ሪፖርት | ድሬዳዋ እና ሲዳማ የሳምንቱን የመጀመሪያ አቻ አስመዝግበዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ያለግብ ተለያይተዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከወላይታ ድቻው ሽንፈት አማረ በቀለን በአብዱለጢፍ መሀመድ ፣ ዳንኤል ኃይሉን በብሩክ አሰበ እንዲሁም ሙኸዲን ሙሳን በአቤል ከበደ በመተካት በ4-2-3-1 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምሯል። አማካይ ክፍል ላይ ሙሉዓለም መስፍንን ብርሀኑ አሻሞ የተካው ሲዳማ ቡና ደግሞ በ4-3-3 ወደ ሜዳ ገብቷል።

ጨዋታው በጀመረበት ቅፅበት ሁለቱም ወደ ፊት የመሄድ ፍላጎታቸውን የሚያሳዩ እንቅስቃሴዎች ተስተውለናል። ድሬዳዋ ከተማዎች በተሻለ ሁኔታ ኳስ በመቆጣጠር ከሁለቱ መስመሮች አቅጣጫ በመነሳት ጥቃቶችን ለመሰንዘር ቢችሉም ዛሬም ሰብሮ የመግባት ነገር ከብዷቸው ታይቷል። ያም ቢሆን ቡድኑ በቶሎ ወደ መከላከል ያደርገው የነበረው ሽግግር ሲዳማዎች በፈጣን ንክኪዎች ወደ ግብ ለመድረስ የሚያደርጉትን ጥረት በማጨናገፉ በኩል ጥሩ ሆኖ ታይቷል። እስከ ውሃ ዕረፍቱ ድረስ ሲዳማዎች 13ኛው ደቂቃ ላይ ብቻ ከዚህ ሂደት የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። በዚህም ዳዊት ተፈራ ከፍ አድርጎ በላከው ግሩም ኳስ ብሩክ ሙሉጌታን ከፍሬው ጌታሁን ጋር አገናኝቶ ግብ ጠባቂው በበላይነት ኳሱን ያወጣበት ነበር።

ከውሃ ዕረፍቱ መልስ ጨዋታው ይበልጥ ቢቀዘቅዝም ሲዳማዎች ይተሻሉ ነበሩ። አጥቂው ይገዙ ቦጋለ ወደ ኋላ ተስቦ ቅብብሎችን እንዲከውን በማድረግ ሲዳማዎች የአማካይ ክፍል ብልጫውን ከድሬ መውሰድ ችለዋል። ያም ቢሆን የድሬዳዋን ተጫዋቾች በራሳቸው ሜዳ ላይ እንዲቀሩ ከማድረግ ያለፈ የጠሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር አልቻሉም። አጋማሹ ሊያበቃ ሲል ብቻ ደግፌ ዓለሙ በቀኝ መስመር ሀብታሙ ገዛኸኝ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ያሳለፈለትን ወደ ግብ የሰደደበት ቅፅበት ተጠቃሽ ቢሆንም ይገዙ ኳሷን ጨርፎ ከማስቆጠር ሞክሮ ፍሬው ጌታሁን ይዞበታል። በድሬዳዋ በኩል ግን አልፎ አልፎ ወደ ሳጥን ከሚላኩ ኳሶች በቀር ቡድኑ የሲዳማን የኋላ ክፍል መፈተን ሳይችል ጨዋታው ተጋምሷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ነቃ ብሏል። ሲጀመር የኳስ ቁጥጥሩን ብልጫ መልሰው የወሰዱት ድሬዎች ቀዳሚውን ዕድል ሲፈጥሩ 47ኛው ደቂቃ ላይ ጋዲሳ መብራቴ ያሳለፈለትን አቤል አሰበ ሳጥን ውስጥ ከቀኝ አቅጣጫ ሞክሮ ተክለማሪያም አውጥቶበታል። ከዚህ በኋላ ግን ቡድኑ ለግብ የቀረበው በ60ኛው ደቂቃ አቤል ከበደ በግራ ከሰጥኑ መግቢያ ላይ ወደ ላይ በላከው ኳስ ነበር።

አዲስ ፈራሚያቸው ሳላዲን ሰዒድን ቀይረው ያስገቡት ሲዳማዎች በሁለተኛው አጋማሽም የእንቅስቃሴ የበላይነቱን መልሰው አግኝተዋል። በዚህም 54ኛው ደቂቃ ላይ ጊት ጋትኩት ከማዕዘ በተነሳ ኳስ በግንባሩ ሙከራ አድርጎ ሲወጣበት ከሦስት ደቂቃ በኋላ የይገዙ እና ሳላዲን ጥምረት ሳጥን ውስጥ በቅብብል ጥሩ ዕድል ፈጥሮ አብዱለጢፍ መሀመድ ወደ ሙከራነት ሳይቀየር በፊት አውጥቶታል። ሳላዲን 64ኛው ደቂቃ ላይ ከአብዱለጢፍ ነጥቆ በቀኝ ከጠባብ አንግል አክርሮ የመታው ኳስም ጠንካራ ሙከራ ሆኖ ሲታይ ንቁ ሆኖ በዋለው ግብ ጠባቂ ፍሬው ተመልሶበታል።

ጨዋታው 80ኛውን ደቂቃ ሲያልፍ ጥሩ የማጥቃት ምልልሶች ማሳየት ጀምሯል። 82ኛው ደቂቃ ላይ ተቀያሪው ተመስገን በጅሮንድ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በፍሬው ሲድንበት ድሬዎችም በተቀያሪያቸው አብዱርሀማን ሙባራክ የቀኝ መስመር ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል። ሆኖም ጨዋታው በመጨረሻ ቅፅበቶች ወደ ቅዝቃዜው ተመልሶ ያለግብ ተቋጭቷል።

በውጤቱ ሲዳማ ቡና በ 27 ነጥብ 5ኛ ድሬዳዋ ከተማ በ 17 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ በነበሩበት ቀርተዋል።