[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በቀጣዩ ሳምንት የሚደረገው 4ኛው የኢቢሲ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስፖርት ሽልማትን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
በኢትዮጵያ ሚዲያ ታሪክ ገናና ስም ያለው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከ2010 ጀምሮ በስፖርቱ ዘርፍ ምርጥ ብቃት አሳይተዋል ያላቸውን ስፖርተኞች ሲሸልም እንደነበር ይታወቃል። ታላቁ ብሔራዊ ጣቢያ ዘግየት ብሎም ቢሆን የ2013 ምርጥ ስፖርተኞችን በዘጠኝ የተለያዩ ዘርፎች ለመሸለም ሽር ጉድ ላይ የሚገኝ ሲሆን በቀጣዩ ሳምንት ሚያዚያ 8 በሸራተን አዲስ ሆቴል በደመቀ ሁኔታ ያሳለፍነውን ዓመት ምርጦች መሸለሚያ ዝግጅቱን ያከናውናል። ይህንን ዝግጅት አስመልክቶም የተቋሙ የመመዝናኛ እና ስፖርት ማኔጂንግ ኤዲተር መሳይ ወንድሜነህ እና የኢቢሲ ስፖርት ክፍል ዋና ዳይሬክተር ግርማ በቀለ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
በቅድሚያም አቶ መሳይ 4ኛው የኢቢሲ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስፖርት ሽልማትን በተመለከተ መጠነኛ ገለፃ አድርገዋል። “ኢቢሲ ከዚህ ቀደም 3 ጊዜ በስፖርቱ ሽልማቶችን አዘጋጅቷል። አራተኛው አሁን መካሄድ ካለበት ጊዜ ዘግይቶ ነው የሚካሄደው። 2014 መጀመሪያ ወራት አካባቢ መካሄድ የነበረበት የሽልማት መርሐ-ግብር ነበር። ነገርግን በአስገዳጅ ሀገራዊ ጉዳዮች ተገፍቶ እዚህ ደርሷል። መደበኛ አመታዊ የስፖርት ውድድር የሽልማት መድረክ ቢሆንም ጊዜው ቢረፍድም የየአመቱን ሽልማት እያካሄዱ መሄድ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘነው ሚያዚያ 8 ይሄንን የሽልማት መድረክ ሸራተን አዲስ ሆቴል እናካሂዳለን።
“የኢቢሲ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስፖርት ሽልማት የሚል ነው የዘንድሮ መጠሪያው። ይሄ የሆነውም የዚህ ፕሮግራማችን ዋነኛ አጋር የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አብሮን መስራት የጀመረበት ዓመት ስለሆነ ነው። ለቀጣይ ዓመታትም ከእኛ ጋር ይቀጥላል ብለን እናስባለን። ይህ አይነት ነገር የተለመደ ነው። በዚህ አጋጣሚ ንግድ ባንክን በጣም እናመሰግናለን።
“ከመጀመሪያው የሽልማት መርሐ-ግብር በአቀራረብም ሆነ በውድድር ዘርፎች ለውጥ እያደረግን አራተኛው ላይ ደርሰናል። ከዚህም በኋላ በየአመቱ እያዘጋጀን እንቀጥላለን። ዘንድሮ ከአመታዊ እንቅስቃሴዎቹ ዘርፎች በተጨማሪ የህይወት ዘመን ተሸላሚ ዘርፍ ይኖረናል። በሁሉም ዘርፍ የሚኖሩት አሸናፊዎች ዋንጫ፣ ሰርተፊኬት እና የገንዘብ ሽልማት ይኖራቸዋል። ኮከብ ተጫዋቾችን በተመለከተ ዓምና 75 ሺ ብር ተሰጥቶ ነበር። አሁን ወደ 100 ሺ ብር ከፍ ብሏል። ለኮከብ አሠልጣኞች ደግሞ የ75 ሺ ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል። የህይወት ዘመን ተሸላሚ ደግሞ 50 ሺ ብር ነበር የሚሰጠው አሁን ወደ 75 ሺ ብር ከፍ ብሏል። ከምንም በላይ ግን ከገንዘቡ በላይ ትልቁን ቦታ የሚይዘው እውቅናው ነው።”
የ2013 የስፖርት እንቅስቃሴዎች ታሳቢ ተደርገው የተዘጋጀው መርሐ-ግብር ላይ ባለሙያዎች በኮሚቴ ተዋቅረው እጩዎችን የመለየት ሥራ የተከናወነ ሲሆን በምርጫውም 25% የህዝብ ድምፅ ዋጋ እንዳለው ተመላክቷል። በመግለጫው እንደተገለፀውም እስካሁን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ድምፅ በአጭር የፅሁፍ መልዕክት በአድማጭ ተመልካቾች እንደተሰጠ ተጠቁሟል።
በማስከተል መድረኩን የተረከቡት ጋዜጠኛ ግርማ በቀለ ዘርፎቹን በተመለከተ ተከታዩን ማብራሪየሰ ሰጥተዋል።
“ዘርፎቹ በዛ ያሉ ናቸው። ይህ ትልቅ ሥራ ይጠይቃል። ዓመቱን ሙሉ ስለሽልማት ማሰብ ትንሽ ከበድ ይላል። ግን ለስፖርት ቤተሰቡ የገባነው ቃል መቅረት የለበትም የሚል ሀሳብ ተቋሙ ስለነበረው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም ለማስቀጠል ሞክረናል። ይህ ሽልማት መስከረም 28 ላይ ለማድረግ ነበር ቀድመን ሥራዎችን ስንሰራ የነበረው። በተለያዩ ምክንያቶች ግን ተራዝሞብናል። ዝግጅቱን ስናዘጋጅ ዓምና የነበረውን ክፍተት በደንብ ገምግመን ነው። ከዛ ወደ ዘንድሮ ስንሰራ ሁለት ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል። አንደኛው ባለሙያዎች የሚገኙበት ኮሚቴ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሁሉንም ነገር የሚቆጣጠር እና በተቋሙ አስተዳደር የሚመራ አብይ ኮሚቴ ነው። ያሉት 7 ዘርፎች ላይ የቴክኒክ ኮሚቴው ነው ሥራ የሚሰራው። ሁለቱ ዘርፎች (ልዩ እንቅስቃሴ ያደረጉ እና የህይወት ዘመን ተሸላሚ) ላይ ደግሞ ዲፓርትመንቱ ባቀረበው ምክረ-ሀሳብ መነሻነት ነው ማኔጅመንቱ ውሳኔ የሚያሳልፈው። ከዚህ ውጪ ያሉት ዘርፎች ግን የቴክኒክ ኮሚቴው ሀላፊነት ወስዶ የሚሰራቸው ናቸው። መሳይ እንደገለፀው ደግሞ 25% የሚሆነው የተመልካች ምርጫ ነው።
“በሚዲያችን እንደገለፅነው ሦስት የመጨረሻ እጩዎችን ለይተናል። የቴክኒክ ኮሚቴው የራሱ ዝርዝር መስፈርቶች ነበሩ። በአትሌቲክስም የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ትኩረት ሰጥተን ተመልክተን ዝርዝር ጉዳዮችን አውጥተን ነጥቦችን አስቀምጠናል። በቴክኒክ ኮሚቴው ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሆነ ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም ከጋዜጠኞች ማኅበር የተመረጡ ሁለት ሁለት ሰዎችን ይዘን ከተቋሙ ስፖርት ክፍል ሁለት ሰው ጋር በመሆን እያንዳንዱን መስፈርት አውጥተናል። ለምሳሌ በእግር ኳሱ ሶከር ኢትዮጵያ በቅርበት መረጃዎችን ስለሚይዝ ከእነሱ ጋር ተባብረን መስፈርቱን ለማውጣት ሞክረናል። በዚህም የመጨረሻ 10 እጩዎችን ይፋ አድርገናል። ከሳምንታት በፊት ደግሞ የቴክኒክ ኮሚቴው 75 የህዝብ 25 በመቶ አካተን የመጨረሻ ሦስት እጩዎችን መርጠናል። አሁን የቴክኒክ ኮሚቴ ከአንድ እስከ ሦስት ያሉትን መርጧል። የሚቀረው የተመልካች ምርጫ ነው። ይህ ስራ እስከ መጨረሻው ድረስ ፍፁም ሚስጥራዊ በሆነ መልኩ ነው።” በማለት ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ በሚደረገው የሽልማት መርሐ-ግብር ላይ በስፖርቱ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መስኮች የሚገኙ ታዋቂ ሰዎችን ጨምሮ በርከታ እንግዶች እንደሚገኙ ተገልጿል። መግለጫውን ሲመሩት የነበሩት ጋዜጠኛ አባይነህ በበኩላቸው ዝግጅቱም በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰናዳ እንደሆነ እና የተቋሙን ብራንድ በጠበቀ መልኩ እንደሚከውን አመላክተዋል።
በ7ቱ ዘርፎች የቀረቡ የመጨረሻ ሦስት እጩዎችም የሚከተሉት ናቸው።
– በሴቶች እግር ኳስ ተጫዋች ዘርፍ
ረሂማ ዘርጋው፣ ሰናይት ቦጋለ እና ሎዛ አበራ
– በሴቶች እግር ኳስ አሠልጣኞች ዘርፍ
ሰርካዲስ እውነቱ፣ ብርሃኑ ግዛው እና መልካሙ ታፈረ
– በወንዶች እግር ኳስ ተጫዋች ዘርፍ
አቡበከር ናስር፣ ያሬፍ ባየህ እና ሸመክት ጉግሳ
– በወንዶች እግር ኳስ አሠልጣኞች ዘርፍ
ካሣዬ አራጌ፣ ሥዩም ከበደ እና አብርሃም መብራቱ
– በሴቶች አትሌቲክስ አትሌቶች ዘርፍ
ለተሰንበት ግዳይ፣ መቅደስ አበበ እና ጉዳፍ ፀጋዬ
– በወንዶች አትሌቲክስ አትሌቶች ዘርፍ
በሪሁ አረጋዊ፣ ሰለሞን አረጋ እና ጌትነት ዋለ
– ከአትሌቲክስ አትሌቶች ዘርፍ
ተሾመ ከበደ፣ ሁሴን ሸቦ እና ሀሉፍ ሀድጎ