ባሳለፍነው ወር ላይ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ለመቼ እንደተዘዋወረ ታውቋል።
ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ዓመታዊ 13ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከወራት በፊት በአርባምንጭ ከተማ መከናወኑ ይታወሳል።
በጉባኤው መጠናቀቂያ ላይ በቀጣዩ የአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ መጋቢት ወር ላይ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚደረግ እና የፌድሬሽኑን ፕሬዝዳንት ጨምሮ የሥራ አስፈፃሚ አባላትን ለመምረጥ የሚደረገው ጉባኤ በሰኔ ወር ጎንደር ከተማ ላይ እንደሚደረግ በወቅቱ መገለፁ ይታወቃል።
ሆኖም አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በተባለበት ወር ሳይካሄድ ቀርቷል። ምክንያቱ ደግሞ የሚሻሻሉ ሰነዶች በአግባቡ ተጠናክረው አለመድረሳቸው በመሆኑ ተገልፆል። በዚህም መሠረት የቀን እና የወር ሽግሽግ ተደርጎ በቀጣይ ግንቦት ሰባት ቀን በአዲስ አበባ ከተማ በተመረጠ ሆቴል ሊካሄድ መታሰቡን አውቀናል።
ግንቦት ወር ሊካሄድ በታሰበው በየአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት የፌድሬሽኑን ፕሬዝዳንት እና የሥራ አስፈፃሚ አባላትን ምርጫን አስመልክቶ አባላቱ በሚወስኑት ወር እና ቀን በጎንደር ከተማ የሚካሄድ ይሆናል።