[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በሦስተኛው ፅሁፋችን ደግሞ ትኩረት የሳቡ አሰልጣኞችን የተመለከቱ ጉዳዮችን እናነሳለን።
👉 ጫና እያየለባቸው የሚገኙ አሰልጣኞች
የአጭር ጊዜ እሳቤ በገነገነበት የሀገራችን እግር ኳስ ይቅርና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንኳን የአሰልጣኞች ሥራ ዋስትና በቀጥታ ከሚያስመዘግቡት ውጤት ጋር የተሳሰረ ነው። በዚህም የጥቂት ጨዋታዎች ውጤት ማጣት ሥራን እስከማጣት የሚያደርስ ዋጋ ሲያስከፍላቸው እንመለከታለን። ታድያ ሊጉ ወሳኝ በሆነው ሁለተኛ ዙር ምዕራፍ ላይ እንደመገኘቱ የተለያዩ አሰልጣኞች ከውጤት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ጫና ውስጥ ይገኛሉ።
በዚህ ረገድ ቀዳሚው የነበሩት እና አሁን ከኃላፊነታቸው ለመነሳት የተስማሙት የፋሲል ከነማ የቀድሞው አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ናቸው። አምና የሊጉ አሸናፊ የነበረው ቡድናቸው ዘንድሮ ግን ከወዲሁ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ10 ነጥቦች ርቆ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በተለይም በሁለተኛው ዙር ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ቡድናቸው ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ሲጋራ በዚህኛው ሳምንት ደግሞ በወልቂጤ ከተማ ሽንፈትን አስተናግዷል። ታድያ ከውጤት ባለፈ ሜዳ ላይ እያዩ በሚገኙት የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ደስተኛ ያልሆኑት የቡድኑ ደጋፊዎች ቡድኑ በወልቂጤ ከተማ በተሸነፈበት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አሰልጣኙ ላይ ያላቸው ዕምነት እንደተመናመነ የሚያሳይ ፅሁፎችን ይዘው ተመልክተናል።
“….የዛሬው ውጤት እኔም ሆነ ተጫዋቾቼ ጋር ያለውን ጫና ከፍ ሊያደርግ ይችላል። ከጫና ወጥቶ መስተካከል የክለቡ፣ የደጋፊዎቹ፣ የእኛ እና የአመራሮቹ በአጠቃላይ የሁላችንም ህብረት እና ጥረት ይጠይቃል። ኳስ ጨዋታ ሂደት ነው። ይህንን ሂደት ለመለወጥ ሁሉም ሰው ከጎናችን እንዲሆን ነው የምጠይቀው። እያንዳንዱ ተጫዋች የሚሰማውን ነገር አውቃለው።….ስለዚህ ሁሉም ሰው ከጎናችን ሆኖ ቡድኑ የተሻለ እንዲሆን ድጋፉ አይለየን ነው የምለው።” የሚልን ሀሳብ አሰልጣኙ በወልቂጤ ከተረቱበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሲናገሩ አድምጠን የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን አሰልጣኙ ከክለቡ ጋር በስምምነት የመለያየታቸው ነገር እርግጥ ሆኗል።
በተመሳሳይ የአምና ስኬታቸው ሰለባ የሆኑት ኢትዮጵያ ቡና እና ካሳዬ አራጌም በዚህ ሳምንት ተቃውሞን አስተናግደዋል። በተለይም በደርቢው ጨዋታ በተቀናቃኛቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ በድምሩ 8-1 የመሸነፋቸው ጉዳይ ደጋፊዎችን አንገት ያስደፋ አጋጣሚ ሆኗል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ጨዋታው እስኪጠናቀቅ በስታዲየም የቆዩ የክለቡ ደጋፊዎች በክለቡ የቡድን አባላት ላይ ሆነ አመራሮች ላይ ከፍተኛ ተቃውሞዎችን ሲያሰሙ አድምጠናል። አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጫና ውስጥ ስለመሆናቸው ለቀረበላቸው ጥያቄ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።
“ቡና ውስጥ ሁሌም ጫና አለ ፤ ተጫዋችም ሆኜ ስለማውቀው። አንድ ታሳቢ መሆን ያለበት ነገር ግን ደጋፊው ውጤት ሲጠፋ ያዝናል ፣ ሥራ አመራር ቦርዱ ያዝናል ፣ ኮቺንግ ስታፉም ተጫዋቹም እንደሚያዝን ግንዛቤ መኖር አለበት ፤ ደጋፊውም ጋር ሥራ አመራር ቦርዱም ጋር። እነሱ ብቻ እንደሚያዝኑ አድርገው ማሰብ የለባቸውም ፤ ያ ሀዘን ያ ቁጭት እኛም ጋር አለ። ይሄ ግንዛቤ እንዲኖር ነው በተረፈ ግን ጫናው ሁል ጊዜ ቡና ውስጥ አለ። እያሸነፍክ ለቻምፒዮንነት እየሄድክም ሆነ እየተሸነፍክ ጫናው ሁል ጊዜ ቀጣይኑት ያለው ነው። በዛ ጫና ውስጥ ተጫዋችም ፣ አሰልጣኙም ፣ ሥራ አመራር ቦርዱም ማለፍ ግድ ነው።”
ሌላኛው በሊጉ በተጠበቀው ደረጃ መፎካከር የተሳነው ባህር ዳር ከተማን እየመሩ የሚገኙት አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱም ብዙ የተጠበቀበትን ስብስብ ወደ ውጤት መምራት አለመቻላቸውን ተከትሎ በደጋፊዎች ዘንድ በአሰልጣኙ ላይ ጥርጣሬዎች እየተነሱ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም የቡድኑ ደጋፊዎች በክለቡ ጽ/ቤት በመገኘት በክለቡ አባላት እና አመራሮች ላይ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን አሁናዊ የቡድኑ ውጤትም ደጋፊዎችን ከሜዳ ቀስ በቀስ እያራቀቸው ይገኛል።
በመሆኑም በቀጣይ በሚኖሩ ጨዋታዎች ሦስቱ ቡድኖች ከሌሎች በበለጠ ይህን ጥሩ ያልሆነ አየር ለማጥራት ውጤት የማግኘት ጫና ውስጥ ሆነው ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።
👉 ገብረመድህን ኃይሌ የሰላ ትችት የሰነዘሩበት የድሬዳዋ አቀራረብ
“ምን ደስ ይላል? ይሄ ጨዋታ ምንም የሚያስደስት ነገር የለውም። እኔን አይደለም ህዝቡንም ሊያስደስት የሚችል አይደለም። የጨዋታው መልክ ልክ አይደለም።…….በአጠቃላይ ደስ የሚል ጨዋታ አልነበረም።”
“ሲጀመር ጀምሮ እስከ መጨረሻ ሰው እንዴት ጊዜ ይገላል። ይሄ ደግሞ ጥሩ አይደለም። በእኔ በእምነት ደረጃ ለማሸነፍ እንድንጫወት ነው የምፈልገው። ለማሸነፍ ተጫውተህ ቡድንህንም ህዝብንም ማስደሰት ያስፈልጋል።”
ይህ ሀሳብ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያለ ግብ በአቻ ካጠናቀቁት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሰጡት አስተያየት ነው።
እግር ኳስ ለሙያተኞቹ ስራ ለተመልካቹ ደግሞ በማያጠያይቅ መልኩ መዝናኛ የመሆኑ ጉዳይ የሚያጠያይቅ አይደለም። ሆኖም ብዙ ጊዜ ይህ እውነታ በተዛባ አውድ ውስጥ ሲተረጎም እንመለከታለን።
በእግርኳስ ስለመዝናናት ሲታሰብ ሁሌም ቅብብሎች ፣ የማጥቃት ጨዋታዎች እና ጎሎች አስቀድመው ወደ አዕምሯችን ይመጣሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የሚከላከሉ ፣ በቀጥተኛ አጨዋወት የሚጫወቱ ፣ ጊዜ የሚያባክኑ ቡድኖች ደግሞ ሁሌም ሲነቀፉ እና ጥረታቸው ሲጣጣል ይስተዋላል።
ነገርግን በአሉታዊ አጨዋወት ለመጫወት ከሚወስደው ትጋት እና ትኩረት እንዲሁም ሌሎች ሁኔታዎች አንፃር ለእነዚህ ቡድኖች ጥረት በመጠኑም ቢሆን ዋጋ መስጠት ተገቢ ነው።
የጨዋታ ዕቅድ ምርጫ ጉዳይ የትኛውም ቡድን በጨዋታ ማሳካት የሚፈልገውን ነገር ከጨዋታው ለማግኘት ያዋጣናል ባሉት መንገድ መቅረብ የአሰልጣኞቹ ምርጫ ነው። በዚህ ሂደት ከፍፁም ማጥቃት እስከ ጥቅጥቅ መከላከል ድረስ በፈለጉት መንገድ የመቅረብ ምርጫቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ሁሉም ቡድኖች አጥቅተው እንዲጫወቱ መጠበቅ ግን የዋህነት ነው።
በዚህ ሂደት ውስጥ ቡድኖች እነሱ ይዘውት በቀረቡት የጨዋታ ዕቅድ ውስጥ የሚፈልጉትን ነገር ለማሳካት የተጋጣሚን ዕቅድ በማክሸፍ የራስን ፍላጎት ጨዋታ ላይ መጫን አስፈላጊ ነው። አሰልጣኝ ገብረመድህንም ቡድናቸውን በመሰል አቀራረብ የገጠማቸውን ድሬዳዋ ከተማን በተለያዩ መንገዶች በማጥቃት ግቦችን አስቆጥረው ማሸነፍ ሲገባቸው ይህን ባላደረጉት ሁኔታ የተጋጣሚን አቀራረብ ላይ ትችት ማቅረቡ ብዙም ውሃ የሚያነሳ ሀሳብ አይደለም።
👉 ጨዋታ በጨዋታ ስለማቀድ
አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ከሸገር ደርቢ መጠናቀቅ በኋላ ቡድናቸው ስለ ሊጉ አሸናፊነት ማሰብ ስለመጀመሩ ሲጠየቁ አሰልጣኙ ተከታዩን ብለዋል።
“እኔ ወደፊት ያለውን ጨዋታ ነው የማየው እና ዛሬ ይሄ አልቋል ነገ ከድሬዳዋ አለ ፤ የድሬዳዋ ግብዓት ሌላ ነው። ስለዚህ ከፊት ያለውን ጨዋታ አስቤ ስለመዘጋጀት ነው የማስበው።”
በተመሳሳይ የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ስለ ዋንጫ ፉክክሩ ሲጠየቁ በሰጡት ምላሽም ከፊት ያሉንን እያንዳንዱን ጨዋታ በተራ በተራ መወጣት መሰረታዊው ጉዳይ ስለመሆኑ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ከውድድሮች በፊት ሆነ በውድድሮች መካከል በስፋት አሰልጣኞቻችን ስለ ዕቅዶቻቸው ሲጠየቁ የሚያነሱት ሀሳብ ነባራዊ ሁኔታን ያልገመገመ በስፋት የተለጠጡ እንዲሁም ከአዕምሮ ይልቅ በልብ የሚሰጡ ሀሳቦችን ስናደምጥ ቆይተናል።
ከውድድሮች አስቀድሞ ሁሉም አሰልጣኞች በሚያስብል መልኩ በውድድሩ የተለመደውን “ከአንድ እስከ ሦስት” ይዘን ለማጠናቀቅ እንጥራለን የሚሉ አስተያየቶችን ሲሰጡ ማድመጥ የተለመደ ነው በውድድር መሀልም ሁኔታዎችን በማጤን ሀሳባቸውን ለማስተካከል ሲሞክሩም አይደመጥም።
በተለመደው እሳቤ ውስጥ ቢሆን ኖሮ ዘሪሁን ሸንገታም ሆነ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም በልባቸው ተመርተው ሀሳብ ሲሰጡ ልናደምጥ በቻልን ነበር። ነገርግን አሰልጣኞቹ በአዕምሯቸው ሁኔታዎችን በመመዘን ከላይ የጠቀስናቸውን ሀሳቦችን አንስተዋል።
በመሆኑም በአውሮፓ እግርኳስ በስፋት እንደምንመለከተው አሰልጣኞች ሀሳቦችን ሲሰጡ ሁሉን ነገር ጨዋታ በጨዋታ ለማስኬድ ጥረት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ። ይህ እሳቤ በሀገራችን አሰልጣኞች ሲነገር መደመጡ በራሱ ደስ የሚያሰኝ ነው።