ወልቂጤ ከተማ ፋሲል ከነማ ላይ ያገኘው ሦስት ነጥብ ለጊዜው እንዳይፀድቅ ለምን ተደረገ?

በ17ኛ ሳምንት ወልቂጤ ከተማ ከወቅቱን የሊጉ አሸናፊ ፋሲል ከነማ ያገኘው ሦስት ነጥብ ለጊዜው እንዳይፀድቅ የተደረገበትን ምክንያት አጣርተናል።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሊግ እርከን ውድድርን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በ17ኛ ሳምንት የታዩ የዲሲፕሊን እፀፆችን በተመለከተ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች በማኅበራዊ ገፁ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ከተወሰኑ ውሳኔዎች መካከል አንዱ ደግሞ በጫላ ተሺታ እና ጌታነህ ከበደ ጎሎች ፋሲል ከነማን ያሸነፈው የወልቂጤ ሦስት ነጥብ በጊዜያዊነት እንዳይፀድቅ መደረጉ ይገኝበታል።

ጉዳዩን ለማጣራት ባደረግነው ጥረትም ፋሲል ከነማ የተጫዋች ተገቢነት ክስ ጨዋታው ከመጀመሩ አንድ ሰዓት አስቀድሞ ማቅረቡን አውቀናል። የቀረበው የተጫዋች ተገቢነት ክስም ሠራተኞቹን በውድድር አጋማሽ እንደተቀላቀሉ የተነገረው አዳዲስ ተጫዋቾችን በተመለከተ እንደሆነ ተረድተናል። የቀረበውን ክስ ዛሬ ረፋድ የተመለከተው የሊጉ የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው እና የተጫዋቾችን ዝውውር የሚያፀድቀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማብራሪያ እንዲጠየቅበት አቅጣጫ አስቀምጦ እስከዛም የተመዘገበው ውጤት ለጊዜው እንዳይፀድቅ አድርጓል።

ያቀረቡትን ክስ እንዲያስረዱን የፋሲል ከነማ አመራሮችን ጥያቄ ብናቀርብም ጉዳዩ በጥንቃቄ እንዲያዝ ከመፈለግ ጋር በተያያዘ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ድረ-ገፃችን ባደረገው ማጣራት ግን ፋሲል ከነማ “ወልቂጤ በተጫዋቾች ዝውውር ላይ እንዳይሳተፍ ዕገዳ ተጥሎበት ተጫዋች አስፈርሞ ማጫወቱ ተገቢ አይደለም” የሚል ይዘት ያለው እንደሆነ አረጋግጠናል።

ወልቂጤ ከተማ ፋሲልን ባሸነፈበት ጨዋታ በዝውውሩ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች መካከል አማካዩ አክሊሉ ዋለልኝን በመጀመሪያ አሰላለፍ አስገብቶ ለ45 ደቂቃዎች ግልጋሎት ማግኘቱ ይታወሳል። የግብ ዘቡ ሮበርት ኦዶንካራ እና አጥቂው ቤዛ መድህን ደግሞ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጠው ነበር።

በተያያዘ ዜና በሁለተኛው ዙር በርካታ የተጫዋች ተገቢነት ክስ እየቀረበ እንደሚገኝ የሰማን ሲሆን ክሱ መቅረብ ከሚገባው የጊዜ እና የሂደት አጠባበቅ ጋር ተያይዞ ብቻ አብዛኞቹ ክሶች ውድቅ እየተደረጉ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።