ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ አርባምንጭ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የ18ኛው ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታን የተመለከተ ዳሰሳችንን እንዲህ አሰናድተናል።

በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት በባህር ዳር ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ላይ ድል የተቀዳጁት ሀዲያ ሆሳዕና እና አርባምንጭ ከተማ እርስ በእርስ በሚያደርጉት ፍልሚያ 18ኛውን ሳምንት ይጀምራሉ። ከአራት ጨዋታ በኋላ ሙሉ ውጤት ይዘው የወጡት ሆሳዕናዎች ከአደጋው ክልል በስድስት ነጥብ መራቅ የቻሉ ሲሆን በነገው ጨዋታ የሰንጠረዡን አጋማሽ ለመሻገር ይልማሉ። በውድድሩ አራተኛ ድላቸውን ያሳኩት አዞዎቹ ደግሞ ከከዚህ ቀድሞቹ ድሎች በኋላ ወደ አቻ የተመለሱበትን አካሄድ አሁን ወደ ተከታታይ ድል መቀየር ከቻሉ ውጤቱ ከላይ ወዳሉት አምስት ቡድኖች ያስጠጋቸዋል።

የተጋጣሚዎቹን ሰሞንኛ አጨዋወት ስንመለከት ነገ ፈጠን ያለ የማጥቃት ምልልስ እና የግብ ሙከራዎችን እንጠብቃለን። በሦስት የኋላ ተከላካዮች ሲቀርብ የሚታየው ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ ለማጥቃት ፍላጎት ከማሳየት አንፃር የማይታማ ቡድን ነው። አርባምንጭ ከተማ በዚህ ረገድ አጥብቆ ከመከላከል ጋር ብቻ ስሙ ሲነሳ ቢቆይም በሁለተኛው ዙር ከወገብ በላይ ባለው እሳቤው ላይ ለውጥ አሳይቷል። ለዚህ ማሳያ የሚሆነን በዚህ ዙር ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች እና በመጀመሪያው ዙር መጨረሻ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ወደ ግብ የሞከራቻውን ኳሶችን ለናሙና ብንወስድ የዘጠኝ ሙከራዎች ዕድገትን መመልከታችን ነው(ከ12 ወደ 21)።

ከማጥቃት ፍላጎት በተጨማሪ ቡድኖቹ ለተጋጣሚ አጨዋወት ምላሽ የሚሰጡበት መንገድ ትኩረታችንን ይስበዋል። እዚህ ጋር በየጨዋታው በብዙ ግብ ልዩነት በማሸነፍ የቀጠለው ቅዱስ ጊዮርጊስን የነገዎቹ ተጋጣሚዎች በተከታታይ ነጥብ ማስጣላቸውን ማንሳት ይቻላል። ከዚህ አንፃር ስንመለከተው እርስ በእርስ ሲገናኙም አንዳቸው የሌላኛቸው ጠንካራ ጎን ላይ የሚወስዱት እርምጃ የጨዋታውን ውጤት የመወሰን ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን እንገነዘባለን። ይህንን ስናስብም የቡድኖቹን የመስመር ጥቃት አለማንሳት ከባድ ነው።

የሜዳውን ስፋት በመስመር ተመላላሾቹ በዋነኝነት በቀኝ በብርሀኑ በቀለ የሚጠቀመው ሀዲያ ሆሳዕና የቦታው ተሰላፊዎች ወደ ሳጥን በሚያሻግሯቸው እንዲሁም ሳጥኑ መግቢያ ላይ ተገኝተው በሚፈጥሯቸው ዕድሎች ሲጠቀም ይታያል። የአርባምንጭን የዚህ ቦታ ጥንካሬ ለመረዳት የሙና በቀለ እና ፀጋዬ አበራን የአዲስ አበባ ከተማ ጥምረት መመልከት ብቻ በቂ ነው።

በመሆኑም በሽግግሮች ወቅት እነዚህ የመስመር ተሰላፊዎች ማጥቃቱን ለማገዝ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት የሚወስዱት የበላይነት አሸናፊነቱን ለቡድናቸው የማምጣት አቅም ይኖረዋል። አዞዎቹ ተጋጣሚን በራሱ ሜዳ የማፈን ልምዳቸው ሆሳዕና ላይ ሲተገበር (ሦስት የሆሳዕና ተከላካዮች ከሁለት የአርባምንጭ አጥቂዎች መገናኘታቸው ልብ ይሏል) የመስመር አማካዮቻቸው የቁጥር ብልጫ የመፍጠር ሚና እና ቦታ አያያዝ ከነብሮቹ የመስመር ተመላላሾች የጊዜ እና ቦታ አጠቃቀም የሚሰጠው ምላሽ ወሳኝ ይሆናል። ከዚህ አንፃር ስናስበው በተለይ አርባምንጬች የአደራደር ለውጥ አድርገው ሊገቡ የሚችሉበትም ዕድል ይኖራል።

ከኮሪደሮች ፍልሚያ ባለፈ በባህር ዳሩ ጨዋታ አዲስ ፈራሚው ግራማ በቀለን ያካተተው የነብሮቹ የኋላ ክፍል በመጀመሪያ ደቂቃዎች ያሳየው አለመናበብ በአህመድ ሁሴን ፍጥነት አፍንጫውን ስል ማድረግ ለቻለው እና ከኳስ ውጪም ቅብብሎችን ከጅምሩ ለማቋረጥ ለሚጥረው አርባምንጭ ዕድል ሊፈጥር ይችላል። ሆሳዕና ከፊት በሁለት ዘጠኝ ቁጥሮች ከመጠቀም ይልቅ አንዱን የአማካይ ባህሪ ያለው ተጫዋች በማድረግ ወደ ኋላ ተስቦ እንዲንቀሳቀስ ኃላፊነት ሲሰጥ መታየቱን ስናስብ መሀል ሜዳ ላይ የሚኖረው የቁጥር ብልጫ ይበልጥ የመጨመሩ ጉዳይ ደግሞ መሀል ለመሀል በሚሰነዘሩ ጥቃቶች ለማይረበሹት አርባምንጮች ፈተና የሚሰጥ ሆኖ እናገኘዋለን።

ሀዲያ ሆሳዕና እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ ግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳህ እና አማካዩ ሳምሶን ጥላሁንን በጉዳት ያጣል። አርባምንጭ ከተማም እንዲሁ በአዲስ አበባው ጨዋታ ተቀይሮ ገብቶ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ኬኒያዊው አጥቂ ኤሪክ ካፓይቶን እንደማይጠቀም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ከዚህ ውጪ ሁለቱም ተጋጣሚዎች በቅጣት ምክንያት የሚያጡት ተጫዋች አይኖርም።

ጨዋታውን ኤፍሬም ደበሌ በመሀል ዳኝነት ሲመሩት ለዓለም ዋሲሁን እና ሶሬሳ ድጉማ በረዳትነት ዮናስ ካሳሁን ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ለሁለተኛ የውድድር ዓመት በሊጉ የተጋናኙት ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለቱ በ 1-1 ውጤት ሲጠናቀቁ አርባምንጭ ከተማ አንዱን ጨዋታ 1-0 ማሸነፍ ችሎ ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

ያሬድ በቀለ

ፍሬዘር ካሳ – ቃለአብ ውብሸት – ግርማ በቀለ

ብርሃኑ በቀለ – እያሱ ታምሩ – ተስፋዬ አለባቸው – አበባየሁ ዮሐንስ – ሄኖክ አርፌጮ

ሐብታሙ ታደሠ – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን

አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ወርቅይታደስ አበበ – አሸናፊ ፊዳ – ማርቲን ኦኮሮ – ተካልኝ ደጀኔ

ሙና በቀለ – አቡበከር ሸሚል – እንዳልካቸው መስፍን – ፀጋዬ አበራ

አህመድ ሁሴን – ሀቢብ ከማል

ያጋሩ