የአሠልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 0-0 ሲዳማ ቡና

ያለ ግብ አቻ ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሠልጣኞቹ የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ተቀብሏል።

ሳምሶን አየለ – ድሬዳዋ ከተማ

በተመዘገበው ውጤት እና እንቅስቃሴ ደስተኛ ነህ?

እንቅስቃሴው ያሰብነው ነው። እኛ በይበልጥ በመከላከል አጨዋወት ተጫውተን በመልሶ ማጥቃት ለመግባት ነበር ያሰብነው። በሁለት የመሐል ተከላካዮች ለመጫወትም ነበር ያሰብነው። ከውጤት አንፃር መጥፎ አይደለም። ቡድናችንን የበለጠ መነቃቃት ውስጥ ያስገባልናል ብለን እናስባለን። እንደ አጠቃላይ ጥሩ ነው።

የኳስ ፍሰቱ ቶሎ ቶሎ ስለመቆራረጡ?

የባለፈው ጨዋታ ላይ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች አልነበሩም። በጣም ስኬታማ የሆኑ እና ጥሩ እንቅስቃሴ ያየንበት ነበር። የተባለው ነገር ትክክል ነው። አንዳንድ ጊዜ በእንቅስቃሴ ውስጥ ይገጥማል። ተጫዋቾቹ በግል ስታያቸው እንደዚህ አይነት ስህተት የሚሳሳቱ አይደለም። ነገርግን አሁን ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ጫናዎች ስላሉ ያ ጫና የፈጠረው ነገር ነው ብዬ ነው የማስበው።

መስተካከል ስላለበት የቡድኑ ቦታ?

አሁንም ኳስን ተቆጣጥረን በመጫወት ችግር የለብንም። ነገርግን በማጥቃት ላይ ቶሎ ቶሎ ግብ ጋር በመድረሱ ላይ ችግር አለ። እዚህ ላይ ጠንክረን እንሰራለን። ተመሳሳይ ክፍተት ያየንባቸው ቦታዎች ላይም የማጠናከሪያ ስራዎችን እንሰራለን።

ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

በውጤቱ እና በእንቅስቃሴው ደስተኛ ነህ?

ምን ደስ ይላል? ይሄ ጨዋታ ምንም የሚያስደስት ነገር የለውም። እኔን አይደለም ህዝቡንም ሊያስደስት የሚችል አደለም። የጨዋታው መልክ ልክ አይደለም። ህጉን ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ነበር። 90 ደቂቃ አሰልቺ ነበር። ጊዜ ማባከን እና ተያያዥ ነገሮች ሲጀመር ጀምሮ ነበሩ። አንዳንድ ጊዜ ለህዝብም መታዘን አለበት። ሰው የሚመጣው ኳስ ለማየት ነው። በአጠቃላይ ደስ የሚል ጨዋታ አልነበረም።

የተቆራረጡ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው እና ወደ ግብ ብዙም ስላልተኬደበት ምክንያት?

የሰው በሰው አያያዝ ስልቶች ነበሩ። እነሱ ይዘውት የመጡት ጨዋታ የእኛን አጨዋወት የማጨናገፍ ነገር ነበረው። የእኛን አማካዮች የመጫወት አቅም ለማሳጣት የተደረገ ጥረት አለ። ከዚህ አንፃር መቆራረጦች ይታያሉ።

ከዳኝነቱ ጋር ተያይዞ ስለነበራቸው ተቃውሞ?

በተለይ ከጊዜ ጋር ነው። ሲጀመር ጀምሮ እስከ መጨረሻ ሰው እንዴት ጊዜ ይገላል። ይሄ ደግሞ ጥሩ አይደለም። እኔ ከእዚህ አንድ ነጥብ አግኝቼ የት ያደርሰኛል? እኔ በእምነት ደረጃ ለማሸነፍ እንድንጫወት ነው የምፈልገው። ለማሸነፍ ተጫውተህ ቡድንህንም ህዝብንም ማስደሰት ያስፈልጋል። የትም አያደርሰንም እና። ከዚህ አንፃር እኛ የማጥቃት አጨዋወት ነው ያለን። ግን ያ እንዳይሆን ሜዳ ውስጥ ብዙ መሰናክሎች ነበሩ።

ያጋሩ