የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ በ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር ውድድር በአዳማ ከተማ በመጀመር ሁለት ሳምንታትን በደማቅ ሁኔታ ማገባደዱ ይታወቃል። የ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተደርገው በትላንትናው ዕለት ፍፃሜ ያገኙ ሲሆን የሊግ ካምፓኒው የውድድር እና ስነ ስርአት ኮሚቴ በሳምንቱ በታዩ የዲሲፕሊን ጉድለቶች ላይ የቅጣት ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በዚህም መሠረት በሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የተጋጣሚ ቡድን አመራሮችን ስለመሳደባቸው እና ቁርጥራጭ ወንበሮችን ወደሜዳ ስለመወርወራቸው እንዲሁም 42 ወንበሮች የተቆረጡ፣ የተሰነጠቁ ወይም የተነቀሉ ስለመሆናቸው ሪፖርት በክለቡ ላይ መቅረቡን በመግለፅ የክለቡ ደጋፊዎች ለፈፀሙት ጥፋትና ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ክለቡ መቀጣቱ እንዲሁም ደጋፊዎቹም ሊታረሙ አለመቻላቸውን ታሳቢ በማድረግ ክለቡ የሰባ አምስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ተወስኗል።
በተመሳሳይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችም ቁርጥራጭ ወንበሮችን ወደ ሜዳ ስለ መወርወራቸው እንዲሁም 34 ወንበሮች የተቆረጡ፣ የተሰነጠቁ ወይም የተነቀሉ ስለመሆናቸው ሪፖርት በመቅረቡ ሃያ አምስት ሺህ የገንዘብ ቅጣት ክለቡ እንዲከፍል ተወስኗል። አዳማ ከተማም ክለቡ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር በነበረው ጨዋታ ደጋፊዎቹ የዕለቱን ዳኛ እና የተጋጣሚ ቡድን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን አፀያፊ ስድብ በመሳደባቸው ሃምሳ ሺህ እንዲከፍል ተወስኗል። የወላይታ ድቻ ቡድን መሪ አቶ ወንድሙ ሳሙኤል በበኩላቸው ከሀዋሳ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ የእለቱን ዋና ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘውን በቃልና በምልክት አፀያፊ ስድብ በመሳደባቸው የአምስት ሺህ ብር የገንዘብ እና የ6 ጨዋታ እገዳ እንደተላለፈባቸው ታውቋል፡፡
አክሲዮን ማኅበሩ ባወጣው ሌላ መረጃ ደግሞ የተገቢነት ክስን በተመለከተ የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ወልቂጤ ከተማ ከፋሲል ከነማ ባደረጉት ጨዋታ የፋሲል ከነማ ቡድን በወልቂጤ ተጫዋቾች ላይ ባቀረበው የተገቢነት ክስ ምክንያት ውጤቱ ለጊዜው እንዳይፀድቅና ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ማብራሪያ እንዲጠየቅበት መወሰኑን ያመለክታል።