የአሠልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-1 ጅማ አባ ጅፋር

የሳምንቱ የማሳረጊያ መርሐ-ግብር በአቻ ውጤት ከተገባደደ በኋላ አሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ

ስለጨዋታው?

የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ መሐል መለዳ ላይ ትንሽ መቆጣጠር አልቻልንም ነበር። በሁለተኛው አጋማሽም ያንን ለማስተካከል ሞክረናል። ጨዋታውን ማሸነፍ የምንችልባቸውን የግብ ዕድሎች አግኝተናል። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ብንጠቀም ማሸነፍ እንችል ነበር። አሁንም ግን በአጀማመራችን ደስተኛ አይደለሁም። ግልፅ የጎል ዕድሎች እያገኘን እየተጠቀምን አይደለም። ጨዋታውን ለማሸነፍ ጫና ውስጥ እንደሆንን ይሰማኛል። በዛ ምክንያትም ነው ጎሎችን እየሳትን ያለነው። እንግዲህ ከዚህ ጨዋታ ተነስተን ለሚቀጥለው ጨዋታ ራሳችንን አስተካክለን እንመጣለን።

በጨዋታው ስለነበራቸው ጠንካራ እና ደካማ ጎን?

በመጀመሪያው አጋማሽ የእነሱን ፈጣን ሽግግር መቆጣጠር ተቸግረን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ያንን ለማስተካከል ሞክረናል። በተቻለ መጠን ቶሎ ቶሎ ጎላቸው ጋር በመድረው ዕድሎችን ለመፍጠር ነበር የሚከርነው። እነሱ በጣም ተጠቅጥቀው እየተከላከሉ ነበር። ይህም ቢሆን ግን ማስከፈት ችለን ነበር። ግን ዛሬ አልተሳካልንም።

በፉክክር ውስጥ ስለመቆየታቸው?

ዕድሎች አሉ። በእርግጥ ዕድሎችን እያባከንን ነው። ከጊዮርጊስ በስተቀር ከእኛ በላይ ያሉት አብዛኞቹ ቡድኖች ነጥብ ጥለዋል። ዛሬ ወደ እነሱ የምንደርስበትን ዕድል ነው ያባከነው። ዞሮ ዞሮ በእግር ኳስ ከድል፣ ሽንፈት እና ድል አንዱን ታገኛለህ። አንዱን አግኝተናል። ምንም እንኳን በየጨዋታው አቻ መውጣታችን ጫና ቢፈጥርብንም ለሚቀጥለው ጨዋታ ራሳችንን አስተካክለን ለመምጣት እንሞክራለን።

በመቀመጫ ከተማቸው ማግኘት ስለሚገባቸው ነጥቦች?

ምንም ጥያቄ የለውም። ደጋፊዎቻችንን ማስደሰት እንፈልጋለን። በእርግጥ እኛን ጫና ውስጥ እንደሚከተን እናውቃለን። ግን እስከመጨረሻው ድረስ ያሉንን ቀሪ ጨዋታዎች በአሸናፊነት ተወተን ወደ ላይ ከፍ ማለት እንፈልጋለን።

ስለዳኝነቱ?

የሚታይ ነው። ብዙም ስለ ዳኞች ማውራት አልፈልግም። ግን አንዳንዶቹ ግልፅ ናቸው። ሳጥን ውስጥ ከአንድም ሁለተ3 ጊዜ የተሰሩት ጥፋቶች ግልፅ ናቸው። እኩሌታው በዳኛ ነው ብዬ ማሳበብ አልፈልግም። ቢሆንም እንደዚህ አይነት የተሳሳቱ ውሳኔዎች ጨዋታዎችን እንዳታሸንፍ እን እንድትሸነፍ ያረጋል።

አሸናፊ በቀለ – ጅማ አባ ጅፋር


በሁለቱ አጋማሽ ስላደረጉት እንቅስቃሴ?

በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ነበረን። መሐል ላይ ስናደርገው የነበረው የኳስ ፍሰት ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ነው። ጎል ሲገባብን ግን ትንሽ የመደናበር ነገር ይታይ ነበር። ዞሮ ዞሮ ውጤቱን አስጠብቀን ወጥተናል። አቻ መውጣቱ ለእኛ በቂ ነው።

በሁለተኛው አጋማሽ ስለነበረባቸው ጫና?

ትልቁ ችግር ኳሱን ተረጋግተን ስላልያዝን ነው። አማካዮቻችን ሌላ ጊዜ እንደሚያንሸራሽሩልን ሊያንሸራሽሩልን አልቻሉም። በራሳችን ኳሶች ነበር የምንጠቃው። ኳሶች ይለጋሉ በዛው ኳስ እንጠቃ ነበር። ትልቁ ችግር ይህ ነበር። በቀጣይ እናስተካክላለን።

ስለአዲሶቹ ተጫዋቾች ብቃት?

ከከፍተኛ ሊግ የመጡ ናቸው። ስለዚህ ተስፋ ሰጪ ነገር አለው። ወደፊት የራስ መተማመናቸው እየዳበረ ሲሄድ ጥሩ ቦታ ይደርሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለው።

ላለመውረድ ስለሚደረገው ትንቅንቅ?

የመውረድ እና ያለመውረድ ትንቅንቁ በእኛ ብቻ አይደለም። ተከታታይ ሁለት ሦስት ጨዋታ የምታሸንፍ ከሆነ ወገብ ላይ ነው የምትደርሰው። ቀጣይ እያንዳንዱ ጨዋታ የፍፃሜ ጨዋታ ነው የሚሆነው። የሚቀጥሉትን ጨዋታዎች በጥንቃቄ ለመጫወት እንሞክራለን።

ስለነበረው ዳኝነት?

እንደውም እኛ ላይ ተፅዕኖ ፈጠረ ከማለት በስተቀር የአቅማቸውን በቅርበት እየተቆጣጠሩ ነው ያለው። በእኔ በኩል ዳኞችን የምለው ነገር የለም። ምክንያቱም በ90 ደቂቃ ውስጥ ዳኛ ላይ ጣት መቀሰሩ በእኔ ደረጃ ያዋጣል ብዬ አላስብም።