ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርተዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ወላይታ ድቻ እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ በሀዋሳ ቢመራም በአንተነህ ጉግሳ የግንባር ጎል ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሁለቱ ተጋጣሚዎች በተመሳሳይ የ4-3-3 አሰላለፍ ጨዋታቸውን ሲጀምሩ ሀዋሳ ከተማዎች ዳግም ተፈራን በመሀመድ ሙንታሪ ፣ አብዱልባስጥ ከማልን በዳንኤል ደርቤ እንዲሁም ተባረክ ሄፋሞን በመስፍን ታፈሰ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል። ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው ጉዳት የገጠመው ስንታየሁ መንግሥቱን በምንይሉ ወንድሙ ቀይረው ገብተዋል።

የተጋጣሚዎቹን የሊጉ ሰንጠረዥ ደረጃ እና የሚጠበቀውን ፍልሚያ በሚመጥን የስታድየም ድባብ የታጀበው ጨዋታ ከጅምሩ ብርቱ ፉክክርን ማሳየት ጀምሯል። በአንድ ለአንድ ግንኙነት ውስጥ ይታዩ የነበሩት ሽኩቻዎችም የጨዋታውን ግለት ይበልጥ ከፍ ያደረጉ ነበሩ። በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ሀዋሳዎች በቅብብሎች ላይ ተመስርተው ሲያጠቁ ወደ ቀኝ አድልተው ወደ ፊት ይሄዱ የነበሩት ወላይታ ድቻዎችም ከቀጥተኛ ኳሶች ይልቅ ኳስ መስርተው ለመውጣት ጥረት ያደረጉባቸው የአጋማሹ ደቂቃዎች ነበሩ።

በሁለቱ ሳጥኖች መካከል ጥሩ የማጥቃት ምልልሶች የነበሩ ሲሆን የቡድኖቹ ሙከራዎች ግን በተከላካዮች የሚደረቡ አልያም በጠንካራ የመጨረሻ ውሳኔ የታጀቡ ሳይሆኑ ሁለቱ ግብ ጠባቂዎች ከባድ ፈተና አላገኛቸውም። ቀዳሚው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች ሲሆኑ ልማደኛው የያሬድ እና አንተነህ የቆሙ ኳሶች ጥምረት ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። በዚህም 21ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳዊት ያሻማውን የማዕዘን ምት አንተነህ ጉግሳ በግንባሩ ሞክሮ መድኃኔ ብርሀኔ ከግብ ውስጥ አውጥቶበታል።

ሀዋሳዎች ቅብብሎቻቸው ተሳልጠው ወደ ድቻ የግብ ክልል የደረሱበት ቅፅበት ግን ወደ ግብነት ተቀይሯል። ብሩክ በየነ ኤፍሬም አሻሞ ያስጀመረውን ማጥቃት ተቀብሎ ኳስ ገፍቶ በመሄድ በሳጥኑ መግቢያ ላይ በአራት የድቻ ተከላካዮች መሀል ያሳለፈለትን ኳስ ወንድምአገኝ ኃይሉ ተረጋግቶ በመቆጣጠር ጎል አድርጎታል። በቀሪው የአጋማሹ ደቂቃዎች የሜዳ ላይ ሽኩቻዎቹ ይበልጥ ጎልተው የታዩ ሲሆን የቡድኖቹ ፉክክር ሌላ ግብ ሳይታይበት ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ቀዝቅዝ ብሎ ታይቷል። ወላይታ ድቻዎች የኳስ ቁጥጥሩን ብልጫ ይዘው በሀዋሳ ሜዳ ላይ አመዝነው ሲታዩ ሀዋሳዎች እንደመጨረሻ ጨዋታቸው የመልሶ ማጥቃት ባህሪን ተላብሰው ታይተዋል። ሆኖም ከዕረፍት መልስ ከባድ ሙከራ የታየው 71ኛው ደቂቃ ላይ አናጋው ባደግ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ መሀመድ መንታሪ ሲያድንነበት ነበር።

 

በጨዋታው ይታዩ የነበሩት ሽኩቻዎች 80ኛው ደቂቃ ቀይ ካርድ አስከትለዋል። እድሪስ ሰዒድ የአዲስዓለም ተስፋዬን በእጅ በመምታቱ የኃይለየሱስ ባዘዘው ቀጥታ ቀይ ካርድ ሰለባ ሆኗል። ሆኖም ድቻዎች ጫናቸውን ሲጠጥሉ 86ኛው ደቂቃ ላይ ንጋቱ ገብረስላሴ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ያደረገውን ከባድ ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ እንዲሁ ቃልኪዳን ዘላለም ወደ ግብ የላከው ሌላ ከባድ ሙከራ በሙንታሪ ጥረት ሲድን እሱን ተከትሎ በአዲስ ህንፃ የተነሳው የማዕዘን ምት አንተነህ ጉግሳ በግንባር ገጭቶ ግብ አድርጎታል። ቀይ ካርዱን ተከትሎ በቁጥር ያነሱት ድቻዎች እስከፍፃሜው ያደረጉት ጥረት በአንተነህ ግብ አንድ ነጥብ አስገኝቶላቸው ጨዋታው በ1-1 ውጤት ተፈፅሟል።

በውጤቱም ወላይታ ድቻ 32 ፣ ሀዋሳ ከተማ 31 ነጥብ በመያዝ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ረግተዋል።