድን በአንደኛው ቡድን ውስጥ መጫወት የሚያስችል ልዩ ብቃት የያዙ ምርጥ ተጫዋቾች ነበሩት። የሁለተኛ ቡድኖች ውድድር ይደረግ የነበረው በአባሲዮን ሜዳ (ጉለሌ አካባቢ የሚገኘው)፣ ሲ ሜዳ (ስታዲየም- ግዮን ሆቴል ፊትለፊት)፣ ቫርኔሮ ሜዳ ()፣ አንዳንዴም በዋናው ስታዲዮም ውስጥና በናዝሬት አዳማ ስታዲዮም ውስጥ ነበረ። ውድድሩ የተጀመረው በ1971 ሲሆን የመጀመሪያው የውድድሩ አሸናፊ ሸዋ ፖሊስ የነበረ ይመስለኛል፡፡ ተከታዮቹን ዋንጫዎች በ1972-በድጋሚ ሸዋ ፖሊስ፣ በ1973-ከፍተኛ 6፣ በ1974-አየር ሃይል አሸንፈውታል። እኔ ወደ ትግል ፍሬን በቅርብ የመከታተል እድል ያገኘሁት ፥ ውድድሩንም በደንብ መከታተል የጀመርኩት ከ1972 ጀምሮ ነው።
በ1972 የተደረጉት የሁለተኛ ቡድኖች ጨዋታዎችን በሙሉ ለመታደም ችያለሁ። የቡድኑን መለያ የምንይዘውና የተጫዋቾች ትጥቅ ማንገቢያ ቦርሳ የምንጠብቀው አብሮ አደግ ጓደኛዬ ኢሳይያስ እና እኔ ስለነበርን ቡድኑ በሚሄድባቸው ሁሉም ቦታዎች መገኘት ይኖርብናል፡፡ መቅረት የማይታሰብ ነው፡፡ በእርግጥ ለእኛ ይህ ሁኔታ የሚፈጥርብን ደስታ ቃላት የሚገልጸው አይደለም፡፡ መታደል ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ቡድኑ ልምምድ ይሠራ የነበረው በቫርኔሮ ሜዳ (ኮሪያዎች ሆስፒታል አካባቢ) ነበር፡፡ የቡድኑ አለቆች ከጉምሩክ መኪና ተራ (ናዝሬት መኪና ተራ) በሚከራዩት የእቃ መጫኛ መኪናም ሆነ በኋላ ሁኔታዎች ተስተካክለው በመጡት የመኢሠማ (የመላው ኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር) ላንደሮቨሮች ለእኛ የሚሆን ቦታ አይጠፋም ነበር።
በልምምድ ሥፍራ የቡድኑ አሰልጣኞች የነበሩት ጋሽ ታደሰ ገብረመድህን፣ በኋላም አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ (ጎራዴው) ዋናውን ቡድን ከሁለተኛው ቡድን ጋር ያጋጥሟቸዋል። እነዚህ ግጥሚያዎች የፍልሚያ ይዘት ነበራቸው፡፡ ጨዋታዎቹ በጣም ከፍተኛ ፉክክር የሚታይባቸው ሲሆኑ አሸናፊውን መለየት እስከሚያስቸግር ድረስ እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ ይደረግባቸዋል፡፡ የሁለቱም ቡድኖች ተፋላሚነት በዋነኞቹ ውድድሮች ላይ ጎልቶ ታይቷል፡፡ በ1972 – ዋናው ቡድን – ለኢትዮጵያ ሻምፒዮና፣ ሁለተኛው ቡድን- ደግሞ በሚወዳደርበት ዲቪዚዮን ለፍጻሜ ማለፍ ችለዋል። የፉክክሩ ፍሬ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
የትግል ፍሬ ሁለተኛው ቡድን በአስደሳች አቀራረቡ የተመልካችን ስሜት ሰቅዞ እየያዘ፣ በማራኪ ጨዋታው የታዳሚውን ጥም እያረካ፣ በአሸናፊ ሥነ-ልቦና የደጋፊዎቹን አንጀት እያራሰ ጠንካራውን የ1972 የዲቪዚዮን ወድድር ረዥም ርቀት መጓዝ ችሏል፡፡ በውድድሩ መጨረሻም እጅጉን ፈታኝ በነበረውና በግማሽ-ፍጻሜው ጨዋታ ከሌላኛው የጊዜው ምርጥ ቡድን <ከፍተኛ-6> ጋር ከባድ ፍልሚያ የማድረግ ዕጣ ገጠመው። ፍልሚያው የተከናወነው በቫርኔሮ ሜዳ ሲሆን በጨዋታው ከፍተኛ-6 ቀድሞ አግብቶ ለበርካታ ደቂቃዎች ቢመራም የትግል ፍሬው መኮንን ሮባ የአቻነቷን ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በዛ ውጤት የሚያልቅ በሚመስልበት ሁኔታ አስተማማኙ የትግል ፍሬ ግብ አግቢ ብርሃኑ ዋቅጅራ ባለቀ ሰአት የድል ጎል አግብቶ ቡድኑን ወደ ፍጻሜ እንዲያልፍ አድርጓል።
የፍጻሜው ጨዋታ የተደረገው ናዝሬት-አዳማ ስታዲዮም ነበር። ተጋጣሚውም ከላይ እንደጠቀስኹት የቀዳሚው ውድድር አሸናፊ ሸዋ ፖሊስ፡፡ በፍጻሜው ጨዋታ ሸዋ ፖሊስ ቀድሞ የማግባት አጋጣሚ ስለፈጠረ በሩን በመዝጋት ወጤቱን ማስጠበቅ ታክቲካዊ ግቡ አደረገ፡፡ የግብ ክልሉን ድርግም አድርጎ ዘግቶ ማሸነፉን ሊያሳውጅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ልማደኛው ጎል አነፍናፊ ብርሃኑ ዋቅጅራ ለትግል ፍሬ እስትንፋስ የምትመልስ ግሩም ግብ አስቆጥሮ የፍጻሜውን ፍልሚያ በዘጠና ደቂቃዎች ብቻ ከመፈጸም ታደገ፡፡ ስለዚህም ጨዋታው በተጨማሪ ሰአት እንዲቀጥል ሆነ፡፡ በተጨማሪው ሰአት ሁለቱም ቡድኖች ግብ ማስቆጠር ስላልቻሉ ጨዋታው በመለያ ፍጹም ቅጣት ምቶች መገባደድ ነበረበት፡፡ በአምስት-አምስት ፍፁም ቅጣት ምቶቹ መለያያ እድል ከሸዋ ፖሊስ ጋር ነበረችና እነርሱ አሸንፈው ዋንጫውን ወሰዱ። ለእኔ በጣም ካዘንኩባቸው ቀናት ያ ቀን አንዱ ነው። ከናዝሬት ወደ አዲስ አበባ እስክንመጣ ድረስ አንዲትም ቃል የተነፈስኹ አይመስለኝም። ሁሉም በጣሙን ተከፍቶ ስለነበር አውቶቡስ ውስጥ የሚያወራ አንድም ሰው አልነበረም።
ያ ዕለት ወደ ኋላ ብዙ አስጉዞ አንድን የጨዋታ ድባብ ብቻ አስታውሶኝ አያልፍም፡፡ በአዕምሮዬ የኖሩና የሚኖሩ ብዙ ወዳጆቼን ወንድማዊ ምስል ይከስትልኛል፡፡ ናፍቆቴንና ናፍቆታቸውን ያመላልስብኛል፡፡ ከትዝታዬ ማህደር ያኖርኋቸውን ጣፋጭ ጊዜያት ይቆነጥርልኛል፡፡ እንደ ታናሽ ወንድማቸው የሚያዩኝ፣ የሚንከባከቡኝ፣ በሄዱበት ሁሉ የሚወስዱኝ የትግል ፍሬን ተጫዋቾች ፍቅር ያሳየኛል፡፡ እነርሱ ልጅነቴን አሳምረውልኛልና ሁሌም አመሰግናቸዋለሁ። ከአንዳንዶቹ ጋር አሁንም እገናኛለሁ። ከወንድ ወሰን ስለሺ እና ከብርሃኑ ዋቅጅራ ጋር በአካል ተገናኝተናል፤ አሁንም አልፎ-አልፎ እንገናኛለን። ከባይሳ በቀለ ጋር በፌስቡክ መልዕክት እንለዋወጣለን። በህይወት ያሉትን ረጅም እድሜ ከሙሉ ጤና ጋር ይስጥልኝ! ያለፉትን ደግሞ እግዚአሄር አምላክ ነፍሰቸውን በገነት ያኑርልኝ።
ስለ ፀሃፊው
ጸሃፊው በአዲስ አበባ ስታዲዮም አካባቢ ያደገና ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ የተደረጉ የዚያን ዘመን የሃገራችን እግርኳስ ጨዋታዎችን በአካል ተገኝቶ የተመለከተ፣ የጨዋታዎቹን አጠቃላይ ገጽታዎች በጥልቀትና በስፋት የሚያስታውስ እግርኳስ አፍቃሪ ነው፡፡ ከ1981 ዓ.ም በኋላ ነዋሪነቱን በአሜሪካ አገር ቢያደርግም አሁንም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሃገሩን እግር ኳስ ከመከታተል ወደ ኋላ ብሎ አያውቅም፡፡
የኤርሚያስ ብርሃነ የግርጌ ማስታወሻ
(ለጽሁፉ የተጠቀምኩባቸውን ፎቶ የሰጠኝ ብርሃኑ ዋቅጅራ ነው። ብሬ-በጣም አመሰግናለሁ!) በነገራችን ላይ በፎቶዎቹ ላይ የተጫዋቾቹን ስም የፃፍኩት እኔው ነኝ። ከአንድ ተጫዋች በስተቀር የሁሉንም ስም አስታውሻለሁ። የብዙዎቹን እስከ አባታቸው አስታውሼ ጽፌዋለሁ። የአንደኛውን ስም ግን እርግጠኛ ልሆን አልቻልኩም። በመጀመሪያው ፎቶ ላይ ያለው የተጠባባቂው ግብ ጠባቂ ስም “ወርቅአለማሁ” ወይም “ወርቅአፈራሁ” ይመስለኛል። የሚያስታውሰው ካለ ቢያርመኝ በደስታ እቀበላለሁ።