[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″] የመጨረሻው ፅሁፋችን ደግሞ ትኩረት የሳቡ የጨዋታ ሳምንቱ ጉዳዮች ተዳሰውበታል።
👉 ከቆሙ ኳሶች የተቆጠሩ ግቦች
በጨዋታ ሳምንቱ በተደረጉ ጨዋታዎች በርከት ያሉ ኳሶች ከቆሙ ኳሶች ሲቆጠሩ መመልከት ችለናል።
በጨዋታ ሳምንቱ በድምሩ ከተቆጠሩ አስራ ስድስት ግቦች አምስቱ የተቆጠሩት ከቆሙ ኳሶች ነበሩ።
ከእነዚህም መካከል አዲስ ግደይ በቀጥታ ከቅጣት ምት ካስቆጠራት ግብ ውጪ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ፣ ፍሬዘር ካሳ ፣ ፀጋዬ አበራ እና አንተነህ ጉግሳ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ በግንባር በመግጨት ማስቆጠር ችለዋል።
በዚህ ሂደት ግን አስቆጣሪዎቹን ብናወድስም የቡድኖቻችን የቆሙ ኳሶችን የመከላከል ሂደት ላይ አሁንም በብዙ መልኩ መሻሻሎችን መመልከት ይገባናል።
👉የኢትዮጵያ ቡና መለያ ጉዳይ
ሁለተኛው ዙር ከመጀመሩ አስቀድሞ ኢትዮጵያ ቡና ላለፉት ዓመታት አጋሩ በመሆን ሲሰራ ከነበረው “ሀ እስከ ፐ” ከተሰኘው ሀገር በቀል ድርጅት ጋር የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ፈፅሟል።
በዚህ ስምምነት ተቋሙ ከ3 ሚሊዮን በላይ የዋጋ ግምታቸው የሆኑ በሁለቱም ፆታዎች ለሚገኙት ቡድኖች የሚሆኑ 500 የመጫወቻ ሙሉ ትጥቆች ፣ ለዋናው ቡድን እና ለአሰልጣኞች 100 ቱታዎች እና 50 የአሰልጣኝ ስታፍ ቲሸርቶች በቅርብ በተካሄደ መርሐግብር ላይ ርክክብ እንደሚፈፀም አይዘነጋም።
ታድያ እነዚሁ በሦስት ቀለም አማራጭ የቀረቡት መለያዎች የንድፍ ሀሳባቸው ከግዙፉ ዓለም ዓቀፉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ የሆነው “Adidas” ከዩሮ 2016 አንስቶ በ2016/17 የክለቦች የውድድር ዘመን የተጠቀመበት እና ተለምዷዊ የአዳዲስ 3 የትይዩ መስመሮች “Stripes” በመለያው እጀታ ይልቅ በመለያው የጎን ወገን ላይ ከሰፈረባቸው መለያዎች በተቀዳ ሀሳብ የተሰሩት መለያዎቹ ናቸው።
የ “Adidas” መለያ የሆኑት ሦስቱ መስመሮች በመለያው ሆነ በቱታዎች ላይ የሰፈሩባቸውን እነዚህ ትጥቆች ላይ በየትኛውም ቦታ ላይ የ “Adidas” አርማ ያለመመልከታችን ጉዳይ ሁኔታውን የሚያነጋግር አድርጎታል። ከመለያው ርክክብ ጋር በተያያዘ በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም ስለጉዳዩ የተሰጠ ማብራሪያ አለመኖሩ ግርምትን የሚፈጥር ሆኗል።
በሦስት አማራጭ ከቀረቡት መለያዎች መካከል በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ የተጠቀመበት ደማቅ ቀይ ቡኒው መለያ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የተጫዋቾች ቁጥር እና ስም በጥቁር ቀለም በመፃፉ አሁንም ለዕይታ አስቸጋሪ ሆኖ ተመልክተነዋል።
በተመሳሳይ ሌላው ከአዲሱ መለያ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ ኢትዮጵያ ቡና ስምምነቱን ከፈፀመ በኋላ ሁለት ጨዋታዎችን ቢያደርግም እስካሁን ድረስ ግን ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ እየተጠቀመው የሚገኘው የቀድሞውን መለያ ነው ታድያ አስገራሚው ነገር ደግሞ አቤል ማሞ እየተጠቀመ የሚገኘው መለያ ላይ የ”ቡና ባንክ” የቀድሞው እንዲሁም በቅርቡ ተቋሙ አርማን ካሻሻለ በኋላ እየተጠቀመበት የሚገኘው አዲሱ አርማውም በተመሳሳይ በመለያው ላይ ሰፍረው ይታያሉ። ከዚህ በተጨማሪም በመለያው ላይ የኢትዮጵያ ቡና አጋር የሆኑ ሁለት ተቋማት አርማም የሰፈረበት አለመሆኑ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ነው።
ክከዚህ ጋር በተያያዘ አዲሱ መለያ ይፋ በሆነበት ሥነስርዓት ላይ ግብ ጠባቂዎች ከሦስቱ የቀለም አማራጮች ቡድኑ ከሚጠቀመው ቀለም የተለየውን መለያ ለብሰው እንደሚገቡ ተጠቁሞ ነበር። ይህም ማለት በዚህ ሳምንት ቡድኑ ቀይቡኒውን መለያ በመጠቀሙ ግብ ጠባቂው በተመሳሳይ ዲዛይን ቢጫውን ወይንም ነጩን አድርጎ እንደሚገባ ይጠበቅ ነበር።
👉 የአዳማን ስታዲየም ያደመቀው የደጋፊዎች ድባብ
የሊግ ውድድሮች በኮቪድ ወረርሺኝ በኋላ ተቋርጠው ከተመለሱ ወዲህ በቅርቡ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም እየተመለከትነው የምንገኘው የደጋፊዎች ድባብ እጅግ የተለየ ነው።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በተወሰኑ ጨዋታዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ በሜዳ የተመለከትን ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ተጠባቂ በነበረው የሸገር ደርቢ ጨዋታ የተመለከትነው የደጋፊዎች ድባብ አስደማሚ ነበር።
ውድድሩ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት በምትገኘው አዳማ ከተማ እንደመደረጉ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች ወደ ስፍራ በማቅናት ጨዋታውን ታድመዋል። እርግጥ በጨዋታው የመጀመሪያ 30 ደቂቃዎች ላይ በር ላይ ከትኬት ጋር በተፈጠረ መጨናነቅ በርከት ያለ ቁጥር ያለው ደጋፊ በፍጥነት ወደ ሜዳ ለመግባት ቢቸገርም በጨዋታው ሂደት ግን በርካታ ቁጥር ያለው የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊ ሜዳ በመግባት ጨዋታው ላይ ህይወት ዘርተውበታል።
ከዚህ ባለፈ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች ስታዲየሙ በመሙላቱ የተነሳ ሜዳ መግባት ሳይችሉ መቅረታቸውን ከግምት ውስጥ ስናስገባ እግር ኳሳችን ወደ ቅድመ ኮቪድ ዘመን ዳግም እየተመለሰ ስለመሆኑ ማሰብ ያስችለናል።
👉 ፋሲል ከነማ በነጩ ቁምጣ ተመልሷል
ፋሲል ከነማ በ2009 የውድድር ዘመን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ከተቀላቀለ ወዲህ በተለይም ደግሞ ከ2010 የውድድር ዘመን አንስቶ የሚጠቀሙበት ነጭ ጃኖ መለያ ከነጭ ቁምጣ ጋር ያለው ስብጥር በብዙዎች ዘንድ የሚወደድ የመለያ ስብጥር ነበር።
ነገርግን ባልታወቀ ምክንያት ፋሲል ከተማዎች ይህን መለያ ከቀይ ቁምጣ ጋር አሰባጥረው ሲጠቀሙ የቆዩ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ቡድኑ በቤትኪንግ የተሰራለትን አዲሱን መለያ ጥቅም ላይ መዋል ሲጀምር መጠነኛ መሻሻሎች ተደርጎበት የተመረተውን አዲሱን ነጭ ጃኖ መለያ ከነጭ ቁምጣ ጋር ተጠቅመዋል።
ይህ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተመለከትናቸው ለዕይታ ማራኪ የሆነ የቀለም ስብጥር እንዲሁም የንድፍ ሀሳብ ያለው መለያ ዳግም ጥቅም ላይ መዋሉ ዕይታ የተለየ መስህብን መፍጠር ይችላል።