አርባምንጭ ከተማ ከድል ጋር ከታረቀበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ
ከጨዋታው በፊት ያሰቡትን በሜዳ ላይ ስለመተግበራቸው..?
አዎ። ከሞላ ጎደል ዝግጅት አድርገን ቪዲዮችን አይተናል። ጨዋታዎችንም እዚሁ በአካል አይተናል። ስለዚህ ጨዋታው እንዳሰብነው ፈጣሪ ረድቶን አሸንፈናል።
መሐል ሜዳ ላይ ብልጫ እንዳይወሰድባቹሁ ማድረግ ዋናው ዕቅዳቹሁ ነበር?
የትኛውም አላማችን ጨዋታዎችን አሸንፎ መውጣት ነው። ባላጋራ ባለው ክፍተት እና እኛ ባለን አቅም ነው። አጠቃላይ የሚኖራቸውን እንቅስቃሴ የማሰር ስራ የትኛውም ቡድን ሲመጣ እናስራለን። እጅ እና እግሩን ካሰርነው በኋላ ማጥቃቱን ላይ እንሄዳለን። እንደተባለውም የትኛውም የማጥቃት መንገዶችን ለመዝጋት ጥረት እናደርጋለን። ያም ተሳክቶልን የመጀመርያው አጋማሽ ጫና ፈጥረናል።
ከዕረፍት በኋላ ብዙ ሙከራ ስለተደረገባቸው..?
በተወሰነ መልኩ እያገባን ይገባብን ነበር። ትልቁ ነገር አግብተን ሁለተኛ ጎል ማግባት አማራጭ ይሆናል። ስለዚህ የማዕዘን ምት አካባቢ የምንሰራቸው አንዳንዴ ውጤት ለማስጠበቅ ከማሰብ ጎል ሲቆጠር ነቅሎ የመውጣት ነገር አለ። በሂደት አንድ አግብተን ሁለት፣ ሦስት ለማግባት እንሞክራለን።
አጥቂው አሪክ ካፓይቶ ጉዳት ኖሮበት አለመቀየራቸው?
ቅያሬያችንን ጨርሰናል። የቀረው አራት ደቂቃ ነው። ስለዚህ የምንቀይረው ተጫዋች ባለመኖሩ ነው።
ስለ ፀጋዬ አበራ..?
ብዙ ጊዜ ሲጥር ነበር። የጎል ሙከራዎችን ሲያደርግ ነበር። ዛሬ ደግሞ ተሳክቶለት ሁለት ጎሎች አስቆጥሯል። ጎል ስታስቆጥር ለቀጣይ ስነ ልቦናህን ከፍ ያደርጋል። ፀጋዬ ጠንካራ የሆኑ ነገሮች አሉት መልካም ነበር።
አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ – አዲስ አበባ ከተማ
ስለጨዋታው ሂደት?
እርግጥ ያው እግርኳስ ነውና በመንፈልገው መንገድ አልሄደም። መጀመርያ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሞክረናል። ከኋላ አካባቢ በተፈጠሩ ክፍተቶች ለመሸነፍ በቅተናል።
መሐል ሜዳ ላይ ስለነበረው ጫና እና ስለወሰዱት ቅያሪ..?
አንደኛ ውጤቱን እንፈልገው ስለነበር ሁለተኛ መሐል ሜዳ ላይ በርከት ያለ ስህተት ስለነበረ የጨዋወት መንገዱን ቀይረን አጥቂ በርከት አድርገን ለመጫወት ሞክረናል። በተሻለ እንቅስቃሴ በሁለተኛው አጋማሽ አድርገናል።
ስለ ተቆጠሩባቸው የግንባር ጎሎች..?
አዎ። ይሄን አይነት ትልቅ ችግር አለብን። ይህን መቅረፍ ካልቻልን ወደፊትም አደጋ ነው። ይሄን ለመቅረፍ እንሰራለን።
በወራጅ ቀጣና ላይ ስላለው ፉክክር..?
የእኛ ትልቁ ችግር ከኋላ ላይ ስለሆነ ይህንን ችግር መፍታት ይጠበቅብናል። እርሱ ላይም ችግሩን ለመፍታት የእርምት እርምጃዎች እንወስዳለን። ያንን አስተካክለን ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን እንቀርባለን።