ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የ17ኛውን ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የተመለከተው ዳሰሳችን እንዲህ ይነበባል።

የጨዋታ ሳምንቱ በሊጉ ዝቅተኛ የግብ መጠን በማስተናገድ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማን በርካታ ግቦች ከተቆጠሩባቸው ቡድኖች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ጅማ አባ ጅፋር ጋር በማገናኘት ነው። እስካሁን ጥቂት ሽንፈት ብቻ (2) የገጠማቸው አዳማዎች አቻ የበዛባቸው በመሆኑ አለመሸነፍ የሚያመጣው ፀጋ ብቻውን ከሰንጠረዡ አጋማሽ አላሳለፋቸውም። በመሆኑም በመቀመጫ ከተማቸው የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘው ጅማን ስለማሸነፍ ያልማሉ። በሰበታ ድል ምክንያት ወደ 16ኛነት የወረዱት ጅማ አባ ጅፋሮች በበኩላቸው ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ሦስት ነጥብ ማሳካት ከቻሉ ነጥባቸውን 14 በማድረስ ላለመውረድ የሚያደርጉት ጥረት ላይ አንድ እርምጃ ለመጨመር ጥረት ያደርጋሉ።

ይህ ጨዋታ በዋነኝነት ኳስ የሚቆጣጠር ቡድንን ለፈጣን ሽግግር ምቹ ከሆነ ቡድን ያገናኛል። ይህ መሆኑ ደግሞ በጨዋታው በአካሄድ የተለያዩ ጥሩ ምልልሶችን እንድንመለከት የሚጋብዝ ነው። ኳስ መስርቶ ለመውጣት የሚያስችል የአማካይ ልምድ እና መዋቅር ያለው ጅማ አባ ጅፋር ነገም መሀል ሜዳ ላይ የተሻለ የቁጥጥር ብልጫ ሊኖረው ይችላል። ሆኖም የአዳማ የመሀል ክፍል በሀዋሳው ጨዋታ ያገኙ የነበሩትን የቅብብል ክፍተቶች የሚፈቅድ ላይሆን ይችላል። በዚህም የአሰልጣኝ አሸናፊ ቡድን በምስረታ ከሜዳው ከወጣ በኋላ ከታታሪዎቹ ከእነአማኑኤል ጎበና ጋር የሚገናኝባቸው ቅፅበቶች የጨዋታውን ውጤት የመወሰን አቅም ይኖራቸዋል። ጥያቄው የሚሆነ የጅማ ቅብብሎች ይህን ፈተና አልፈው ወደ አዳማ ሳጥን ያለቀላቸው ዕድሎችን ያደርሳሉ ወይንስ ኳስ አቋርጠው ወደ ፊት ሲያደርሱ አደገኝነት የሚነበብባቸው አዳማዎች በፈጣን ሽግግር ምላሽ ይሰጣሉ የሚለው ጉዳይ ይሆናል።

አዳማ ከተማ መሀል ላይ ብቻ ሳይሆን እንደቡድን ያለው የመከላከል አደረጃጀት የጅማን ቅብብሎች ለመቆጣጠር የሚያስችለው ጥንካሬው ነው። ሆኖም በግራም በቀኝም ለማጥቃት የተመቹ የመስመር ተከላካዮች ያሉት ቡድኑ በዳዋ ሆቴሳ የሚመራው የፊት መስመሩን የሚመጥኑ የማጥቃት ዕድሎችን መፍጠር ላይ ክፍተት ይታይበታል። አዳማ የሀዋሳን መንገድ ከመረጠ እና ጅማዎችን ማፈን ከቻለ ግን የመጨረሻ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ዘግይተውም ቢሆን መምጣታቸው የሚቀር አይመስልም። ለዚህ ምክንያት የሚሆነው ጅማ በእንቅስቃሴ ደረጃ ቢሻሻልም የቁጥጥር የበላይነቱን በጎል ማጀብ ሲሳነው ካለበት የውጤት ማጣት አንፃር ይበልጥ የማጥቃት ድፍረት ሲጨምር ከኋላው ለቀጥተኛ ኳሶች የሚሆን ክፍተት ሲተው መታየቱ ነው። የአዳማ የአማካይ ክፍል ከሰራተኝነት ባለፈ ቅብብሎችን በመከውንም ቢሆን ይህን ያህል የሚታማ አለመሆኑም መሰል ቅፅበቶች ለጅማ የሚሰጡት ፈተና ቀላል አይሆንም።

በአዳማ ከፊት እንደሚጣመሩ የሚጠበቁት የዳዋ ፣ አሜ እና አብዲሳ ዘጠኝ ጎሎች ያሉት የፊት መስመር ወይንስ ስድስት ጎል ያላቸው እዮብ እና መሀመድ ኑር በጨዋታው ያብባሉ የሚለው ይጠበቃል። እዚህ ላይ ሁለት ግቦች ያሉት እና የቡድኑን የኳስ ፍሰት ከማቀላጠፍ ባለፈ ለሳጥን ቀርቦ ሙከራዎችን ሲያደርግ የሚታየው ዳዊት እስጢፋኖስም መረሳት የለበትም።

አዳማ ከተማ አቡበከር ወንድሙን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ የማግኘት ዕድሉ የመነመነ ሆኗል። በዝውውር መስኮቱ በውሰት ስብስቡን ለመቀላቀል የተስማሙት ሦስቱ ተጫዋቾች (ወሰኑ ዓሊ ፣ ፀጋአብ ዮሐንስ እና ውብሸት ጭላሎ) ደግሞ የወረቀት ጉዳዮች ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ባለመገባደዱ ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸው ተመላክቷል። በጅማ አባ ጅፋር በኩል ዱላ ሙላቱ ጉዳት ላይ የሚገኝ ሲሆን በውሰት የመጡት (ጫላ በንቲ ፣ ቦና ዓሊ ፣ አስጨናቂ ፀጋዬ እና አካሉ አቲሞ) መጫወት ይችላሉ። የሀሪሰን ሄሱ የወረቀት ሥራ ግን አለመጠናቀቁን ሰምተናል።

ተከተል ተሾመ በመሀል ዳኛነት ፣ ሲራጅ ኑርበገን እና ማህደር ማረኝ በረዳትነት በላይ ታደሰ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ጨዋታውን ይመሩታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በቡድኖቹ የእስካሁኑ ሰባት ግንኙነት 11 ግቦችን በማስቆጠር 3 ድል ያስመዘገበው ጅማ አባ ጅፋር ቀዳሚ ሲሆን አዳማ ከተማ ሁለቴ አሸንፎ 8 ግቦችን አስመዝግቧል ፤ ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው

ጀሚል ያዕቆብ – ቶማስ ስምረቱ – አዲስ ተስፋዬ – ሚሊዮን ሰለሞን

አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው

አሜ መሀመድ – ዳዋ ሆቴሳ – አብዲሳ ጀማል

ጅማ አባ ጅፋር (3-5-2)

አላዛር ማርቆስ

ኢያሱ ለገሠ – የአብስራ ሙሉጌታ – ወንድማገኝ ማርቆስ

በላይ አባይነህ – ዳዊት እስጢፋኖስ – ሙሴ ካበላ – መስዑድ መሐመድ – እዮብ አለማየሁ

መሐመድኑር ናስር – ዳዊት ፍቃዱ

ያጋሩ