በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች የሁለተኛው ፅሁፋችን አካል ናቸው።
👉 ሦስቱ “ጉግሳዎች” ግብ ያስቆጠሩበት ሳምንት
የጨዋታ ሳምንቱ ለሦስቱ “ጉግሳዎች” የማይረሳ ነበር ፤ ቸርነት ፣ ሽመክት እና አንተነህ ጉግሳ ሁሉም ለክለቦቻቸው ግብ ያስቆጠሩበት ሳምንት ነበር።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን 4-0 በረታበት የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የሚጫወተው ቸርነት ጉግሳ ደምቆ ውሏል። የጨዋታውን መልክ የቀየረችውን ሁለተኛ ግብ ከዕረፍት መልስ በነበሩት የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በግሩም አጨራረስ በማስቆጠር በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ የመጀመሪያ ግቡን ከ764 የጨዋታ ደቂቃዎች በኋላ ማስመዝገብ ችሏል።
ሽመክት ጉግሳ በበኩሉ ቡድኑ በወልቂጤ ከተማ በተሸነፈበት ጨዋታ ቡድን ከሽንፈት ያልታደገችውን ግብ ሲያስቆጥር ይህችም ግብ የውድድር ዘመኑ ሦስተኛ ግብ ሆና ተመዝግባለች።
በጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ዕለት በሰንጠረዡ አናት እጅግ ይጠበቅ በነበረው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ተቃርቦ የነበረ ሲሆን አንተነህ ጉግሳ ግን በ90ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት የግንባር ኳስ ቡድኑን ከሽንፈት ታድጓል። ይህችም ግብ አንተነህ በውድድር ዘመኑ ያስቆጠራት ሁለተኛ ግብ ነበረች።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት የሰጡት ቸርነት እና አንተነህ ግቦቻቸውን ለደጋፊዎቻቸው እና በቅርቡ ህይወታቸው ላለፉት ወላጅ አባታቸው ያበረከቱበት ሂደት በራሱ ትኩረት የሚስብ ነበር።
👉 የረመዳን ወር እና ተጫዋቾቻችን
በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ታላቁ የረመዳን ወር ከገባ ቀናት የተቆጠረ ሲሆን በአመሻሽ በሚደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ ተጫዋቾች በጨዋታ መሀል አፍጥር ሲያደርጉ ተስተውሏል።
ታድያ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች መካከል ባህር ዳር ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ባደረጉት ጨዋታ ወቅት ቀኑን ሙሉ ምግብ እና ውሃ ሳይቀምሱ የዋሉት የባህር ዳር ከተማ ተጫዋቾች በጨዋታው ወቅት አፍጥር አድርገዋል።
በ41ኛው ደቂቃ የሀዲያ ሆሳዕናው የመስመር ተመላላሽ የሆነው ብርሃኑ በቀለ ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ ጨዋታ ሲቋረጥ የባህር ዳር ከተማ ተጫዋቾች የሆኑት ፉአድ ፈረጃ ፣ መናፍ ዓወል ፣ አህመድ ረሺድ እና ፈቱዲን ጀማል የቡድናቸው ተጠባባቂዎች ወደሚገኙት የሜዳው ጠርዝ በማምራት አፍጥር ሲያደርጉ ተመልክተናል።
በተመሳሳይ አዳማ ከተማ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ እንዲሁ በ42ኛው ደቂቃ አላዛር ማርቆስ ላይ በተሰራ ጥፋት ጨዋታው መቋረጡን ተከትሎ ጀማል ጣሰው ፣ አሜ መሀመድ እና ጀሚል ያዕቆብ በተመሳሳይ አጋጣሚውን አፍጥር ለማድረግ ተጠቅመውበታል።
👉 ሳላ ተመልሷል
በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ከተመለከትናቸው ድንቅ አጥቂዎች መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደበው ሰልሀዲን ሰዒድ ለግማሽ የውድድር ዘመን ከእንቅስቃሴ ርቆ ቢቆይም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ዳግም ወደ ሜዳ ተመልሷል።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የነበረው ቆይታ መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ጅማ አባ ጅፋር ለማቅናት ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ማድረግ ሳይችል ቀርቷል። ይህን ተከትሎ ሁለተኛው ዙር ከመጀመሩ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ ወደ ሲዳማ ቡና ለማምራት መስማማቱ አይዘነጋም።
ከቡድኑ የህክምና ባለሙያ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሳቢያ በፌደሬሽኑ የተጣለበትን ቅጣት እስኪያጠናቅቅ ድረስ በ16ኛ የጨዋታ ሳምንት በስታዲየም ተገኝቶ የቡድኑን ጨዋታ መከታተል ችሎ የነበረ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ሲዳማ ድሬዳዋ ከተማን በገጠመበት ጨዋታ ከተጠባባቂነት በመነሳት 45 ያህል ደቂቃዎች ተሰልፎ መጫወት ችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ ብሩክ ሙሉጌታን ቀይሮ መግባት የቻለው ሰልሀዲን ሰዒድ በጨዋታው አንድ አደገኛ የነበረች የግብ ሙከራ ማድረግ ሲችል በጨዋታው በጥልቀት የሚከላከለውን የድሬዳዋን የተከላካይ መስመር ለመፈተን በሚያስችል መልኩ ከርቀት ወደ ግብ ኳሶችን ሲሞክር አስተውለናል።
ሌላው ከሳልሀዲን ተቀይሮ መግባት በኋላ ያስተዋልነው ጉዳይ የቡድኑ ሁነኛ የግብ አዳኝ የሆነው እና በሊጉ ሁለተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ይገዙ ቦጋለ በሳላ መግባት ከፊት አጥቂነት ይልቅ ከቀኝ መስመር እንዲነሳ ተደርጓል። ታድያ በቀጣይ ሰልሀዲን ሰዒድ ይበልጥ ቡድኑን እየተላመደ ሲመጣ አሰልጣኙ ሁለቱን አጥቂዎች በምን መልኩ ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ የሚለው ነገር በጉጉት ይጠበቃል።
👉 ሙና በቀለ እና ፀጋዬ አበራ የደመቁበት ጨዋታ
በጨዋታ ሳምንቱ ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል አርባምንጭ ከተማ አዲስ አበባን 2-1 የረታበት ጨዋታ ብዙም ሳይጠበቅ አዝናኝ ሆኖ የተጠናቀቀ ጨዋታ ነበር።
በጨዋታው ትኩረትን ከሳቡ ጉዳዮች አንዱ የነበረው በማጥቃት ፍላጎት ረገድ የተሻሻለውን አርባምንጭ ከተማ የመመልከታችን ጉዳይ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ በተለይ ቡድኑ በጨዋታው በተጠቀመው የ4-4-2 የተጫዋቾች አደራደር ውስጥ መስመር አማካይነት ጨዋታውን የጀመሩት ሙና በቀለ እና ፀጋዬ አበራ እጅግ ውጤታማ የነበረ ቀንን ማሳለፍ ችለዋል።
በጨዋታው አርባምንጭ ከተማ ያስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ሙና በቀለ ከማዕዘን ምት እና ከቀኝ መስመር ካሻማቸው ኳሶች የተገኙ ሲሆን በሁለቱም አጋጣሚዎች ኳሱን ሳጥን ውስጥ በመገኘት በመግጨት ያስቆጠረው ደግሞ ፀጋዬ አበራ ነበር።
በስብስቡ ውስጥ ከአማካዩ እንዳልካቸው መስፍን ቀጥሎ በአስራ አምስት ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ የቻለው አማካዩ ፀጋዬ አበራ እስካሁን በሊጉ ምንም ግብ ሳያስቆጥር ቢቆይም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሁለት ግቦች በማስቆጠር የግብ መዝገቡን የከፈተ ሲሆን ሙና በቀለ እንዲሁ ሁለት ግብ የሆኑ ኳሶች በማቀበል በሊጉ ያቀበላቸውን ጎል የሆነ ኳሶችን መጠን ወደ 3 ማሳደግ ችሏል።
👉 በውሰት የመጡት ተጫዋቾች
በሀገራችን እግርኳስ በቋሚነት ከሚደረጉ ዝውውሮች ባለፈ በውሰት የሚደረጉ ዝውውሮች ሲፈፀሙ እምብዛም አንመለከትም። ነገርግን አሁን ላይ በዚህ ረገድ አውንታዊ መሻሻሎችን እየተመለከትን እንገኛለን።
በጠባብ የቡድን ስብስብ ፕሪሚየር ሊጉን የጀመረው ጅማ አባ ጅፋር ይህን ክፍተት ለመድፈን በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንታት የተወሰኑ ተጫዋቾች በውሰት ውል የማስፈረሙ ነገር በዚህ ረገድ ፈር ቀዳጅ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ በተለይ የከፍተኛ ሊግ ውድድር አስቀድሞ መጠናቀቁን ተከትሎ አንዳንድ የሊጉ ክለቦች ክፍተት አለብን በሚሏቸው የመጫወቻ ስፍራዎች ላይ የተወሰኑ ተጫዋቾችን በውሰት ውል እያስፈረሙ ይገኛል።
በዚህ ሂደት ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ዝውውራቸውን ከፈፀሙ ተጫዋቾች መካከል ጥቂቶቹ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አድርገዋል።
ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያመራው የተከላካይ አማካዩ አብነት ደምሴ በሸገር ደርቢ ቡድኑ ሲረታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተቀይሮ በመግባት ተሳትፎ ያደረገ ሲሆን በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባህር ዳር ከተማን የተቀላቀለው አደም አባስም እንዲሁ ቡድኑ በሀዲያ ሆሳዕና በተሸነፈበት ጨዋታ 59ኛው ደቂቃ ላይ አለልኝ አዘነን ተክቶ በመግባት በግሉ የጨዋታውን ውጤት ለመቀየር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ አስተውለናል።
ከሻሸመኔ ከተማ እና ሀምበሪቾ ዱራሜ ወደ ጅማ አባ ጅፋር ያመሩት ቦና ዓሊ እና አስጨናቂ ፀጋዬ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ማድረግ የቻሉ ሲሆን በተለይ አማካዩ አስጨናቂ ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴን ሲያደርግ የመስመር አጥቂው ቦና ደግሞ በመስመር ተከላካይነት ሲጫወት አስተውለናል።
የውሰት ውሎች ተጫዋቾችን በውሰት ለሚሰጠውም ሆነ ተጫዋቹን በውሰት ለሚያገኘው ክለብ ከሚኖረው ጥቅም አንፃር የውሰት ውሎች ከዚህ በበለጠ በሊጋችን ሊለመዱ ይገባል።
👉 በስህተቶች ውስጥም ጥረቱን ያላቆመው ተከላካይ
ኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ባስተናገደበት የደርቢው ጨዋታ ከቡድኑ የ90 ደቂቃ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ብቸኛው አውንታዊ ጉዳይ የወጣቱ ተከላካይ ደሳለኝ ገዛኸኝ ጥረት ነበር።
በሊጉ አራተኛ ጨዋታውን ያደረገው ወጣቱ ተከላካይ ከፍተኛ ግምት በሚሰጠው በዚህ ትልቅ ጨዋታ አሰልጣኙ በጉዳት በሳሳው ስብስብ ውስጥ ሌላ አማራጭ እያላቸው እሱን ለመጠቀም መወሰናቸው በራሱ የሚያስገርም ቢሆንም የተጫዋቹ እንቅስቃሴ ግን አሰልጣኙ ለምን ተመራጭ እንዳደረጉት የሚያሳይ ነበር።
ከፋሲል ከነማ ጋር በመጀመሪያ ዙር በነበራቸው ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና መለያ የመጀመሪያውን ጨዋታ ያደረገው ወጣቱ ተከተላካይ በወቅቱ ያሳየን የራስ መተማመን እና ድፍረት የሚደነቅ የነበረ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ባለ ልምድ ተጫዋቾች እንኳን እምብዛም ሲያደርጉት የማንመለከተውን በስህተቶች ውስጥም ሆኖ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ያደረገው ጥረት የተለየ ነበር።
በቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ከፍተኛ ጫና ይደርስባቸው የነበሩት የኢትዮጵያ ቡና ከወገብ በታች የሚገኙ ተጫዋቾች ውስጥ በጨዋታው ኃላፊነትን ወስዶ ቡድኑ ከዚህ ጫና ሊያመልጥባቸው የሚችሉ መንገዶች በመፈልግ ረገድ ገዛኸኝ የተሻለው ነበር።
በድፍረት ኳሶችን በጫና ውስጥ እየተቀበለ ደህነታቸው ከተጠበቀ አማራጮች ይልቅ “ከፍተኛ ስጋት ከፍተኛ ምላሽ” ያላቸውን የቡድኑን የኳስ ሂደት ማሳደግ የሚችሉ ወደ ፊት የሚደረጉ ቅብብሎችን ለማድረግም ሆነ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ተጫዋቾች በመቀነስ እንቅስቃሴውን ወደ ፊት ለማስቀጠል ጥረት አድርጓል።
ታድያ በዚህ ሂደት ከተጋጣሚ ያየለ ጫና ጋር ተያይዞ ኳሶቹ በተደጋጋሚ ቢቋረጡም ከወጣትነቱ በላቀ የአዕምሮ ብሰለት ከቡድኑ የጨዋታ መርህ ሳይወጣ ያደርገው የነበረው ድፍረት የተሞላ እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነበር።
👉 ተፅዕኖ ፈጣሪው ተቀያሪ – አዲስ ግደይ
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከረጅም ጊዜ ጉዳት የተመለሰው አዲስ ግደይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ዳግም ወደ መጀመሪያ ተመራጭነት ለመመለስ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ በነበረው የጨዋታ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ በርካታ ተጫዋቾችን በኮቪድ ምክንያት መጠቀም አለመቻሉን ተከትሎ ከጉዳት መልስ ዳግም በቀጥታ ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት በመምጣት አዲስ አበባ ከተማ ላይ ግብ በማስቆጠር የጀመረው አዲስ ግደይ በሁለተኛው ዙር ሁለት ጨዋታዎች ከተጠባባቂ ወንበር በመነሳት ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።
በድምሩ 119 ደቂቃዎችን በሦስት ጨዋታዎች ማድረግ የቻለው አዲስ ግደይ በሊጉ በአማካይ በአርባ ደቂቃ አንድ ግብ እያስቆጠረ ይገኛል። ለአንድ ዓመት ያህል በጉልበት ጉዳት ከሜዳ ርቆ የተመለሰው አዲስ የቀደመ ብቃቱን ለማግኘት ይቸገራል ተብሎ ቢገመትም ቀስ በቀስ ግን የምናውቀውን አዲስ ዳግም ልንመለከት እንደምንችል ፍንጭ እየሰጠ ይገኛል። ከጨዋታ ጨዋታ በግቦቹ ታግዞ የራስ መተማመኑ እየተመለሰ የሚገኘው ተጫዋቹ በቀጣይ ጨዋታዎች ወደ ቋሚነት ለመምጣት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን ለማሳመን የተቻለውን እየጣረ ይገኛል።
👉 የባህር ዳር ከተማ ግብ ጠባቂዎች
በሁለት ተከታታይ የጨዋታ ሳምንታት ባህር ዳር ከተማ በግብ ጠባቂዎቹ ስህተት ነጥብ ለመጣል ተገዷል።
ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ባህር ዳር ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋራ ወጣቱ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑሪ ከቡድን አጋሩ ሰለሞን ውዴሳ ወደ ኋላ የተመለሰለት ኳስ በእግሩ ስር አምልጣው ግብ እንደተቆጠረበት የምናስታውስ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ አቡበከር ኑሪን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ፋሲል ገ/ሚካኤል በጨዋታው ውጤቱን የቀየረችው ግብ ስትቆጠር ለግቡ መቆጠር ምክንያት የሆነ ስህተት ፈፅሟል።
እንደ አቡበከር ሁሉ ፋሲል ገ/ሚካኤል ከቡድን አጋሩ ፈቱዲን ጀማል ወደ ኋላ የተመለሰለትን ኳስ በፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ጫና ውስጥ ገብቶ በአግባቡ ማቀበል አለመቻሉን ተከትሎ የተሳሳተውን ፍቅረየሱስ እንዳይጠቀም ፈቱዲን ጀማል ባደረገው ጥረት ኳሱ ወደ ማዕዘን ምት ይቀየራል። የማዕዘን ምቱ ሲሻማም ፋሲል በሰራው የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ፍሬዘር ካሳ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል።
ታድያ በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ጠባቂ የቀየረው ባህር ዳር ከተማ ቡድኑ “በንድፈ ሀሳብ” ደረጃ መጫወት ለሚፈልገው የኳስን ቁጥጥር መሰረት ላደረገው የጨዋታ መንገድ የተመቹ ተጫዋቾች በተለይም ግብ ጠባቂዎች በስብስቡ አሉት ወይ ስንል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድዳል።
እርግጥ ሁለቱም ስህተቶች መሰረታዊ መነሻቸው የባህር ዳር ከተማ ግብ ጠባቂዎች ከተጋጣሚ ተጫዋቾች ጫና ሲደርስባቸው ያላቸው ምላሽ አሉታዊ ከመሆኑ ይመነጫል። በዚህ ሂደትም ግብ ጠባቂዎቹ መሰረታዊ ስህተቶችን ሲሰሩ እንመለከታለን ፤ ይህም በሀገራችን እግርኳስ ውስጥ ካለው ደካማ የቴክኒክ ክህሎት አረዳድ ጋር ተዛማጅነት አለው።
“ጥሩ ተጫዋች ከሆንክ በጫና ውስጥ ሆነህ መጫወት ትችላለህ ፤ ከጫና ውጪ የትኛውም ተጫዋች ጥሩ ኳስ ሊያቀብል ይችላል ስለዚህ ጫናዎች የትኛው ተጫዋቾች ጥሩ እንደሆነ ለማሳየት ይረዳል።” የሚለው የታላቁ የእግር ኳስ ሰው ዮሀን ክራይፍ አባባል ሁኔታውን በአጭሩ ያስረዳልናል።
በመሆኑም ግብ ጠባቂዎቹ ተቀይረው ስህተቱ የሚቀጥል ከሆነ የግብ ጠባቂዎቻችን በመለስተኛ ጫና ውስጥ ሆነው እንኳን በእግር የመጫወት አቅማቸውን ጨምሮ ሌሎች ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ማስገባት ጠቃሚ ይሆናል።
ስለዚህ ወጣት ግብ ጠባቂ ስለሆነ ብቻ በእግር መጫወት ይችላል ከሚለው እሳቤ ተወጥቶ የትኞቹ ግብ ጠባቂዎች ምቾት ተሰምቷቸው በእግራቸው ይጫወታሉ የሚለው ጉዳይ በደንብ መመዘን ይገባል ይህ ካልሆነ ግን ምቾት ሳይሰማቸው በእግር እንዲጫወቱ የሚገደዱ ግብ ጠባቂዎች ካሉ መሰል ስህተቶች መኖራቸው አይቀሬ ይመስላል።
ከባህር ዳር ከተማ ውጪ ግን ከኳስ ጋር ምቾት በማጣት እና በሌሎች ስህተቶች መነሻነት ደካማ እንቅስቃሴ ያላሳዩ ከዛም አልፎ ንቁ ሆነው የዋሉ ግብ ጠባቂዎች የተመለከትንበት ሳምንት ነበር ማለት ይችላል። በየቡድናቸው ለግብ የቀረቡ ከአንድ በላይ አደገኛ ኳሶችን በማዳን የድሬዳዋው ፍሬው ጌታሁን ፣ የሀዲያ ሀሳዕናው ወጣት ግብ ጠባቂ ያሬድ በቀለ ፣ በተከታታይ ሳምንት ድንቅ አቋም ያሳየው የወልቂጤው ሰዒድ ሀብታሙ ፣ ከባድ በነበረው የአርባምንጭ ከተማ እና አዲስ አበባ ጨዋታ በሁለቱም ግቦች የነበሩት ሳምሶን አሰፋ እና ዳንኤል ተሾመ እንዲሁም ሌላኛው ወጣት የጅማው አላዛር ተጠቃሽ ይሆናሉ።